የጠቋሚዎች መብዛት ለዕጩነትና ለፓትርያሪክነት መመረጥን አያረጋግጥም

የዘገባውን ሙሉ ይዘት ደግመው ይመልከቱ

 • ለአቡነ ሳሙኤል የተካሄደው የጠቋሚዎች ዘመቻ የኮሚቴውን አባላት አስጨንቋል
 • በቡድን የተሰጡ ጥቆማዎች ተቀባይነት አላገኙም
 • ዕጩዎችን ለመለየት ከምርጫ ሕገ ደንቡ በተጨማሪ አለ የተባለው አሠራር አነጋግሯል
 • ከሀገር ውጭ ስምንት አህጉረ ስብከት መራጭ ተወካዮቻቸውን ይልካሉ ተብሏል
 • ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሚቴው አባላት መካከል ተገኝተዋል
Election comittee PR

የአስመራጭ ኮሚቴው ሁለተኛ ዙር መግለጫ ሲነበብ (ፎቶ ማኅበረ ቅዱሳን)

የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ዛሬ፣ የካቲት ስምንት ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ላይ ሁለተኛ ዙር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ከተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ በተለየ አኳኋን በሦስት ዙር ከጋዜጠኞች ለቀረቡት በርካታ ጥያቄዎችም የኮሚቴው አባላት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚቴው በመግለጫው እንዳመለከተው፣ ካህናትና ምእመናን ስድስተኛው ፓትርያሪክ ይኾናል የሚሉትን አባት በአካልና በፋክስ እንዲጠቆሙ በተላለፈው መልእክት ከየካቲት 1 – 8 ቀን 2005 ዓ.ም በርካቶች ጥቆማቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹መላው የቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ ሰምተን ጸሎታችንን ለፈጣሪያችን በማቅረብ ላይ ነን›› ያለው መግለጫው በቀሪው ጊዜ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ጸሎቱ የምርጫው ሂደት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ካህናትንና ምእመናን አሳስቧል፡፡

የካህናቱና ምእመናኑ ጥቆማ የመስጠቱ የጊዜ ሰሌዳ በዛሬው ዕለት ከ10፡00 በኋላ የተጠናቀቀ ሲኾን ከነገ የካቲት 9 ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ዕጩዎችን የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚካሄደው ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለማቅረብ አስመራጭ ኮሚቴው ውይይቱን እንደሚቀጥል በመግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡ ኮሚቴው ለዕጩዎች ልየታ በሚያካሂደው ውይይት ከካህናትና ምእመናን የተሰጡ ጥቆማዎችን በግብአትነት ብቻ እንደሚጠቀምበት ነው የገለጸው፡፡

መላው የኮሚቴው አባላት በተገኙበት የተሰጠው ሁለተኛ ዙር መግለጫ፣ በሰብሳቢው ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከተነበበ በኋላ ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡ ጥያቄዎቹ ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ÷ የምርጫው ሂደት የተለያየ ፍላጎት ካላቸው አካላት ተጽዕኖ የጸዳ ስለመኾኑ፣ ኮሚቴው የተሰጡ የካህናትና ምእመናን ጥቆማዎችን በግብአትነት ብቻ የሚጠቀምና የራሱን ተጨማሪ አሠራሮች የሚከተል በመኾኑ የጥቆማው ፋይዳ ምን ያህል እንደኾነ፣ ስለ ጥቆማ መስጠቱ ያልሰሙ፣ መረጃው ያልደረሰባቸው አህጉረ ስብከት እንደሚበዙና እንቅስቃሴው በአዲስ አበባ የተገደበ ስለመኾኑ፣ ይህም በቀጣይ ኮሚቴው መልእክቱን ለካህኑና ምእመኑ ለማድረስ ያለበትን ውስንነት እንደሚያሳይ፣ በኮሚቴው የዕጩ ልየታ ሂደት ለዕጩ ፓትርያሪክነት መስፈርቱን ያሟሉት አባቶች ከአምስት የሚበልጡበት ኹኔታ ቢኖር እንዴት ወይም በምን አሠራር ይጣራሉ/ይወዳደራሉ፤ በጥቆማው ስለተሳተፈው ሰው ብዛት መረጃው ይታወቃል ወይ፤ በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ የተለዩ ዕጩዎችን መረጃ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ለመቀበል የሰፈረው ድንጋጌ በኮሚቴው የጊዜ ሰሌዳ ለምን አልተከበረም ወይስ ተለዋጭ አሠራር ተዘርግቷል ወይ፤ በምርጫው እንደሚሳተፉ የተገለጹት መራጮች ብዛት 800 ነው – ትክክለኛ ስሌት ነው ወይ፤ ይህ አኀዝ ከዚህ በፊት በተከናወኑት ፓትርያሪኮች ምርጫ ከተሳተፈው መራጭ በእጅጉ እንደሚበልጥ የተደረገው ንጽጽር በሦስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምርጫ ጊዜ ከተመዘገበው 1133 መራጭ (990 ተሳትፈዋል ተብሏል) የሚያንስ በመኾኑ መረጃው ትክክለኛ ነው ወይ የሚሉ ናቸው፡፡

ጋዜጣዊ ጉባኤው በአቶ ባያብል ሙላቴ የተመራ ሲኾን ለጥያቄዎቹ ምላሽ በመስጠት በዋናነት÷ የኮሚቴው ዋና ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ፣ የኮሚቴው የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ባያብል ሙላቴ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የኮሚቴው አባላት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ መልአከ ሰላም ዓምደ ብርሃን ገብረ ጻድቅ፣ ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ ከእነርሱም ጋራ በመግለጫው ላይ የተገኙት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እየተፈራረቁ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Lique Maemeran Fantahun MUche

ዋና ጸሐፊው ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ

ኮሚቴው የተለያየ ፍላጎት ካላቸው አካላት ተጽዕኖ ምን ያህል ነጻ ነው ለሚለው ጥያቄ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ በሰጡት ምላሽ÷ እኛ እስከምናውቀው ድረስ ይህ ዓለማዊ ምርጫ አይደለም፤ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማገልገል የሚካሄድ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምርጫ ነው፤ ምንም ዐይነት ተጽዕኖ የሌለበት፣ ከምንም ዐይነት ተጽዕኖ የጸዳ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቻ ተብሎ የሚካሄድ ምርጫ ነው ብለዋል፡፡ የኮሚቴው አባል ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ በበኩላቸው፣ የምርጫው ሂደት በቀኝም በግራም ከማንኛውም አካል ተጽዕኖ የለበትም፤ ይህን ላረጋግጥላችኹ እወዳለኹ በሚል አጽንዖት ተናግረዋል፡፡

በካህናቱና ምእመናኑ የተሰጡ ጥቆማዎች በሺሕ እንደሚቆጠሩ ዋና ጸሐፊውና የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው የገለጹ ሲኾን ፋይዳቸውን በተመለከተ ኮሚቴው ለሚያካሂደው የዕጩ ፓትርያሪኮች ልየታ እንደ ግብአት ብቻ እንደሚያገልግሉ ነው ያመለከቱት፡፡ አንዱ አባት በአንድ ሺሕ ሰው ቢጠቆም፣ ሌላው አባት ደግሞ በአንድ ሰው ቢጠቆም ጥቆማው ከጥቆማነት ባሻገር በዕጩ ፓትርያሪክነት መካተትን ወይም በፓትርያሪክነት መመረጥን እንደማያረጋግጥ ያስረዱት የአስመራጭ ኮሚቴው ሓላፊዎች፣ በቡድን ወይም ተቋምን በመወከል ‹‹እገሌን ጠቁመናል›› ወይም ‹‹እገሌን መርጠናል›› በሚል የመጡ የፊርማ ማሰባሰቦች ወይም ማመልከቻዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

ጥቆማውን እንደ ግብአት ከመጠቀም ባሻገር ለፓትርያሪክነት የሚቀርቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በኮሚቴው የሚለዩት፣ በምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 5 ከተዘረዘሩት ዐሥራ አንድ መስፈርቶች አንጻር እንደኾነ ያብራሩት የኮሚቴው ሓላፊዎች፣ ዕጩ ፓትርያሪኮችን ለመጨረሻ ጊዜ ወስኖ የሚያስታውቀው ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መኾኑን ጠቅሰዋል፤ ተመራጩ ፓትርያሪክም የሚታወቀው በምርጫው ቀን በሚሰጥ የመራጮች ድምፅ መኾኑን አስታውሰዋል፡፡

ሐራዊ ምንጮች ከጉዳዩ ጋራ በተያያዘ ያሰባሰቧቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት÷ የአዲስ አበባ አራት አህጉረ ስብከት፣ የደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት በማመልከቻ ደብዳቤ፣ የመቐለ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት በፋክስ÷ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለዕጩ ፓትርያሪክነት እንዲጠቆሙ ከዚህም አልፎ በፓትርያክነት እንዲመረጡ እንደ ሀገረ ስብከትና እንደ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ለአስመራጭ ኮሚቴው ማመልከቻዎችና ፊርማዎች (እስከ ሦስት ሺሕ ሰዎች ተብሏል) መላካቸውተነግሯል፡፡

ብፁዕነታቸውን ለፓትርያሪክነት ያበቋቸዋል ተብለው የታመነባቸውንመግለጫዎች በመዘርዘር አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ አህጉረ ስብከት ደረጃ የተካሄደው የጥቆማ ዘመቻ፣ሥራ አስኪያጆችንና በሥራ አስኪያጆቹ ተጽዕኖ ሥር ያደሩ ናቸው የሚባሉ ሓላፊዎችን በቀጥታ የስልክ ግንኙነትበማግባባት ጭምር መከናወኑ ነው የተነገረው፡፡የጥቆማ ዘመቻውን ለማስተባበር ብፁዕነታቸው በሊቀ ጳጳስነት የሚመሩት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ቢሮና በአንዳንዶችም መረጃ የኮሚሽኑ ሀብት፣የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱና ሓላፊዎቹ ሳይቀሩ የቅስቀሳ ኀይሎችና ማእከላት ኾነው ማገልገላቸውተዘግቧል፡፡

ለብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የመዝመቱ፣ የማግባባቱ ግፊት÷ በነገር ሁሉ ለየአህጉረ ስብከቶቻቸውሊቃነ ጳጳሳት የመታዘዝ ልማድ ያላቸውን ሥራ አስኪያጆችንና ሌሎች መራጮችን (ከየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆችን ጨምሮ 13 መራጮች አሉ) አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተታቸው ተሰምቷል – በተለይም በዕጩነት ለመካተት፣ በፓትርያሪክነትም ለመመረጥ ፍላጎት ያሳዩ አባቶች በሚመሯቸው አህጉረ ስብከት፡፡

የዘመቻውኀያልነት አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከት የተሰጋው መራጮችን ብቻ ሳይኾን ጥቆማዎችን እንደ ግብአት በመጠቀም፣ ለፓትርያሪክነት የሚመረጡ ዕጩዎች በሚመዘኑባቸው መስፈርቶች መሠረት ዕጩ ፓትርያሪኮችን የመለየትሥራውን በቀጠለው የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ዘንድም መኾኑ አሳዛኝ ነው፡፡ ‹‹በግልጽ ማመልከቻ፣ በፋክስና በፊርማ ስብስቦች እንደ ቡድን የመጡ ጥቆማዎችን ብንመልስም ግፊታቸው በአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ላይ ጫና እንደሚፈጥር ግልጽ ነው፤›› ይላሉ የሂደቱ ተከታታዮች፡፡

ጥቆማዎቹ የተሰበሰቡባቸው ቅጾች፣ ጠቋሚዎች ስድስተኛው የቤተ ክርስቲያናችን ፓትርያሪክ ሊኾን ይገባል የሚሉትን አባት የሚጠቁሙት በቲፎዞ ወይም በአድሏዊነት ሳይኾን ስለሚጠቁሙት አባት ተገቢና ትክክለኛ መረጃ በመያዝ መኾኑን ለመለካት የሚያስችሉ መጠይቆች እንደተካተቱበት የኮሚቴው ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ባያብል ሙላቴ ገልጸዋል፡፡መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊት ስለሚፈጽሙት ቃለ መሐላ በሚያመለክተው የምርጫ ሕገ ደንብ አንቀጽ 11 ንኡስ አንቀጽ አንድ÷ መራጮች ያለምንም አድልዎና ግላዊ ፍላጎት፣ በማስተዋልና በጥንቃቄ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል ብለው የሚያስቡትን አባት ብቻ እንዲመርጡ፣ ክፋትን፣ ተንኰልን፣ ቅናትንና ምቀኝነትን ከኅሊናቸው እንዲያርቁ፣ የዝምድና ወይም የጓደኝነት ትስስር እንዳይገፋፋቸው ያሳስባል፤ ለዚህም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፊት ማእምረ ኅቡአት በኾነው በኀያሉ በእግዚአብሔር ስም ይምላሉ፤ ‹‹ቃል የገባኹትን ባላደርግ በዚህ ዓለምም ኾነ በሚመጣው ዓለም በታላቁ የፍርድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት እጠየቅበታለኹ›› በማለት መፆር መስቀሉን ይዘው በሚያስምሏቸው በዐቃቤ መንበሩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፊት ይገዘታሉ፡፡

Abune Estifanos, Abune Samuel and Abune Gorgorewos

ከግራ ወደ ቀኝ – ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ

የቃለ መሐላው አንቀጽ በተግባር ተፈጻሚ ኾኖ፣ መራጮች ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል ብለው ያመኑበትን ብቻ ቢመርጡ ታላቅ ቁም ነገር ነው የሚሉ ታዛቢዎች፣ በሳምንቱ ውስጥ ለጥቆማው የታየው ኀያል ዘመቻና ማግባባት ግን መራጮች በቃለ መሐላው ተፈጥመው ለኅሊናቸውና ለእግዚአብሔር በመገደድ ሳይኾን ለጎጤ፣ ለእህል ውኃዬ፣ ለወንበሬ ብለው እንደማይመርጡ ዋስትና የሚያሰጥ እንዳልኾነ ይሰጋሉ፡፡

በዕጩ ጥቆማው ከፊሎቹ አባቶች ለማለት በሚቻል ደረጃ የመጠቆም ዕድል ሊያገኙ እንደሚችሉ የተገመተ ሲኾን መልክ ለይቶ ዐደባባይ ወጥቶ ግልጽ ቅስቀሳ የተካሄደለት ግን ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሌላአይገኝም፡፡ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ራሳቸው ቀደም ብለው በነገሩ ያሰቡበት በሚመስል አኳኋን በ31ው የመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ባዘጋጀው ዐውደ ትምህርት በተፈጠረው መድረክ ጎልተው እንዲወጡ መደረጉ፣ ለዐውደ ትምህርቱ ተሳታፊዎች እንዲከፈል የተደረገው አበል በምርጫው ሥራ አስኪያጆችን ጨምሮ ድምፅ በመስጠት የሚሳተፉትን የአህጉረ ስብከት ተወካዮች የማግባባት ዘመቻ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

አጠቃላይ ጉባኤው በቆየባቸው ስድስት ቀናት ለተሳታፊዎች መስተንግዶ በተበተኑት የሻይ ቡና ኩፖኖች ጀርባ ላይ ‹‹የብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ዕድሜ ያርዝምልን›› ከሚሉት ምስጋናዎች ጀምሮ ‹‹ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ለበለጠ ክብር/ሥልጣን ያብቃልን›› የሚሉ ጥቁምታዎችም ነበሩ፡፡ በቀጣይም የመንፈሳዊ ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት በእግር ጉዞ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ በመሄድ የጠቆሙት አባት በዕጩነት ከመካተትም በላይ ለፕትርክና እንዲሠየም ጥያቄ ያቀርባሉ የሚል መረጃ ተሰምቷል፡፡

ጥቆማ ከመስጠት ያለፉትእኒህ ሁሉ ግፊቶች በፈጠሩት አእምሯዊ ኹኔታ ምክንያት፣ አስመራጭ ኮሚቴው ያሻውን ያህል መመዘኛና ተጨማሪ ውስጣዊ አሠራሮች ቢጠቀም ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ከዕጩ ተወዳዳሪነት ውጭ ማድረግ እንዳይችል የማያፈናፍን (stifling) ቅርቃር ውስጥ እንደከተተው ታውቋል፡፡ በተለይ አስመራጭ ኮሚቴው ጽ/ቤት ድረስ በቡድንየሚመጡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች በፈጠሩት አጣብቂኝ የተነሣ አንዳንድ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ብፁዕነታቸው በዕጩነት እንዳይካተቱ ሐሳብ እስከመስጠት መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ አንዳንዶቹ የካቲት 16 ቀን ዕጩዎችን ወስኖ ለማስታወቅ ስብሰባውን በሚጀምረው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ በአድማነት የፈረጁትን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን የመጠቆም ‹ከመጠን ያለፈ› እንቅስቃሴ አቤቱታ ሳያሰሙበት አይቀርም ተብሏል፡፡

በዕጩ ልየታው ክልላዊ ተወላጅነት (በመንግሥት አነጋገር የብሔር ተዋፅኦ) እንደ አንድ ማነጻጸሪያ ሊካተት እንደሚችል የሚናገሩ ምንጮች፣ የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የምርጫ ዘመቻ ተግዳሮቶች ከዚህም ሊነሣ እንደሚችል ይገምታሉ፤ ከየክልሉ አንድ አንድ በውክልና ነውና፡፡ ከዚህ በመነሣት የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የምርጫ ተግዳሮት፣‹‹ከጥቆማ ያለፈ ነው››የተባለው የደጋፊዎቻቸው የማግባባት ዘመቻ ብቻ ሳይኾን፣እንደርሳቸው በዕጩነት ለመካተት ከመቻል አልፈው ለፕትርክናው መንበርም ሊበቁ ይችላሉ የሚባሉ በተወላጅነት ትግራዋይ የኾኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መብዛታቸው ነው፡፡

His Grace Abune Lukas

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ

በመንፈሳዊነታቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በአቋመ ጽኑነታቸው፣ በሥራ ልምዳቸውና ለምነው ሳይኾን ተጠይቀው ለኤጲስ ቆጶስነት በመብቃታቸው የሚታወቁት የምዕራብ ሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ቋሚ ሲኖዶሱን ለማጠናከር ከተመረጡት ስምንት አባቶች መካከልየኾኑት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ አንዱ ናቸው፡፡ የብፁዕ አቡነ ሉቃስ ተጠቃሹ የምርጫ ተግዳሮት እንደ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከመንግሥት ጋራ ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ አለመኾኑና ጎልቶ ያልወጣ የዐደባባይ ሰውነት ነው፡፡

አንዳንድ ወገኖች ማኅበረ ቅዱሳን ብፁዕ አቡነ ሉቃስን ለቀጣይ ፓትርያሪክነት በመደገፍ ይንቀሳቀሳል በሚል የተለያዩ አጋጣሚዎችን ቢጠቅሱም የምርጫውን ሂደት በጥንቃቄ የሚከታተሉ ወገኖች በአንጻሩ፣ ማኅበሩ ወስኖ ያስቀመጠው አባት አለመኖሩን፣ ለብፁዕ አቡነ ሉቃስም ያደረገው የተለየ የድጋፍ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ይጠቅሳሉ፤ እንዲያውም በዚህ የተነሣ ጥቂቶቹ ማኅበሩን አምርረው የሚወቅሱ ናቸው፡፡

His Grace Abune Matyas

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ

ሌሎቹ የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ተገዳዳሪዎች በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው÷ በሹመት ቅድምናቸው፣ ከአስመራጭ ኮሚቴው አባላት መካከል በሰብሳቢው ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስና በሌላው አባል ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ዘንድ እንዳላቸው የሚነገረው ጥብቅ ድጋፍ፣ከአስተዳደር ይልቅ ለመንፈሳዊ አገልግሎት (ጸሎተ ቅዳሴ) ማድላት፣ ለዘብተኝነትና ዓለም አቀፍ ልምድ (ሰውነት)፣ ብዙዎች በጸጋነት የሚጠቅሱላቸው የአባትነት ዐይነተኛ መልክና ሞጎስ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ‹ፖሊቲካ›ና ውጥንቅጥ ርቀው በመቆየታቸው በወገንተኝነት የሚከሣቸው አለመኖሩ፣ ለዕርቀ ሰላሙ ሂደት ያላቸው ቀናነት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ‹‹ከምርጫው በፊት በፕትርክና ሾሟቸዋል›› በሚባለው በመንግሥት ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከወዳጃቸው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጋራ በዕጩ ልየታና በምርጫ ሊያወዳድራቸው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ከብፁዕነታቸው አባታዊ ‹ተክለ ሰውነት› እና ብፁዕነታቸውን ለማስመረጥ የሚሯሯጡት የመንበረ ፓትርያሪኩ ሹመኞች÷ የቤቱን ወግና ተንኰል የተካኑበት እነንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣መጋቤ ካህናቱ ሊቀ ማእምራን ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፣ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ የአሲራ መቲራው እነአባ ገብረ መድኅን እንዲሁም አንዳንድ የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎች መኾናቸው የብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን የምርጫ ተግዳሮት የዋዛ አያደርገውም፡፡

ሦስተኛው የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የምርጫ ተገዳዳሪ፣ የምሥራቅ ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ ናቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ የቀድሞው ፓትርያሪክ በጠረጉላቸው ጎዳና ከመንግሥት አካላት ጋራ ያዳበሩት ቅርበትና ‹‹በጋራ የፈጸሟቸው ተግባራት››፣ ከቀድሞው ፓትርያሪክ ጋራ በመነጋገር ጥቂት ለማይባሉ ገዳማትና አድባራት አለቆች ‹‹የዋሉት ውለታ›› (በሹመት፣ በውጭ ተልእኮ) እንዲሁም የሚደነቅላቸው ነገር ዐዋቂነታቸው የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ወደረኛ እንደሚያደርጋቸው ተገምቷል፤ የዓዲግራት ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስም እንዲሁ፡፡ ከእኒህ አባቶች ጋራ በዕጩ ተወዳዳሪነት ለሚታሰቡ ሌሎች አባቶች የሚደረገው የጥቆማና ድጋፍ እንቅስቃሴ ሲጨመር አስመራጭ ኮሚቴው የተለያየ ፍላጎት ያላቸው የውጭና የውስጥ አካላት ተጽዕኖ አይጫነውም ማለት አዳጋች ነው፡፡

ኮሚቴው መረጃዎችን ለሕዝብ ለማድረስ ስላለበት ውስንነት በተመለከተ፣መልእክቱን በማስተላለፍ ረገድ የሚዲያውን እገዛ በማግኘታቸው የኮሚቴው አባላት ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ለጥቆማው አቀባበል በመብራት መቋረጥ ሳቢያ የማይስተጓጎሉና በጀኔሬተር የሚሠሩ ሁለት የፋክስ አድራሻዎችን መመደባቸውን፣ በየአህጉረ ስብከቱ ስልክ በመደወል ሰባክያነ ወንጌል ለምእመኑ መልእክቱን እንዲያስተላልፉ ማሳሰቢያ ለመስጠት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በርካታ ጠቋሚዎች የተመዘገቡት ከአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት መኾኑን ያልሸሸጉት የኮሚቴው አባላት ከሌሎች አህጉረ ስብከትና ከአውሮፓም ጥቆማዎችን መቀበላቸውን ተናግረዋል፡፡

የስድስተኛው ፓትርያሪክ መራጮች ብዛት በተመለከተ ባለፈው መግለጫ የተመለከተው አኀዝ (800) እንደ መነሻ የተሰጠ እንጂ የመጨረሻ አይደለም ተብሏል፡፡ በየጊዜው ከውጭ አህጉረ ስብከትና ከሀገር ውስጥም ለመራጭነት ዕውቅና የሚሰጣቸው አካላት ሲጨምሩ አስመራጭ ኮሚቴው በቃለ ጉባኤ ይዞ እየተወያየ በመወሰን ሊጨምር እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ከሀገር ውጭ የስምንት አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን ጨምሮ አንድ፣ አንድ የካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች በድምሩ 32 መራጮች፣ ከአኀት አብያተ ክርስቲያን መካከል ከኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ባለን የቆየ ስምምነት መሠረት አራት ተወካዮች በድምፅ የሚሳተፉ ሲኾን ይህም በሂደት የመራጮችን ጠቅላላ ቁጥር እስከ 850 ሊያደርሰው እንደሚችል ተገልጧል፡፡

የሀገር ውስጥ መራጮች ጠቅላላ ወጪ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚሸፈን ሲኾን የውጭዎቹ ግን በራሳቸው እንደሚሸፈን ታውቋል፡፡ የስድስተኛው ፓትርያሪክ መራጮች ጠቅላላ ብዛት በሦስተኛ ፓትርያሪክ ምርጫ ወቅት ከተመዘገበው ጋራ ሲነጻጸር አንሶ ሳለ ‹‹በእጅጉ የላቀ ነው›› በሚል ለቀረበው ጥያቄ የአስመራጭ ኮሚቴው ዋና ጸሐፊ ‹‹እርሱን የሚያሳይ ዶኩመንት አላገኘንም›› የሚል ምላሽ በመስጠት የጋዜጠኛውን እገዛ ጠይቀዋል፡፡

በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ አስመራጭ ኮሚቴው ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ከለየ በኋላ የዕጩዎችን የትምህርት ደረጃ፣ ችሎታና ልምድ ለዐሥራ አምስት ቀን ይፋ በማድረግ ከሕዝብ ጥያቄዎችና አስተያየቶች እንደሚቀበል የሰፈረው ድንጋጌ በኮሚቴው የምርጫ መርሐ ግብር ለምን እንዳልተካተተ ለቀረበው ጥያቄ ዋና ጸሐፊው ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ ሲመልሱ÷ ‹‹ከምርጫ ሕገ ደንቡ በተጨማሪ በቅ/ሲኖዶሱ ጸድቆ ለአስመራጭ ኮሚቴው የተሰጠው ሕግ አለ፤ ይህ ሕግ ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ኮሚቴውን ተግባራት እየተከታተለ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ እንደሚችል የተገለጸበት ሕግ ነው፡፡ በሕጉ መሠረት ኮሚቴው ያዘጋጀውን የድርጊት መርሐ ግብር ለቋሚ ሲኖዶስ አቅርቦ  ቋሚ ሲኖዶሱምልአተ ጉባኤው በተሰጠው ሥልጣንና ውክልና የጊዜ ሰሌዳ ትክክል ነው ብሎ አጽድቆ ሰጥቶታል እንጂ አስመራጭ ኮሚቴው ሕግ የማውጣትም ሆነ ሕግ የመለወጥ ሥልጣን የለውም፤›› ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጋራ በተያያዘ በምርጫ ሕገ ደንቡ የሰፈረው 15 ቀን ቢካተት ጊዜው ወደ ዐቢይ ጾም ስለሚገባ በመዋዕለ ጾም ምርጫና በዓለ ሢመት ላለመፈጸም፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ከ40 – 80 ቀናት ተተኪውን ፓትርያሪክ መሾም የሚገባት ቤተ ክርስቲያንም ያለመሪ ለተጨማሪ ጊዜ እንዳትቆይ ለማድረግ÷ ኮሚቴው በቀረጸውና ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ባጸደቀው የተሻሻለ ‹ፕሮፖዛል› መሠረት የጊዜ ሰሌዳው መውጣቱን ዋና ጸሐፊው አስረድተዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው በይፋ ያልታወቀውን ተጨማሪ ሕግ አገልግሎት ‹‹ለፓትርያሪክነት የሚበቁ ከአምስት በላይ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩ በምን ትለያላችኹ?›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስም ተጠቅመውበታል፡፡ ይህን ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ካጸደቀው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ በተጨማሪ አለ የተባለው ሕግ ምንነትና ትክክለኛ አገልግሎት ከግልጽነት አኳያ አወያይ መኾኑ አልቀረም፡፡

‹‹ዐሥር አባቶች የዕጩነት መመዘኛው ቢያሟሉ አምስት ዕጩዎችን የምትለዩት እንዴት ነው?›› ለሚለው ጥያቄ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው፣ ከዐሥርም የበለጠ ቁጥር ሊገኝ እንደሚችል በማመልከት ዋናው ነገር በተቀመጠው መመዘኛ መስፈርት መሠረት ከሦስት ያላነሱ ከአምስት ያልበለጡ ዕጩዎችን ነው ለቅዱስ ሲኖዶሱ የምናቀርበው ብለዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሚቴው ሁለተኛ ዙር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የታዩት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስና ሰብሳቢው ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ለጥያቄው በሰጡት መልስ ደግሞ፣ አስመራጭ ኮሚቴው ወሳኝ አካል እንዳልኾነ በመጥቀስ ዋና ተግባሩ ብቁ አባቶችን መርጦ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ማቅረብ ብቻ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ኮሚቴው የሚያቀርባቸው አባቶች የቱንም ያህል ቁጥር ቢኖራቸው ምልአተ ጉባኤው ዕጩ መኾን የሚገባቸውን ተወዳዳሪዎች ሊሠይም እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ራሳቸውን ከአስመራጭ ኮሚቴው ስለማግለላቸው ሲዘገብ ቢቆይም ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱና የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ባበዙባቸው ውትወታና ልመና ዘግይተውም ቢኾን ኮሚቴውን መቀላቀላቸው ተዘግቧል፡፡ በተለይም ብፁዕነታቸው የመጡበት ወቅት ኮሚቴው የጥቆማ አቀባበል መርሐ ግብሩን ጨርሶ ወደ ዕጩ ልየታ የሚገባበት መኾኑን ያስታወሱ ታዛቢዎች፣ ኹኔታውን ለመንበረ ፕትርክናው ከሚደረገው የተለያዩ ቡድኖች ፉክክር ጋራ በማያያዝ ‹‹ሚዛን እንዲያነሡ›› ይላሉ፡፡ የአምስተኛውን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ምርጫ ባስፈጸመው አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የምክትል ሰብሳቢነት ሓላፊነት እንደነበራቸው ይታወሳል፡፡

የስድስተኛውን ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ስብሰባ ብዙውን ጊዜ የሚመሩት ምክትል ሰብሳቢው ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ መኾናቸው ተመልክቷል፡፡ የመጀመሪያው የኮሚቴው ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ቀን ከሀ/ስብከታቸው ተጉዘው የገቡትና መግለጫውን በንባብ ያሰሙት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ መግለጫ ላለማንበብም አመንትተው እንደነበር ተሰምቷል፡፡

ለመኾኑ በዕጩ ፓትርያሪክነት እነማን ሊካተቱ ይችላሉ?

Advertisements

6 thoughts on “የጠቋሚዎች መብዛት ለዕጩነትና ለፓትርያሪክነት መመረጥን አያረጋግጥም

 1. Anonymous February 16, 2013 at 2:01 am Reply

  The fools can only believe you about your claim whether this election is free from TPLF influence. You cannot fool us. We know this is just coverup to make it TPLF free election.

 2. ምእመን February 16, 2013 at 12:59 pm Reply

  እንደ ድርድሩ ምርጫውም አሜሪካ ውስጥ መደረግ አለበት? ከፖለቲካ ነፃ እንዲሆን ምንመደረግ ነበረበት? ጥሩ አባት እግዚአሔር እንዲሰጠን እግዚአብሔርን መለመን የኛ ሀሳብ ምንም ለውጥ አላመጣምና

 3. abacoda February 16, 2013 at 2:12 pm Reply

  ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች
  በዚህ ወቅት እየተካሄደ ባለው የቅዱስ ፓትርያርክ ምርጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣውን የምርጫ ሕግና ደንብ ጠብቆ እስከመጨረሻ ሊቀጥልበት ይገባል ማንኛውም የበተክርስቲያኒትዋ አማኝና ሀገር ወዳደድም በዚህ ወንበር እንዲቀመጥ የሚመርጠው አባት ከአሁን በፊት ምን ሰርተዋል ከአሁን በኃልስ ምን ሊሰራ ይችላል በማለት ከብሄርተኝነት እና መንደርተኝነት የጸዳ መሆኑንም በመገንዘብ ከአሁን በፊት በተሰጠው ኃላፊነት ላይ ዜጎችን ሁሉ በቤተክርስቲያኒትዋ ልጅነታቸው ብቻ በማየት በማቅረብ ሲሰራ የነበረ ለመሆኑ የሚወራለት ሳይሆን ሠርቶ ያሳየ ለቤተክርስቲያኒትዋ እድገት በር ከፋች የሆኑ መሪ እቅዶች በማዘጋጀት ፤ጠቃሚ የሆኑ መጽሐፍትን በመፃፍ ሆነ የጥናት መድረኮች በማዘጋጀት ሲደክም እንደነበረ የሚመሰከርለት ወንበር የሚያገኝ ተሸሚ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ድሃ ወገን ስራ ፍላጊ ዘመድ ባይጠፋውም ስራና ሰራተኛን ብቻ በማገናኝ የሚሰራ ለመሆኑ የተመሰከረለት አባት እንዲሆን ቢታሰብበት ከሙስና በጸዳ ዜጎችን ሁሉ በእኩልነት ያገለገለ ለመሆኑ ካህናት፤ አበው መነኮሳት ሊቃውንት የሚመሰክሩለት እና በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ኢትዮጵያና ቤተክርስቲያኒትዋን ለማሳደግ ራዕይ እና ዓላማ ያለው የሚሰራለት ሳይሆን የሚሰራ አባት ሊሆነን የሚችል የየትኛው ቋንቋ ይናገር እስከአሁን በሰራው የተመሰገነ ቢቻል በአይን የሚታይ ሥራ ያለው ቢሆን ቤተክርስቲያናችን ታድጋለች ሀገራችን ትባረካለች አገልጋዮች በእኩልነት ይስተናገዳሉ ሮሮ ይቀንሳል የሀብት ክፍል እኩልነት ይሰፍናል እና ለቤተክርስቲያን ከማሰብ አንፃር ምርጫው ብናከናወን እላለሁ ማን እስከ አሁን ምን ሰራ የሚለው ጉዳይ ወደ ኋላ ሊባል አይገባም ምክንያቱም ጌታችን መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ‹‹ገብር ሄር ወገብር ምእመን ዘበውሁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ››እንዳለው በሊቀጵጵስና ደረጃ ስንት ዓመታት ቆዬ ሳይሆን ምን ሰራ የሚባለው ነገር መኖር አለበት ምክንያቱም ወጥቶ ወርዶ መስራት በሚችልበት ወቅት ምንም ያልሰራ አባት በዚህ ከባድ ወንበር ከተቀመጠ በኃላ ይሰራል ተብሎ መገመትም መታሰብም ለበትም ወስብሀት ለእግዚአብሄር !!!!

 4. Anonymous February 16, 2013 at 7:38 pm Reply

  ጂቦች ተሰበሰቱና ውሳኔ አሳለፉ
  ውሳኔውም
  እንብላው ነበር
  መነኮሰ ማለት በላ ማለት ነው አሉ ሰባኪው

 5. Anonymous February 17, 2013 at 6:44 pm Reply

  Is this a blog established to promote the election of Abune Samuel? I have been following the blog and liked its up-to-date information. But, on wards, I think I understood the sidings of the blog and never trust again! Thank you for the information so far.

 6. Anonymous February 19, 2013 at 9:56 am Reply

  Egziabher Yehatiyatachinin Bizat; Yesewinetachinin Kifat; Yelibunachinin Timet Temelikito Hayimanotina Migibar Yelelew Abat Endayishomibin Kidus Fekadu Yihunilin!!! Endecherinetu Ewinetegnawin Abat Patriyarich Adirigo Endiseten{Endishomilin} Enileminew Enji Were[Mereja] Bichawin Yemifeyidew Guday Yelem::

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: