ቤተ ክርስቲያናችን በኮፕት ቴሌቪዥን ዕለታዊ የአየር ሰዓት ልታገኝ ነው

 • የቴሌቪዥን ጣቢያው ለኢትዮጵያውያን የጥምቀት ክብረ በዓል ሽፋን ሰጥቷል
 • የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለጥምቀት በዓል አከባበር የሰጠው ሽፋን ተተችቷል
 • ‹‹መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ለመገኘት ወደ ሀገር ቤት ከመጡ 1,284,892 የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ብር 11,726,662.777 ያስገባ ቢኾንም የበዓሉን ይዘት ለማጠናከር በየጊዜው የምትደክመው ቤተ ክርስቲያናችን ግን ከተገኘው ገቢ የድርሻዋን የምትጠቀምበት መንገድ አልተፈጠረም፡፡›› /የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ/

  ታዋቂው የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን ጣቢያ

  ታዋቂው የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን ጣቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአኀት አብያተ ክርስቲያን አንዷ ከኾነችው የኮፕት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኦፊሴሊያዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ (Coptic TV – CTV) ዕለታዊ የአየር ሰዓት መደብ ተሰጣት፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በየዕለቱ የአራት ሰዓታት የስርጭት ቆይታ እንደሚኖረው የተነገረውን የራሷን የአየር ሰዓት መደብ ያገኘችው÷ በ118ው የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ/መንበረ ፕትርክና እና በቤተ ክርስቲያናችን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን መካከል በተደረገ ንግግር እና በተደረሰው ስምምነት መኾኑ ተገልጧል፡፡ ዝርዝሩ በይፋ ያልተገለጸ ቢኾንም÷ ስምምነቱ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ጥንታውያን አኀት አብያተ ክርስቲያን መካከል እየተሻሻለና እየተጠናከረ ለመጣው ተቋማዊ ግንኙነት አንድ ተጨማሪ ርምጃ መኾኑ ተዘግቧል፡፡

በብፁዓን አባቶች የሚመራና ኻያ ካህናት የሚገኙበት የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ልኡክ ከታኅሣሥ 12 – 15 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተገኝቶ ከካህናት፣ ከሰንበት ት/ቤት አባላት፣ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ምሩቃን እንዲሁም ከሰባክያነ ወንጌል ጋራ የልምድ ልውውጥ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በሥልጠና ላይ የተመሠረተው ይኸው ልምድ ልውውጥ በቀጣይ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና መሰል የተቋማዊ መሻሻል ርእሰ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

የእስክንድርያ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ኦፊሴሊያዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የኾነው ኮፕቲክ ቴሌቪዥን (CTV)÷ ዋና ጽ/ቤቱ በግብጽ ካይሮ ይገኛል፤ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ስርጭቱን በሳተላይት የጀመረው እ.አ.አ በ2007 ነው፤ ዋነኛ የስርጭት ቋንቋው ዐረብኛ ሲኾን በግብጽና ሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ ግብጻውያን የሚዳረስ ነው፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያው ከኢትዮጵያው መንበረ ፓትርያሪክ የፊልም ዶኩሜንቴሽን ያገኘውንና ባለፈው ዓመት በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት የነበረውን የጥምቀት በዓል አከባበር የሚያሳይ ዝግጅት ጥር 12 ቀን 2005 ዓ.ም ማቅረቡ ተነግሯል፡፡ ለዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር ለሁለት ሰዓት የሚቆይ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚሰጥ ተጠብቆ እንደነበርም ተመልክቷል፡፡

ከአገራችን የብሮድካስት ሕግ የተነሣ የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ያደረገችው ክርስቲያናዊ ድጋፍ የሚደነቅ ቢኾንም በእኛ በኩል ‹‹ዕለታዊ እና ለአራት ሰዓት የሚዘልቅ ነው›› የተባለውን የአየር ሰዓት ለመጠቀም ብቻ ሳይኾን በአግባቡ ለመጠቀም በሚመለከተው አካል ዘንድ በማቴሪያል፣ በበጀትና ለሞያው አግባብነት ባለው የሠለጠነ የሰው ኀይል ረገድ ስለተደረገው ቅድመ ዝግጅት በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡

በአሁኑ ወቅት በሚዲያና ሚዲያ ነክ መንገዶች መንፈሳዊ አገልግሎት እየተሰጠ የሚገኘው በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መመሪያ ሥር በሚዘጋጀው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣና ልሳነ ተዋሕዶ ዘኦርቶዶክስ መጽሔት ሲኾን የሰው ኀይል አቅማቸውና በጀታቸው ለብሔራዊቷ እና ኵላዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን አሳፋሪ ሊባል የሚችል ነው፡፡ በቀድሞው ፓትርያሪክ ዘመን በተገነባው ጽርሐ መንበረ ፓትርያሪክ የተሟላ ሊባል የሚችል ስቱዲዮ እና የስቱዲዮ መሣሪያዎች ስለመኖራቸው ሲነገር ቢቆይም ከዶኩመንቴሽን ያለፈ ሥራ ሲሠራበት አልታየም፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር የሰጠው የቀጥታ ሽፋን ቤተ etv_liveክርስቲያናችን በየጊዜው ከምታሰማው አቤቱታ የተማረ አልኾነም፡፡ የቀጥታ ስርጭቱ ሥነ በዓሉን በተሟላ ገጽታው የማያሳይና የተቆራረጠ ነው፤ ቴሌቪዥኑ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን በሰጠበት የጃንሜዳው ባሕረ ጥምቀት በዓል አከባበር የተለያዩ የውጭ ቱሪስቶች በማቅረብ ተጠምዶ ታይቷል፡፡ ‹‹ከመንግሥት ሚዲያነቱ አንጻር ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ ነው፤ የመንግሥት ሚዲያ ስለኾነ ወደ ሃይማኖት ሥራ ማድላት የለበትም፤›› ከሚሉና ከመሳሰሉ ሰበቦች የሚነሡትን ይህን የድርጅቱን ስንኵል አሠራር የተቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሕዝብ ግንኙነት መመሪያ÷ ‹‹ይህ አሠራር በራሱ ሚዛናዊ ነው ለማለት ያስቸግራል›› በማለት አጣጥሎታል፡፡

የጥምቀት በዓል አከባበርን በቀጥታ ሥርጭት አማካይነት ለመላው ዓለም የሚያስተላልፈው ቴሌቪዥኑ፣ ‹‹በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩ ዕድል ይሰጣል፤ ጎብኚዎች የበዓሉን ኹኔታ ተመልክተው በሌላ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ከማድረግ አንጻር የማይተካ ሚና ይጫወታል፤›› ያለው መምሪያው÷ ‹‹በሥርጭቱ ወቅት አንዱን ይዞ ሌላውን በመልቀቅ ተመልካቹን ግራ ከማጋባት ይልቅ ለተመልካቹም ለጎብኚውም የሚስቡትን የበዓል ዝግጅቶች፣ ለምሳሌ፡- የካህናቱን ዝማሬና ወረብ፣ የታቦታቱን የተረጋጋ ጉዞና የምእመናኑን መዝሙር፣ የባሕረ ጥምቀቱን መባረክ እንዲሁም የመረጨቱን ሥርዐት በማሰራጨት ጎብኚዎች የሚማረኩበትን ዕድል መፍጠር ሲገባው በቃለ መጠይቅ ጊዜን ማጥፋት ጉዳቱ እንደሚያመዝን ሊያጤነው ይገባል፤›› ብሏል፡፡

Jan Meda Bahire Timket

የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት

በዚህ ዓመት የታየው የድርጅቱ የከፋ አሠራር ደግሞ የዓመታዊ በዓሉን መጠናቀቅ እንኳ ሳይታገሥ ሳምንታዊ ወደኾነው የልጆች ፕሮግራም (የስቱዲዮ ዝግጅት) መሻገሩ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ በዓሉን የተመለከተ ትምህርተ ወንጌል የሰጡት የብፁዕ አቡነ ሉቃስ እና የዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ቃለ ምዕዳን ጨርሶ ሳይተላለፍ ቀርቷል፡፡ ሐራዊ ምንጮች ስለ ኹኔታው ለማጣራት ባደረጉት ጥረት÷ ቴሌቪዥን ጣቢያው ይህን ያደረገው፣ ‹‹ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለአየር ሰዓቱ መክፈል የሚገባውን ከአርባ ሺሕ ያላነሰ ብር ባለመክፈሉ ነው፤›› የሚል ሰበብ ተሰጥቷል፡፡ ግለሰቦች አጋጣሚውን በመጠቀም ቤተ ክህነቱን ከሚያስፈልገው በላይ ወጪ በማስወጣት መሥርተውት የቆዩትን ያልተገባ የጥቅም ግንኙነት ለመቁረጥ የጠ/ቤ/ክ ማኔጅመንት ክፍያውን እንዳይፈጸም ማድረጉ ታውቋል፡፡

የዘንድሮው የጥምቀት በዓል አከባበር አሰልቺ ይዘትና አቀራረብ ባላቸው ቃለ መጠይቆች እየተቆራረጠ እስከ ፍጻሜው እንዳይታይ ያደረገው ከክፍያው አፈጻጸም ጋራ በተያያዘ ሲካሄዱ የቆዩ የጥቅም ግንኙነቶችን ለማገድ ቢኾንም÷ ለመንግሥትም ይኹን የቱሪዝሙ ባለድርሻ ለኾኑት የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶች ባለቤት ለኾነችው ቤተ ክርስቲያናችን በቂና የተሟላ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን ለመንፈግ ምክንያት አይኾንም፡፡

በሕዝብ ግንኙነት መመሪያ ሓላፊው አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ አዘጋጅነት በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ የወርኀ ጥር እትም ‹‹የጥምቀት በዓል ከቱሪዝምና ሚዲያ አንጻር›› በሚል ርእስ የወጣ ጽሑፍ÷ ወደ አገራችን የሚመጡ ቱሪስቶች በጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት በእጅጉ በርክተው እንደሚታዩ ያስረዳል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ የሚጠቅሰው የመምሪያ ሓላፊው ጽሑፍ÷ በ2002 ዓ.ም 447,795 ቱሪስቶች የጥምቀትን በዓል ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ይጠቅሳል፡፡ በ2003 ዓ.ም ደግሞ 515,336 ቱሪስቶች ወደ አገራችን የገቡ ሲኾን በተመሳሳይ መልኩ በ2004 ዓ.ም የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት 321,761 ጎብኚዎች በጥምቀት በዓል ለመገኘትና ሌሎች የአገራችንን የቱሪስት መስሕቦች ለመጎብኘት መጥተው እንደነበር ጽሑፉ ይገልጻል፡፡

መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ለመገኘት ወደ ሀገር ቤት ከመጡ 1,284,892 የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ብር 11,726,662.777 ያስገባ ቢኾንም የበዓሉን ይዘት ለማጠናከር በየጊዜው የምትደክመው ቤተ ክርስቲያናችን ግን ከተገኘው ገቢ የድርሻዋን የምትጠቀምበት መንገድ አልተፈጠረም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የራሷን ሀብቶች በአግባቡ ከተጠቀመችና ከዚህ አገራዊ ገቢም ድጋፍ ከተደረገላት የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግና ጎብኚዎች አስፈላጊውን መረጃ አግኝተው ሌሎችን ለመጋበዝ የሚችሉበትን ኹኔታ ለመፍጠር ትችላለች፡፡

በሚዲያ በኩል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ገጽታዎችን ከማደበላለቅ ይልቅ የዐደባባይ በዓሎቻችንን ትክክለኛ ምንነትና ፋይዳ በአግባቡ በማስተዋወቅ÷ ቤተ ክርስቲያናችንም መንግሥትም የሚዲያ ተቋማቱም የጋራ ተጠቃሚ የሚኾኑበትን ዕድል መጨመር እንደሚቻል በጽሑፉ ተገልጧል፡፡

የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ቤተ ክርስቲያናችን የራሷ የጉዞ ወኪልና አስጎብኚ ቢሮ የምታደራጅበትን የቱሪዝም መመሪያ በማቋቋም ላይ መኾኑ ከቱሪዝም ሀብቷ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንድትኾን፣ ማንነቷን ለማስጠበቅና ተገቢውን አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማበርከት እንደሚያስችላት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Advertisements

4 thoughts on “ቤተ ክርስቲያናችን በኮፕት ቴሌቪዥን ዕለታዊ የአየር ሰዓት ልታገኝ ነው

 1. ግእዝ በመሥመር-ላይ January 29, 2013 at 3:45 pm Reply

  የተገኘውን ሰዓት የሚጠቀምበት ማን ነው? ረ ለመኾኑ ቤተ ክሲያኗ የቷ ናት፦ የሐዋርያትን ጉባኤ እየበተነ ያለው ሲኖዶስ ነው? ወይስ ቅን አገልጋዮችን በዐላውያን ፊት እየከሰሰ የሚያሳድደው ቤተ ክህነት? ረ ማን ነው?… መጀመሪያ የመቀመጫየን አለች አሉ…

 2. Anonymous January 29, 2013 at 7:19 pm Reply

  መጀመሪያ ይህንን ለመጠቀም ቅን የቤትክርስትያን አገልጋይ መሆንን ይጠይቃል ።ቤተክህነቱ እንደሆነ አይችልም ምክንያቱም ክርስቲያናዊ ጠባይ አየታይበትም የሌቦች የመናፈቃን እንዲሁም የካድሬ መደበቂያ መሆኑን አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው ።የግብፅ አባቶችም ይህንን አስተውለው ለተገቢው አካል መፍቀድ አለባቸው ።

  እግዚአብሔር ቤተክርስትያንን ይጠብቅ ።

 3. Anonymous January 30, 2013 at 2:01 pm Reply

  ቦ ጊዜ ለኩሉ! መቼም ሁሉንም በጊዜው ውብ ያደርገዋልና ሙያው ያላችሁ የቤተክስቲያን ልጆች ብቅ በሉ፡፡ ለአባቶቻችን ተገለጡላቸው፡፡ አልያ አፈ ጮሌዎቹ ሚዲያውን እንዳይነጠቁትና መርዝ መርጫ እንዳይሆን፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ግን በታቀደና የማስፈጸሚያ ስልት ባለው የሚዲያ ፖሊሲ እንዲመራ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት ሊያየውና ባለቤት ሊያበጅለት ይገባል፡፡ የቴለቪዥኑንም ሰዓት እንደ ሌሎቹ ሚዲዎች የሌሎች ስጋዊና ግለሰባዊ ሀሳቦች ማራመጃ እንዳይሆን ኃላፊነትና ተጠቂነት በአለበት መንገድ ሊደራጅ ያስፈልገዋል፡፡ ሚዲያ የአውደምህረት ጉባዔ ስላይደለ ልዩ ትኩረት ይሻል፡፡
  ቸር አማላክ ቸሩን በሚዲው ያሰማን፡፡

 4. Anonymous May 7, 2014 at 8:50 am Reply

  AMILAK YIMESGEN

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: