የብፁዕ አቡነ ናትናኤል የበዓለ ጥምቀት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ

ጥምቀት ማለት ጥሬ ቃሉ ሲተረጎም መጠመቅ፣ መዘፈቅ፣ መነከር፣ ከእግር እስከ ራስ ከውኃ መግባት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሀብቱን ለሰው ልጆች ከሚያድልባቸው ከምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንደኛውና የመጀመሪያው ምስጢረ ጥምቀት ነው፡፡

ጥምቀት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት የመጀመሪያው በር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ለመኾንና የክብሩ ወራሽ ለመኾን ወደ ክብሩ የሚወስደውና የሚያደርሰው መንገድ ጥምቀት ነው፡፡ ጥምቀት ከእግዚአብሔር በመንፈስ የምንወለድበት ምስጢር ነው፡፡

የክርስቶስ ጥምቀት

DSC_0086

ጉዞ ወደ ጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት

ክርስቶስ ከመጠመቁ በፊት በነቢያት አንደበት ‹‹የጠራ ውኃ አፈስባችኋለኹ፤ ከርኵሰታችኁም ሁሉ አነጻችኋለኹ›› /ሕዝ.36÷25/፤ ‹‹ኃጢአታቸውንም ሁሉ ወደ ጥልቁ ባሕር ትጥላለኽ›› /ሚል.7÷19/ ተብሎ ተነግሮለት ነበርና ይህን ትንቢት ለመፈጸም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፴ ዓመቱ(ዘመኑ) በዮርዳኖስ ለመጠመቅ በወደደ ጊዜ መጥምቁ ዮሐንስ ‹‹ከኔ በፊት የነበረ፣ ከኔም የሚበልጥ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል›› እያለ ይመሰክርለት ነበር፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዘመን ለሕዝቡ ተገልጦ እየታየ ከገሊላ ተነሥቶ ዮሐንስ ያስተምርበትና ያጠምቅበት ወደነበረው ወደ ዮርዳኖስ መጥቶ አጥምቀኝ አለው፡፡ ዮሐንስም ‹‹እኔ በአንተ እጠመቃለኹ እንጂ አንተ በእኔ እንዴት ትጠመቃለኽ፤ አይኾንም›› አለው፡፡ ጌታችንም ‹‹አንተ እኔን በማጥመቅ እኔም ባንተ እጅ በመጠመቅ የሰውን ሥራ እንፈጸም ዘንድ ይገባናልና አጥምቀኝ፤›› አለው /ዮሐ.3÷13/፡፡ ዮሐንስም መልሶ ‹‹ሌላውን ባንተ ስም አጠምቃለኹ፤ አንተን በማን ስም አጠምቃለኹ፤›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ጌታችንም መልሶ ‹‹ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ፤ ብርሃንን የምትገልጥ የቡሩክ የአብ ልጅ ሆይ÷ ይቅር በለን እያልኽ አጥምቀኝ›› በማለት መለሰለት፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜም (ሲጠመቅም) የዮርዳኖስ ውኃ በማለት ከሰው ይልቅ ፈጣሪዋን አከበረች/መዝ.113÷3/፡፡ አጥማቂው ዮሐንስም በጌታችን ራስ ላይ እጁን ዘርግቶ ውኃውን ሳይነካ ጌታን አጠመቀው፡፡ ጌታችንም ተጠምቆ ከውኃ ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ ታይቷል፡፡

አብም በደመና ኾኖ ‹‹የምወደው የምወልድው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ መስክሮለታል /ማቴ.3÷16 – 17/፡፡ ይህም ቀን ኤጲፋንያ ተብሏል፡፡ ይህም በግሪክ ቋንቋ ነው፡፡ በግእዝ አስተርእዮ ይባላል፤ ትርጉሙም መገለጥ፣ መታየት ማለት ነው፡፡

ክርስቶስ ለምን ተጠመቀ?

ይህ ጥያቄ የብዙ ሰዎች ጥያቄ እንደኾነ ይገመታል፤ ምክንያቱም ጥምቀት የሚያስፈልገው ከኃጢአት ለመንጻት የዘለዓለም ሕይወትን ለመውረስ ነው፡፡ ታድያ የክርስቶስ መጠመቅ ለምን አስፈለገ? እከብር አይል የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ከኃጢአት ልንጻ አይል እርሱ በባሕርዩ ንጹሕ ነው፡፡ ታድያ ለምንድንነው ሰማያዊው አምላክ በምድራዊው በዮሐንስ እጅ የተጠመቀው የሚለውን ጥያቄ ለምእመናን ለመመለስና የክርስቶስን የመጠመቅ ዓላማ ሁሉም እንዲያውቀው ከብዙ በጥቂቱ ዋና ዋና ነጥቦችን መግለጽ ያስፈልጋል፡፡

  1. ክርስቶስ የተጠመቀበት ምክንያት ለሰው ልጅ ልጅነትን ለመስጠት፤
  2. በጥንተ አብሶ (በውርስ ኃጢአት) የተያዙትን ነጻ ለማውጣት፤
  3. ሥላሴን ማለትም የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን ህልውና ለማስረዳትና እንደገናም በአካል ሦስት ቢኾንም በባሕርይ ተገናዝበው የሚኖሩ መኾናቸው ከዚህ በፊት ጎልቶ ስለማይታወቅ አንድነታቸውንና ሦስትነታቸውን ለማስረዳት፤
  4. ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ሰው የኾነ አካላዊ ቃል ወልድ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ መኾኑንና ሁለት ልደት እንዳለው ዓለም እንዲያውቅ ነው፡፡

ከላይ እንደተገለጸው ጌታችን የተጠመቀው ለሰው ልጅ ብሎ እንጂ ባይጠመቅ የሚቀርበት ኑሮ አይደለም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ የተጠመቀው ከላይ የተጠቀሱትን አራት ነጥቦች ለመፈጸም እንጅ ለክብር አይደለም፡፡ ለአዳምና ለዘሮቹ የተወሰደባቸውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፤ ምክንያቱም አዳም በሠራው ኃጢአት ከፈጣሪው ተለይቶ ነበር፤ ‹‹አዳም የዲያብሎስ ወንድ አገልጋይ ነው፤ ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ ናት›› የሚል የዕዳ ደብዳቤ ዲያብሎስ አስፈርሞ አንዱን በሲኦል፣ አንዱን በዮርዳኖስ ወንዝ አስቀምጦት ነበር፡፡ ‹‹ወሰጠጠ መጽሐፈ እዳነ›› እንዳለ ሊቁ በጥምቀቱ የዕዳ ደብዳቤአችንን ቀደደልን፤ አጠፋልን፡፡ በአጠቃላይ የክርስቶስ መጠመቅ የሰው ልጆችን ለማዳን ነው፡፡

የጥምቀት በዓል የምናከብርበት ምክንያት

DSC_0095

የማኅበረ ቅዱሳን የበገና ዘማርያን

በዚህ ቀን አይሁድ በዓለ መጸለትን ያከብሩበት ነበር፡፡ በበዓለ መጸለት ካህናተ ኦሪት ወንዝ ወርደው ድንኳን ተክለው ‹‹አባቶቻችንን ባሕር ከፍለኽ በደመና ጋርደኽ ያወጣኻቸው አንተ ነኽ፤›› እያሉ በዓሉን ያከብሩት ነበር /1ቆሮ.10÷1/፡፡

እንደዚሁም በዘመነ ሐዲስ በበዓለ መጸለት በዓለ ጥምቀት ተተክቷልና ካህናተ ወንጌል ወንዝ ወርደው ድንኳን ጥለው በክርስቶስ ጥምቀት ክርስቲያኖች ባሕረ ኃጢአትን መሻገራቸውን ያስቡበታል፡፡ የታቦቱ ወንዝ መውረድ ደግሞ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መውረድ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ መሄዱን የሚገልጽና የሚያስረዳ ነው፡፡ የጥምቀት በዓል አከባበር ይህን ይመስላል፡፡

 

ቃና ዘገሊላ

ቃና ከናዝሬት ሰባት ኪሎ ሜትር ርቆ በስተሰሜን በኩል የነበረ መንደር ነው፡፡ በዚህ መንደር ክርስቶስ ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ በሠርግ ታድሞ ነበር፡፡ በዚያም የመጀመሪያውን ተኣምር አደረገ፡፡ ዮሐ.2÷1፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ በቃና ዘገሊላ ታድመው ሳለ ሠርገኞች ወይን አለቀባቸው፡፡ ድንግል ማርያምም ይህን አይታ ጌታችንን፣ ልጄ ሆይ÷ ወይን የላቸውም አለችው፡፡ እርሱም አንቺ ሴት ካንቺ ጋራ ምን አለኝ፡፡ ድንግል ማርያም የልጇን በጎ ምላሽ ከሰማች በኋላ ለሚያስተናግዱት የሚላችኁን አድርጉ አለቻቸው፡፡ ጌታችንም ጋኖቹን ውኃ ሙሏቸው አለ፡፡

DSC_0017

የጥምቀት ልጆች በሥራ ላይ

ውኃ ሙሏቸው፤ ቅዱና ለአሳዳሪው ስጡት አለ፤ ሰጡት፡፡ አሳዳሪውም ቀምሶ አደነቀ፡፡ ጌታችንም ይህን ተኣምር ለመጀመሪያ ጊዜ በቃና አደረገ፡፡ በዚያን ጊዜ የእርሱ አምላክነት የድንግል ማርያም አማላጅነት ተገለጠ፡፡

አንድ አንድ ሰዎች ‹‹አንቺ ሴት ከኔ ምን አለሽ›› በማለት አዋርዷታል የሚሉት ጠላታችንን ሰይጣን እንዳያስተውሉ ልባቸውን ስለዘጋው እንጂ ወደው አይደለም፡፡ እንዲህማ ቢኾን ኑሮ ‹‹አባትኽንና እናትኽን አክብር›› ብሎ ሕግ ባልሠራም ነበር፡፡ አትሳቱ÷ እናቱንና አባቱን የሚያዋርድ፣ የሚያቃልል አምላክ የለንም፡፡ አንቺ ሴት ካንቺ ምን አለኝ ማለቱ ስድብ ሳይኾን ካንቺ ተወልጄ ሰው ኾኛለኁና አንቺ ጠይቀሽኝ የማላደርገው ምን አለ ማለቱ ነው፡፡ 9 ወር ከ5 ቀን የተሸከመችውን እናቱን ቀርቶ ለወዳጆቹ ቅዱሳን እንኳን ሰማይ እንዲለጉሙ፣ እሳት እንዲያወርዱ፣ ፀሐይ እንዲያቆሙ አድርጓል፡፡ 1ነገ. 17÷1፤ ኢያ. 10÷12፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ቢኾንማ ኑሮ የሚላችኹን አድርጉ ከማለት ይልቅ ልጄ÷ በሰው መሀል አቃለልኽኝ፤ አዋረድኽኝ ባለች ነበር፡፡

የቃና ዘገሊላ ማለትም ጥር 12 ቀን የምናከብረው በዓል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓል ነው፡፡ ለለመኑት የሚሰጥ ቸር አምላክ የለመነውን ይስጠን፤ በቸርነቱ ይጎብኘን፤ በዓሉን የደስታና የሰላም በዓል ያድርግልን፤ አሜን፡፡

                                                                                  አባ ናትናኤል

የአርሲ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: