የቅ/ሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ በከፍተኛ ጥበቃ ውስጥ ተጀምሯል

  • ‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› የሚሉ አባቶች በአቋም ተጠናክረዋል፤ በቁጥር ጨምረዋል

የዕርቀ ሰላም ንግግሩ ፍጻሜ ሳይታወቅ አንዳችም ተግባር መከናወን እንደማይገባው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ ተሳታፊዎች አሳሰቡ፡፡ ከቀን ወደ ቀን በአቋም እየተጠናከሩና በቁጥርም እየጨመሩ የመጡት እሊህ ብፁዓን አባቶች፣ የዕርቀ ሰላሙ ፍጻሜ ምንም ይኹን ምን ለሰላም ጉባኤው ቅድሚያ ሰጥቶ ውጤቱን መጠበቅ እንደሚገባና ለውጤቱም መሥራት እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተው መናገራቸው ታውቋል፡፡

የምርጫ አጀንዳውን በተመለከተ÷ ቤተ ክርስቲያናችን ባለፉት ፓትርያሪክ ዘመን ለኻያ ዓመታት ተቸግራ መኖሯን ያስታወሱት የምልአተ ጉባኤው አባላት÷ ‹‹ሌላ ኻያ ዓመት መቍሰል አይገባንም፤ ወደ ምርጫው የምንገባው በአንድነትና በተረጋጋ መንፈስ ለቤተ ክርስቲያን እረኛ የሚኾነውን አባት ለመምረጥ መኾን ይገባዋል›› ማለታቸውን ከዕለቱ የቅ/ሲኖዶሱ አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ውሎ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ዛሬ በተጀመረውና ከቀትር በፊት በነበረው የቅ/ሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ÷ የዳላሱን የሰላም ጉባኤና ተጓዳኝ ጉዳዮች የተመለከተ ሪፖርት በዕርቀ ሰላም ልኡካኑ አማካይነት ለምልአተ ጉባኤው ቀርቦ ተደምጧል፤ ከቀትር በኋላም በተለይም በሪፖርቱ በተመለከቱት የውሳኔ ሐሳቦች ላይ ግልጽ ተቃውሞ የሚያሰሙ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችንም ያካተተ ውይይት መጀመሩ ተዘግቧል፡፡

ውይይቱ ነገ ተሲዓት በኋላ (ከቅድሥት ሥላሴ ክብረ በዓል በኋላ ከቀኑ በ9፡00) ጀምሮ እንደሚቀጥል ከስብሰባው ምንጮች የተገለጸ ሲኾን ከመንበረ ፓትርያሪኩ ዋና መግቢያ በር ጀምሮ ሠራተኞችንና ለመግባት የሚፈቀድላቸውን ውስን ባለጉዳዮች ጨምሮ የተጠናከረ ጥበቃ በመደረግ ላይ መኾኑ ተገልጧል፡፡

በቀደሙት ዘገባዎቻችን ስናስነብብ እንደቆየነው÷ በምልአተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ጠረጴዛ ላይ ከፊት መሥመር የተቀመጠው አጀንዳ ‹‹ቅድሚያ ዕርቀ ሰላሙ›› የሚለው ቁምነገር ነው፡፡ የኻያ ዓመታትን ልዩነት አስወግዶ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት እንደሚያረጋግጥ ተስፋ በተጣለበት በዚህ ቁምነገር የተለያዩ የዕርቅ አማራጮች ቀርበውበታል፡፡ የመጀመሪያው÷ ዕርቀ ሰላሙ ተፈጽሞ (ውግዘቱ ተነሥቶ?) አራተኛው ፓትርያሪክ በሕይወት እስካሉ ድረስ ከሢመተ ፓትርያሪክ ታግሦ መንበረ ፕትርክናው በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ ብፁዓን አባቶች በጋራ በሚመርጡት እንደራሴ/ዐቃቤ መንበር እንዲጠበቅ ነው፡፡ ሁለተኛው÷ ዕርቀ ሰላሙ ተፈጽሞ አራተኛው ፓትርያሪክ መንበራቸውን በፈቃዳቸው ለቀው በአንድነት ወደ ስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ መቀጠል ነው፡፡ ሦስተኛው÷ ዕርቀ ሰላሙ ተፈጽሞ አራተኛው ፓትርያሪክ ወደ መንበራቸው ይመለሱ የሚለው አቋም ነው፡፡

ይኹንና በአራተኛው እና በአምስተኛው ፓትርያሪኮች ሢመተ ፕትርክና የሚነሡት ክርክሮች (በፓትርያሪክ ላይ ፓትርያሪክ መሾም) ተመሳሳይ መኾናቸውን፣ የዕርቅና ሰላም ሂደቱ የተጀመረው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በመንበረ ፕትርክናቸው እያሉ መኾኑን የሚጠቅሱ ወገኖች÷ ዕርቀ ሰላሙ ከፓትርያሪክ ምርጫው ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለውና ሊኖረው እንደማይገባ ይከራከራሉ፡፡ ሁለቱም ‹‹በተጓዳኝ ሊካሄዱ ይችላሉ›› በሚለው አቋማቸው ‹‹በጋራ በሚመረጥ እንደራሴ/ዐቃቤ መንበር መቆየት›› የሚለውን አማራጭ/አቋም በከፍተኛ ደረጃ ለመሞገት ተዘጋጅተዋል፡፡

በእነርሱ እምነት ‹‹ወደ መንበር መመለስ›› የሚባለው አቋም/አማራጭ ‹‹ታሪክ የሚያፋልስ በመኾኑ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡›› ‹‹እኛ የምንይዘው አራተኛው ፓትርያሪክ ጽፈው ያስገቡትን ደብዳቤ ነው›› የሚሉት እሊህ ወገኖች በአቡነ መርቆሬዎስ ላይ የመንግሥት ጫና እንደነበር ቢያምኑም በአቶ ታምራት ላይኔ ተጽፏል ለሚባለው ደብዳቤ ዕውቅና አይሰጡም፡፡ ከእርሱ ይልቅ አቡነ መርቆሬዎስ መንበሩን እንደሚለቁ አሳውቀው ሲያበቁ ኋላ ላይ በአንዳንድ አባቶች ምክር በተለወጠው አቋማቸው ወደ መንበራቸው እንዳይመለሱ የተደረጉት ዐቃቤ መንበር በነበሩት ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ‹ፈጣን ርምጃ› ምክንያት እንደነበር በማስታወስ ‹‹አውራጅም ወራጅም አንድጋ ናቸው›› በማለት ይሣለቃሉ፡፡

በመኾኑም ‹‹ወደ መንበር መመለስ፣ በእንደራሴ መቆየት የሚባል ነገር አይኖርም፤ ወደ አገር ተመልሰው በጡረታ ደንብ እንዲኖሩ እንስማማለን፤ ቡራኬ መስጠት ይችላሉ፤ ስማቸውን በቅዳሴ ለመጥራት እንፈቅዳለን፤ ከሚመረጡት ፓትርያሪክ አጠገብም ሊቀመጡ ይችላሉ፤ ተበድያለኹ ካሉ በራሳቸው ድምፅ ገጽ ለገጽ እንነጋገር፤ ቅዱስነታቸውን ተከትለው ከአገር የወጡቱም ይኹን በቅዱስነታቸው አንብሮተ እድ የተሾሙት አብረውን ሊመርጡ፣ ሊመረጡ፣ በሥራ ሊመደቡ፣ በቅ/ሲኖዶሱ ሊሰበሰቡ፣ ሐሳብ ሊሰጡና ሊወስኑ ይችላሉ፤›› ይላሉ፡፡

ይህም ኾኖ ለቤተ ክህነቱ በተመደቡ ደኅንነቶች የሚደረገው ውተወታና ጫና ቢጠናከርም ዛሬ በተጀመረው የምልአተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብስባ ‹‹ቅድሚያ ለዕርቀ ሰላሙ›› የሚሉ አባቶች በአቋም መጠናከራቸው፣ በብዛትም የበላይነት መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ እንደ ብፁዕ አቡነ ዳንኤልና እንደ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ያሉ አባቶች የሚወተውቷቸውን ወትዋቾች ‹‹ለመንግሥትም ለቤተ ክርስቲያንም የማትጠቅሙ›› በሚል እስከመገሠጽና እስከማባረር መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: