ሰበር ዜና – በውጭ ለሚገኙት ብፁዓን አባቶች ጥሪ ተደርጎ ምርጫው እንዲካሄድ ተወሰነ

አርእስተ ጉዳይ፡-

  • የዕርቀ ሰላሙ ሂደት ከፓትርያሪክ ምርጫው ጎን ለጎን ይቀጥል ተብሏል
  • በውሳኔው ያልተስማሙት የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ስብሰባውን ጥለው ወጡ!
  • የዐቃቤ መንበሩ አቋም በዕርቀ ሰላም እና ምርጫ መካከል ሲዋዥቅ ውሏል
  • ዐቃቤ መንበሩ ለምርጫው በቶሎ መፈጸም የፌዴራል ጉዳዮች ሚ/ርን እገዛ ጠይቀዋል
  • መንግሥት አስቸኳይ ስብሰባው በቶሎ እንዲፈጸም ይሻል
  • የምልአተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ነገ ያበቃል፤ ጋዜጣዊ መግለጫም ይሰጣል

በከፍተኛ ጥበቃ ሥር የተከናወነው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ በውጥረት ተጀምሮ በውጥረት ለመጠናቀቅ ተቃርቧል፡፡ በስብሰባው ዋዜማ ባስነበብነው ዘገባ እንደተመለከተው÷ የፓትርያሪክ ምርጫው እና ዕርቀ ሰላሙ በተጓዳኝ እንዲካሄድ፣ ለምርጫው በሚደረግ ዝግጅትም በውጭ ለሚገኙት ብፁዓን አባቶች በሙሉ ጥሪ እንዲደረግላቸው ከፍተኛ ውዝግብ ከታየበት የምልአተ ጉባኤው ውሎ በኋላ ውሳኔ ላይ የተደረሰ መስሏል፡፡

His Grace Abune Natnael

ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል

የስብሰባው ርእሰ መንበር ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል÷ በአንድ በኩል፣ ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ ጀምሮ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች÷ የምርጫውን ሂደት በአግባቡ እንዳያከናውኑና በሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ዕንቅፋት እየፈጠሩባቸው መኾኑን በመግለጽ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ የጠየቁ ሲኾን በሌላ በኩል ደግሞ በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ላይ በዐቃቤ መንበርነታቸው የመቆየትና ከምርጫው በፊት የዕርቀ ሰላሙን ፍጻሜ የመጠበቅ ዝንባሌ በሚያሳዩ አቋሞች መካከል ሲዋዥቁ መዋላቸው ተገልጧል፡፡

‹‹የዕርቀ ሰላሙን ፍጻሜ ታግሠን የፓትርያሪክ ምርጫውን በውጭ ከሚገኙት አባቶች ጋራ በአንድነት እናካሂድ›› በሚለው አቋማቸው የጸኑት የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ስብሰባውን ትተው መውጣታቸው ተዘግቧል፡፡ እንደ አንዳንድ ምንጮች ጥቆማ

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል

የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል

ከኾነ ዋና ጸሐፊው ስብሰባውን ትተው በሚወጡበት ወቅት የልዩነት አቋማቸውን ለብዙኀን መገናኛ ይፋ እንደሚያደርጉ በግልጽ ተናግረዋል/ዝተዋል ተብሏል፡፡

ስብሰባው በነገው ዕለት ረፋድ ላይ መግለጫ በመስጠት እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል፡፡ ስለ ስብሰባው ለብዙኀን መገናኛ የሚሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲያዘጋጁ ሦስት ብፁዓን አባቶች ማለትም ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተመድበዋል፡፡

በውጭ ከሚገኙትና በዚህ ስብሰባ ላይ እንደሚካፈሉ ተጠብቀው ከነበሩት ዐሥር ያህል ብፁዓን አባቶች ስድስቱ (ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘኢየሩሳሌም፣ ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ – የካሪቢያን፣ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ፣ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የደቡብ አፍሪካ፣ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የኒውዮርክ እና ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ) ከአገር ውስጥም እንደ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ እና ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ያሉት አባቶች አለመገኘታቸው ታውቋል፡፡

ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የሚበጅ በመኾኑ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንዲሰጥ ከሚሰማው የአገልጋዮችና ምእመናን ተማኅፅኖ፣ ይህም በአብዛኞቹ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ተደግፎ ሳለ÷ የዕርቀ ሰላም ሂደቱ እንዲቀጥል የምርጫውም ዝግጅት እንዲጀመር፣ ለዚህም በውጭ ለሚገኙት አባቶች ጥሪ እንዲተላለፍ ቅ/ሲኖዶስ መወሰኑ በርካታ ጥያቄዎችን ያለመልስ የሚተው፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ሰላምና አንድነት ለከፋ የመከፋፈል አደጋ የሚዳርግ ነው፡፡

ወዲያውም ደግሞ ከዋና ሥ/አስኪያጁ ለአስመራጭ ኮሚቴው አባላት የተጻፈው ደብዳቤ አስመራጮቹ ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም በቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት ተገኝተው ሥራቸውን እንዲጀምሩ ያሳስባል፡፡ ማሳሰቢያውን በመቀበልና ባለመቀበል በያዟቸው አቋሞችና ውልውሎች የተመናመኑትና የሚዋልሉት የኮሚቴው አባላት የምልአተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ በሚያበቃበት ነገ ጥር 8 ቀን በቁጥራቸው ተሟልተው ሥራቸውን ይጀምሩ ይኾን?

ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ

Advertisements

One thought on “ሰበር ዜና – በውጭ ለሚገኙት ብፁዓን አባቶች ጥሪ ተደርጎ ምርጫው እንዲካሄድ ተወሰነ

  1. Daniel January 16, 2013 at 1:45 am Reply

    I found this very interesting comment on Dejeselam and i send it share with you. በአባቶችና በምእመናን መካከል ያለው ግንኙነት በእኛና በፖለቲከኞቻችን ካለው ግኑኝነት መለየት ያስፈልገናል። አባቶችን “እንዲህስ ቢሆን ምን ይመስላችኋል?” ማለት ያባት ነው፤ “4ኛው ፓትሪያርክ ቢመለሱ ደስ ይለናል” ማለት መልካም ነው። መማጸን፤ መለመን፤ ማሳሰብ ተገቢ ነው። ካልሆነ ባልተገራ አንደበት እንደወረደ መልቀቅ መቆም አለበት ። ምእመናን የመጨረሻ ውሳኔ ለአባቶች ትተን በፀሎት ማገዝ ነው ያለብን። ሲጀመር ነገር ሲኖዶሱን ማመን ያስፈልጋል። አባቶቻችን ለመንግስት፤ ለዚህም ለዛም ቡዱን ተፅእኖ የሚገዙ፤ የራሳቸው አቋም የሌላቸው ተደርገው እንዲሳሉ ባንዳንድ ወገኖች የሚደረገው ስም ማጥፋት መቆም አለበት። አባቶቻችን መታመን ፤መከበር አለባቸው። ከነምሳሌው “ባለቤቱ ያቀለለው አሞሌ…” ነውና። የአባቶችን እርቅ በሚመለከት በመጀመሪያ ግንዛቤ ለወሰድባቸው የሚገቡ ነገሮች ያሉ ይመስለኛል። ቤተ ክርስቲያን ለሁለት አልተከፈለችም። አሁንም ቤተ ክርስቲያን አንድ ነች። አርባ ሚልዮን የሚሆን ምእመን ካላት ቤተ/ክ የተወሰኑ፤ በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆችዋ ባስተዳደር ለጊዜው በመለየታቸው ምክንያት ቤተ/ክ ለሁለት ተከፍላለች ልንል አያስኬድም። አለማዊ ንፅፅርም ከወሰድን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ቤተሰብነት ተለየች ነው እምንለው እንጂ ኢትዮጵያ ለሁለት ተከፈለች አንልም። ይህ ልዩነት ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ ቆይቶ ወይም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማ ሊቃውንቱ መስማማት አቅቶአቸው የመጣ መለያየትም የለም። ፖለቲካና ወንዘኝነት የፈጠሩት ችግር ነው። በመሰረቱ የተለያዩት አባቶች እንጂ ምእመኑም አይደለም። በውጭ ያለው ምእመን በሦስቱም እንዳመቸው ሲገለገል ነው እሚገኘው ። አብዛኛው ካህንም እንዲሁ። እንዲያውም የሚሳለመው ቤተ/ክ ገለልተኛ ይሁን ስደተኛ የማያቅ አሊያም ግድ እማይሰጠው ምእመን ቁጥሩ የትዬለሌ ነው። ዋናው የእርቁ አላማና መንፈስ መሆን ያንድ አዛውንት አባት ወደ መንበሩ መመለሳቸው ሳይሆን ከግንዱ የተለዩትን ወደ ቀደመ ቦታቸው መመለስ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ያገር ቤት አባቶች በተደጋጋሚ እዚህ ድረስ በመምጣት ለእርቅና ለቤተ/ክ አንድነት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ያገር ቤት አባቶች ፤የውጭ አባቶች ከኢትዮጵያ የተለየ ሲኖዶስ ማቋቋማቸው፤ ጳጳሳት መሾማቸው በጽኑ ሲቃወሙት ነበር፤ ተወጋግዘዋልም። ነገር ግን ለሰላም ዋጋ መክፈል አስፈላጊ ስለሆነ ይሄን ችላ ብለው የውጭ አባቶችን “ኑ ሁሉን ነገር ለግዜር ይቅር ብለን አብረን አንድ ሲኖዶስ ሆነን ፓትሪያርክ እንምረጥ” እያሉ ነው። ታዲያ የውጭ አባቶችም በበኩላቸው “4ኛው ፓትሪያርክ ወደ መንበራቸው ይመለሱ” የሚለውን አቋም በመተው ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል። የአቋም ሽግሽግ በሌለበት ሁናቴ እርቅ የሚታሰብ አይሆንም። የጎጡን ሳይሆን የአገሩንና የቤተ ክርስቲያኑን ጥቅም እሚያስቀድም ሁሉ በዚህ የቬኦኤ እንተርቪው በድምጣቸው የለየኋቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ያሉትን ልብ ብሎ ማስተዋል አለበት። አገራችን ውስጥ ያለውን የተበላሸውን ሁሉ ለመለወጥ ለማሻሻል ጠንክረን መታገል አለብን እንጂ ቤተ/ክ ለትርፍ የተቋቋመች ካምፓኒ ትመስል እዚህ እማታሰሩን ከሆነ ውጭ ወስደን እንተክላታለን ሊባል አይገባም። ቤተ/ክ outsourcing አይመለከታትም። ምእመናን በበኩላችን ለቤተ ክርስቲያኑ የሚበጀው ምንድን ነው ብለን ማጤንና ለኢትዮጵያዊ ባህላችን በሚመጥን ቋንቋ ሃሳባችን ማቅረብ እንችላለን ። በርግጥ የማንኛውም ወገን የመፍትሄ ሃሳብ ከፖለቲካዊና የወንዜ ልጅነት እድፍ የፀዳ መሆን ይኖርበታል። ነገር ግን የመጨረሻው ውሳኔ የሲኖዶሱ መሆኑ መቀበል ያስፈልጋል። ሲኖዶስ አቡነ መርቆሬዎስን ወደ መንበሩ እንዲመለሱ በስደተኛ አባቶች የቀረበውን ሃሳብ ቢስማማበት እሰየው ነበር። ነገር ግን የለም “ለቤተ ክርስቲያኑ የሚበጀው የሁለቱ ሲኖዶስ መዋሃድና በጋር ሆኖ ምርጫ ማካሄድ ነው” ካለ- ሁሉም ወገን ያስደስት አያስደስት ሌላ ጉዳይ ሆኖ እንደ ቤት ከርስቲያን ልጅነታችን ያንኑ መቀበል ተገቢ ነው። ካልሆነ ያገር ቤቱ ሲኖዶስ የሚወስነው ውሳኔ የእኛን አመለካከት የሚደግፍ ሆኖ ሲገኝ ልናሞግሰው ሳይሆን ሲቀር ደግሞ “የመንግስት እጅ አለበት” የምትል ካርድ ልንመዝባቸው አይገባም። የውጭም አባቶች እኮ በዚሁ መንገድ ከሄድን ከወቀሳ ነፃ አይደሉም። የአገር ቤቱ ሲኖዶስ ከመተቸት የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች ካለበት ሁናቴ ጋራ አገናዝቦ መረዳት ያስፈልጋል። የውሳኔው ሚዛናዊነት እንደየአመለካከቱ ሊለያይ ይችላል። ትልቁ ነጥብ በውጭ ላለው ሲኖዶስ እውቅና መስጠት ነው። ይህ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሲባል ያገር ቢቱ ሲኖዶስ የዘረጋው የሰላም እጅ እንደ ዋዛ ማየት የለብንም። የፓትሪያርኩ ወደ መንበሩ መመለስ “ቢሆን ጥሩ” ከማለት ውጭ የእርቁ የማእዝን ድንጋይ ሊሆን አይገባውም። እርቅ በመሰረቱ ያንድ ወገን ፍላጎት ማስፈፀሚያ አይደለም-የጋራ አካፋይ ፍለጋ እንጂ። የጋራ አካፋዩም የሁለቱ ሲኖዶሶች ውህደት ነው። የፓትሪያርክ ወደ መንበሩ መመለስ ያለፈውን ስህተት የማረም ጉዳይ ነው ከተባለም ያለፈውን ምእራፍ መዝጋት ያለብን አንዱን ወገን ጥፋተኛ ሌላው ትክክል በማድረግ ሳይሆን እንደ ትላንቱ አባቶቻችን “የሞትንም እኛ የገደልንም እኛ” በሚል መንፈስ ሊሆን ይገባዋል። ፓትሪያርኩን በመመለስ ብቻ ነው ያለፈውን ስህተት ማረም የሚቻለው ማለት ለቤተ/ክ አለማሰብ ነው። ይህ ስህተትን በማረም ላይ ሳይሆን በድል አድራጊነት አሸንፎ የመውጣት ስሜትን ያሳያል። በሁሉም አባቶች ለተፈፀሙ ስህተቶች የተወሰነውን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አይሆንም። ለማጠቃለል አሁን ቤተ ክርስቲያናችን ከተጋረጠባት ፈተና አንጻር ትልቁ ነገር የአባታችን ያቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበሩ የመመለስ ጉዳይ ሳይሆን፤ በውስጥና በውጭ፤ በቆላና በደጋ ያለው ህዝበ ከርስቲያን አንድ የመሆንና ባጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከገባችበት ቀውስ የሚያወጣት፤ ለማንኛውም አይነት የፖለቲካ ተፅእኖ እማይንበረከክና፤ ታላቅ መንፈሳዊ ጉልበት( Charismatic power) ያለው አንድ ኢትዮጵያዊ ሺኖዳ እማግኘትዋ ላይ ነው። ልብ እንበል! የመንግስት ተፅኖ ለምን ይኖራል ከማለት ለምን ለተፅእኖ እማይንበረከክ እረኛ አባት አጣን ብለን እንጠይቅ። ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: