በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ለማቋቋም ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው

 • የሚደራጀው የቱሪዝም መምሪያ አጎብኚውንና የጉዞ ወኪሉን ያስተባብራል
 • በግል አስጎብኚዎች የሚዘጋጀውን የኢየሩሳሌም ጉዞ በሓላፊነት ይመራል
 • በቱሪዝም ዘርፍ የቤተ ክርስቲያንን ፋይናንሳዊ አቅም ለማጠናከር ታቅዷል
 • ጥናቱ በኢየሩሳሌም ጉብኝት ባደረገው የልኡካን ቡድን እየተካሄደ ነው
 • የቡድኑ የኢየሩሳሌም ጉብኝት አቡነ ማቲያስን ለፕትርክና ለማግባባት እንደ ኾነ ተደርጎ መዘገቡን የልኡካኑ አባላት አስተባብለዋል

የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሀገር ውስጥና በውጭ አህጉረ ስብከት በተለይም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያሉ ገዳማትንና የቤተ ክርስቲያኒቱን የቱሪስት መስሕቦች የሚያስተዋውቅ የቱሪዝም መምሪያ ለመመሥረት በዝግጅት ላይ መኾኑን አስታወቀ፡፡ በመምሪያው ሥር መምሪያው የሚያስተባብረው አስጎብኚ ድርጅት እና የጉዞ ወኪል ለማቋቋም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ጥናት ለቅዱስ ሲኖዶስ መቅረቡ ተመልክቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያን አስጎብኚ ድርጅትና የጉዞ ወኪል በማእከል ማደራጀቷ÷ ወደተለያዩ ቅዱሳት መካናት የሚደረጉ የምእመናን ጉዞዎችን በባለቤትነት ይዛ ትምህርተ ሃይማኖቷን፣ ሥርዐተ እምነቷንና ክርስቲያናዊ ትውፊቷን በሚያስጠብቅ አኳኋን በሓላፊነት ለመምራት፣ በተሳላሚነት ስም የሚፈጸመውን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በመቆጣጠር ተመጣጣኝ ዋጋ እና በቂ ዋስትና ያለው አገልግሎት ለመስጠት፣ በአገልግሎቱ ከሚሰበሰበው ከፍተኛ ገቢ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ለማጠናከርና ለማስፋፋት የሚያስችል ፋይናንሳዊ አቅም ለማዳበር እንደሚያስችላት ተገልጧል፡፡

በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የውጭ ግንኙነት መምሪያ ለሚዲያ አካላት ባሰራጨው መግለጫው÷ ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የምትሰጥባቸው ጥንታዊና ታሪካዊ ሀብቶቿ ከሚያስገኙት የቱሪዝም ገቢ የበይ ተመልካች ኾና በመቆየቷ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተቋማዊ አቅሟን ለማጠናከር መሥራት የምትችልበት ጊዜው አሁን እንደኾነ አስታውቋል፡፡ በዋናው መሥሪያ ቤት ለማቋቋም በታቀደው የቱሪዝም መምሪያ የአስጎብኚ እና የጉዞ ወኪል ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ጥናት የተደረገ ሲኾን ጥናቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መኾኑን መምሪያው በመግለጫው ላይ አመልክቷል፡፡

የቅድመ ዝግጅት ጥናቱ በዋናነት የተደረገው ቤተ ክርስቲያናችን የቅዱሳት መካናት ይዞታ ካላቸው አገሮች ቀደምት ባለርስት በኾነችበት በእስራኤል – ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የቅድስት ሀገር ይዞታዋን እንደ አንድ ሀ/ስብከት አደራጅታና አንድ ሊቀ ጳጳስ መድባ ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዙትን ምእመናን አቅሟ በፈቀደ መጠን ስታስተናግድና ተልእኮዋን ስትፈጽም መኖሯን ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ አንጋፋው የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት ተመሥርቶ በድርጅቱ አማካይነት ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዙ ምእመናን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ድርጅቱ ለሚያጓጉዛቸው ምእመናን በድርጅቱ ፈቃድና ወጭ አንድ አንድ ቡራኬ ሰጪ አባት በመላክና ተጓዦች ምእመናን በጸሎት በመሸኘት ተወስና ቆይታለች፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የግል አስጎብኚዎቹ ቁጥር (በሰሞኑ የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ አገላለጽ ‹‹በኢየሩሳሌም ታሪካውያን ስፍራዎች ቁጥር ልክ››) እየበዛ መጥቷል፡፡ የዚያኑ ያህል በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ዐይነቱ ‹‹ቀራንዮ አስጎበኚና የጉዞ ወኪል›› በተሳላሚዎች ስም የሚጓዙ ግለሰቦች ሕገ ወጥ ዝውውር የሚያካሂዱበት መኾኑ መንፈሳዊ በረከትን ከማግኘት ጎን ለጎን ለቅዱሳት መካናት ይዞታችን የምእመኑ አለኝታነት የሚረጋገጥበት የእውነተኛ ተሳላሚዎች ጉዞ እንዳይደናቀፍ ስጋት አሳድሯል፡፡ ለዚህም ሲባል የተሳላሚዎችን ዕድሜና የዋስትና ማስያዣዎችን መሠረት ያደረገ የጉዞ መስፈርት የሚዘጋጅበት ኹኔታ ለዳሰሳ ጥናት ወደ ኢየሩሳሌም አምርቶ የነበረው ልኡክ ስለ ጥናቱ ለቅ/ሲኖዶስ ባቀረበው አጭር መግለጫ ላይ በመፍትሔ ሐሳብነት ቀርቦ ተመልክቷል፡፡

በግል የተቋቋሙትን የቅድስት ሀገር አስጎብኚ ድርጅቶች በአንድ ማእከል ማስተባበር የቤተ ክርስቲያናችንን የገቢ ምንጭ ለማዳበር፣ ለተሳላሚ ምእመናን ክፍያ ለመቀነስና በጉዞ ላይ ለሚደርሰው ችግር ሁሉ በቂ ዋስትና ለመስጠት የተሻለ አማራጭ ኾኖ ተወስዷል፡፡ የቱሪዝም ማእከሉ ጠቀሜታ ለኢየሩሳሌም ብቻ ሳይኾን የቱሪስት መናኸርያና ‹የወፍ አዕላፉ› ሁሉ መጠቀሚያ የኾኑትን በጣና ሐይቅ ዙሪያ የሚገኙትን ገዳማት፣ የአኵስምንና የላሊበላን ታሪካውያን ስፍራዎችና የመሳሰሉትን ‹‹በቁጥጥር ሥር ለማዋልና ለመዳኘት›› ያስችላል ተብሎ እንደሚታመን ተገልጧል፡፡

በቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የተመራው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች የሚገኙበት የልኡካን ቡድን ከኅዳር 14 – 22 ቀን 2005 ዓ.ም የዳሰሳ ጥናቱ በተጀመረበት በኢየሩሳሌም ተገኝቶ ከገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስና ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ ተገናኝቶ ተወያይቷል፡፡ የልኡካኑን የሥራ ጉብኝት በማስተባበር የዳሰሳ ጥናቱን ካቀረቡት መካከል የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊው መምህር ሰሎሞን ቶልቻ እንደገለጹት÷ ከሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ጋራ በቱሪዝሙ ሀብቶቻችን ላይ ያተኰረና ለሁለት ሰዓት የዘለቀ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

ከዚህም ባሻገር ከገዳሙ ማኅበር ጋራ በገዳሙ ዋና መጋቢ አማካይነት ቤተ ክርስቲያናችን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስለምትከፍተው የቱሪዝም መምሪያ ምክክር ተደርጓል፡፡ የልኡካኑ ውይይት በእስራኤል የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የኾኑ አካላትንም ያካተተ እንደነበር መ/ር ሰሎሞን ቶልቻ ተናግረዋል፡፡

ከብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በተጨማሪ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንን በሚመለከት ሌላ የሥራ ጉብኝት በኢየሩሳሌም የነበሩት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከብፁዕ ዋና ጸሐፊው ጋራ አይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎችን ማነጋገራቸው ተዘግቧል፡፡ ንግግሩ ቤተ ክርስቲያናችን በስታተስኮው ምክንያት የባለይዞታነት መብቷ ሳይከብር፣ ገዳማቷን ለማስፋፋትና ለማደስ ሳትችል ለዘመናት ተጨቁና በኖረችበት ኹኔታ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጧል፡፡ አይሁዳውያኑ የሃይማኖት አባቶች በዚህ ረገድ ከቤተ ክርስቲያን ጋራ አብሮ ለመሥራት፣ ግንኙነቱን ለማጠናከርና ለማስፋፋትም የጋራ (የትብብር) ኮሚቴ ለማቋቋምና የጉብኝት ልውውጥ ለማድረግ በሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጧል፡፡

ቡድኑ ወደ ኢየሩሳሌም ከማምራቱ አስቀድሞ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ም/ዋና ሥራ አስኪያጅና ከልኡካኑ አንዱ በኾኑት አቶ ተስፋዬ ውብሸት መሪነት በኢትዮጵያ የእስራኤል መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ከኾኑት ወ/ሮ በላይነሽ ዛቫድያን ጋራ ውይይት መደረጉን ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ አስታውቀዋል፤ በውይይቱም አምባሳደሯ ቤተ ክርስቲያን በቱሪዝም ኢንዱስትሪው በምታከናውናቸው ተግባራት መንግሥታቸው አብሮ ለመሥራት ያለውን በጎ ፈቃድ መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡

በማእከል በሚቋቋመው የቱሪዝም መምሪያ አማካይነት በልደተ ክርስቶስ እና በትንሣኤ በዓላት ምእመናን ወደ ኢየሩሳሌም ለሚያደርጉት ጉዞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብሮ እንዲሠራ ቤተ ክርስቲያኒቱ መጠየቋን የመምሪያ ሓላፊው አስረድተዋል፤ በውጤቱም ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው የቱሪዝም እንቅስቃሴ አየር መንገዱ በሚበርባቸው ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻዎች ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችንን የቱሪስት መዳረሻዎች በማስተዋወቅ አብሮ እንደሚሠራ መግለጹ ታውቋል፡፡

የቱሪዝም መምሪያንና በሥሩም አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ማቋቋሙ በቀድሞው ፓትርያሪክ ዘመን የተወጠነ እንደነበር የገለጹት መ/ር ሰሎሞን÷ ውጥኑን የሚያብራራ ባለ12 ገጽ የጥናት ምክረ ሐሳብ በጥቅምት ወር ለቋሚ ቅዱስ ሲኖዶሱ ቀርቦ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት፣ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊው አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ እንዲሁም የውጭ ግንኙነት መመሪያ ሓላፊው መ/ር ሰሎሞን ቶልቻ (የጥናቱ ምክረ ሐሳብ በቀረበበት ወቅት የገዳማት መምሪያ ሓላፊ ነበሩ) የተካተቱበትና በብፁዕ ዋና ጸሐፊው የተመራው የልኡካን ቡድን በኅዳር ወር አጋማሽ ወደ ኢየሩሳሌም ያመራውም በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ እና በብፁዕ ዋና ጸሐፊው ፈቃድ ለገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ እንዲሁም ለመንግሥት አካል በተጻፉት የድጋፍ ደብዳቤዎች እንደነበር ተረጋግጧል፡፡

እውነታው ይኸው ኾኖ ሳለ በአንዳንድ የጡመራ መድረኮችና ከጡመራ መድረኮቹ ገልብጠው በአገር ቤት ጽሑፎቻቸውን ባተሙ መጽሔቶች ላይ የልኡካን ቡድኑ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገው ጉዞ ዓላማ÷ ብፁዕ አቡነ ማቲያስን ‹‹ለስድስተኛ ፓትርያሪክነት ሢመት ለማግባባት›› እንደነበር መዘገቡ ‹‹ከእውነት የራቀ፣ የጉዞውን ዓላማም ይኹን ደረጃ እንደማይመጥን በሁሉም ዘንድ ሊታወቅ እንደሚገባው›› በመግለጽ የልኡካን ቡድኑ አባላት ዘገባውን አስተባብለዋል፡፡ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ በተፈቀደው የልኡካን ቡድኑ የሥራ ጉብኝት መርሐ ግብር ውስጥ የተባለው ዘገባ እውነትነት እንደሌለው መገለጹ አንድ ነገር ኾኖ÷ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ግን ስድስተኛው ፓትርያሪክ እንዲኾኑ የመንግሥትንና አንዳንድ የቅ/ሲኖዶሱን አባላት ድጋፍ ማግኘታቸው ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

 

 

 

                                 በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ መሪነት ወደ እስራኤል የተጓዘው ልኡክ

ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረበ አጭር የጉዞ መግለጫ

ቤተ ክርስቲያን በዋናነት በያዘችው ሐዋርያዊ ተልእኮዋ የሰው ልጆችን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲገቡና የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ለማድረግ ትተጋለች፡፡ ከዚህ የዕለት ከዕለት አገልግሎትዋ በተጨማሪ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ቀዳሚ በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት እየሠራች ትገኛለች፡፡ ይኹን እንጂ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ አልሠራችም፤ ተጠቃሚም አይደለችም፡፡ በአንጻሩ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ መንግሥታዊ እና የግል ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኗ ስም በሚያገኙት የቱሪዝም ገቢ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ኾነዋል፡፡

ከአገራችን ተጠቃሽ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አብዛኛውን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች በአደራ እና በባለቤትነት ይዛና ጠብቃ የምታገለግለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይኹን እንጂ ከዚህ አትራፊና ምንም ወጪ ከሌለበት ኢንዱስትሪ የበይ ተመልካች ከመኾን በቀር የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ አልኾነችም፡፡ ይህ ዐይነቱ አሠራር እየቀጠለ ከሄደ በገንዘብ ደረጃ ከምታጣው ጥቅም በላይ ቀኖናዋን፣ ትውፊቷንና አስተምህሮዋን እየሸረሸረ መሄዱ ስለማይቀር ቅዱስ ሲኖዶስ የቱሪዝምን ጠቀሜታና አስፈላጊነት ተመልክቶ፣ ከዚህ ቀደም ለቱሪዝሙ ከተሰጠው ትኩረት በላይ አጽንዖት ሰጥቶ ውሳኔ ሊያሳልፍበት፣ መመሪያ ሊሰጥበት ይገባል፡፡ ለዚህም መነሻ ይኾን ዘንድ የጥናት ዳሰሳ አስፈልጓል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በጥንታዊነቷ፣ በረዥም ዘመን አገልግሎቷ፣ በውስጧ በያዘቻቸው በርካታ ቅርሶችና የቅድስና ሥፍራዎች ከማንኛውም አካል በፊት ከኢንዱስትሪው ተጠቃሚ ትኾን ዘንድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የቱሪዝም መምሪያ በቤተ ክርስቲያናችን በዋናው መ/ቤት በኩል ቢከፈት የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊትና ክብር ከማስጠበቁም በላይ ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለአገራችን ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የላቀ ነው፡፡ ይህም፡-

 • ዘርፉ በሚያስገኘው ከፍተኛ ገቢ ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎቷን ታጠናክራለች፡፡
 • ቤተ ክርስቲያናችን በራሷ የቱሪዝም ክፍል አገልግሎት እየሰጠች እምነቷን፣ ሥርዐቷንና የአበውን አስተምህሮ ትጠብቃለች፤ ታስጠብቃለች፡፡
 • ለበርካታ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
 • ሕጋዊና ዘመናዊ አሠራርን በማጠናከር አገራዊ የልማት ተሳትፎዋን ያጎላዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስፖንሰር አድራጊነት ከኅዳር 14 – 22 ቀን 2005 ዓ.ም ወደ እስራኤል የተጓዘውና በቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የተመራው ልኡክ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ያላትን ተሳትፎ የሚያጠናክር ጥናታዊ ዳሰሳ አካሂዷል፤ ጥናታዊ ዳሰሳውን በተመለከተም ልኡኩ ለቅ/ሲኖዶስ መግለጫ አቅርቧል፡፡

ቅ/ሲኖዶስ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ ሰብሰባዎች በቱሪዝም ጉዳይ ውሳኔዎች ቢያሳልፍም ውሳኔው ተግባራዊ አልኾነም፡፡ አሁን ግን በቱሪዝሙ ዘርፍ ባለድርሻ ከኾኑት አካላት፡-

 • ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር
 • ከኢትዮጵያ አየር መንገድ
 • ከእስራኤል ኤምባሲ

እንዲሁም ከሌሎች በዘርፉ ግንኙነት ካላቸው አካላት ጋር በተደረገ ምክክር የቤተ ክርስቲያናችንን ራእይ በመደገፍ በቱሪዝሙ አብሮ ለመሥራት ከፍተኛ በጎ ፈቃድ ተገኝቷል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው የቱሪዝም እንቅስቃሴ አየር መንገዱ በሚበርባቸው ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻዎች ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችንን የቱሪስት መዳረሻዎች በማስተዋወቅ አብሮ እንደሚሠራ ቃል ገብቶልናል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የቤተ ክርስቲያናችን የቱሪዝም አስጎብኚና የጉዞ ወኪል በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ሲጸድቅና ሲከፈት በጠቅላይ ቤተ ክህነት በመምሪያ ደረጃ የቱሪዝም መምሪያ ተብሎ እንዲዋቀር ይደርጋል፡፡ መምሪያው በሀገሪቱ የቱሪዝም ሕግና የንግድ ሥርዐት በአገልግሎት ሰጪነት እንዲከፈትና እንዲሠራ ይደረጋል፡፡ ይህም ሥራ ሲጀመር የቱሪዝም ክፍሉ ሁለት ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ እሊህም፡-

 • አስጎብኚ (ቱሪስት አስጎብኚ)፣
 • የጉዞ ወኪል (የትኬት ቢሮ) ናቸው፡፡

ቱሪስት አስጎብኚው÷ የቱሪስት ማስጎብኘት ሥራ ይሠራል፡፡ የጉዞ ወኪሉ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮች፣ አባቶች እና ምእመናን ወደ ውጭ ጉዞ ሲያደርጉ የአየር ትኬት ይቆርጣል፤ የትኬት ቢሮ ይኖራል፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን ለተለያየ ተልእኮ እስከ ዛሬ ከሌላ ትኬት ኤጀንሲ ይቆረጥ የነበረው ቀርቶ ከራሷ ቱሪዝም መምሪያ የትኬት ኤጀንት ቢሮ ትኬት በመቁረጥና ኮሚሽኑን ገቢ በማድረግ ከቱሪዝም ከሚገኘው ገንዘብ ባላነሰ ከአየር መንገድ የትኬት ኮሚሽን ተጠቃሚ ትኾናለች፡፡

የቱሪዝም መምሪያው የሰው ኀይልና የቢሮ አደረጃጀት

የቱሪዝም መምሪያው በታቀደለት ዓላማ ሙሉ ሥራውን ለመጀመር የተሟላ የሰው ኀይል አደረጃጀት ሊኖረው ይገባል፡፡ በቅድሚያ መምሪያውን በመምሪያ ደረጃ እንዲዋቀርና የመምሪያ ሓላፊ እንዲኖረው ማድረግ፣ በቀጣይ ባለሞያዎችን እንደ አስፈላጊነቱ መመደብ፡፡ የቱሪዝም መምሪያው ሁለት ክፍል ቢሮዎች ከሙሉ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶች ጋራ በማሟላት ሥራ እንዲጀምር ይደረጋል፡፡

ፈቃድ አደረጃጀት

የቱሪዝም መምሪያው በቅዱስ ሲኖዶስ ተፈቅዶ ሲጸድቅ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በመምሪያ ደረጃ ይዋቀርና በሀገሪቱ የንግድና የቱሪዝም ሕግና ደንብ መሠረት እንዲቀጥል አስፈላጊው ፎርማሊቲ እንዲያሟላ ይደረጋል፤ ሂደቱም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በሚያደርገው የቅርብ ክትትልና በሚሰጠው መመሪያ ይከናወናል፡፡

ልኡኩ በእስራኤል ጉዞው ስለ ቱሪዝም የተመለከተው

እንደሚታወቀው ሁሉ ቱሪዝም የሰው ልጆችን በቋንቋ፣ ባህል፣ አኗኗር፣ በሃይማኖት፣ በታሪክ የሚያስተሳስር ምንም ወጪ የሌለበት ትርፋማ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ማእከለ ምድር ተብላ የምትታወቀው ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ከበርካታ ዘመናት ጀምሮ የንግድና የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ማእከል ኾና ቆይታለች፡፡ በኢየሩሳሌምና አካባቢዎቹ ያሉትን የቅድስና ቦታዎች በየቀኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ይጐበኟቸዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ቱሪዝም በእስራኤል በከፍተኛ ኹኔታ አድጓል፡፡ ሀገሪቱ በዚህ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ገቢዋ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ በተለይም በዓመት ሁለት ጊዜ በልደተ ክርስቶስ እና በትንሣኤ በዓላት በርካታ አባቶችና ምእመናን ቅድስት አገርን ለመሳለምና ለመጐብኘት በተለያዩ የግል አስጐብኚዎችና በተለይም በኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት አማካይነት እንደሚጓዙ ይታወቃል፡፡ በሌላ መልኩ በየዓመቱ ከ50 ሺሕ ያላነሱ እስራኤላዊ አይሁዳውያንና በትውልድ ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤሎች ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ይጐበኛሉ፡፡ በመኾኑም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ጥንታዊና ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ዳብሮ በቱሪዝም እየተሳሰሩ ይገኛል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በዋናው መ/ቤት በኩል የቱሪዝም አገልግሎትን ብታስፋፋ በተለይም ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን በዓመት ሁለት ጊዜ በልደትና በትንሣኤ በዓላት በማስጐብኘት ሐዋርያዊ አገልግሎቷን የሚያጠናክር በሚልዮን የሚቆጠር ገቢ እንደሚያስገኝላት ልኡኩ አረጋግጧል፡፡ በዚህም ፋይናንሳዊ አቅሟን በማጎልበት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶቿን ታስፋፋበታለች፤ ታጠናክርበታለች፡፡ ከዚህም ባሻገር፡-

 • ቤተ ክርስቲያናችን ከምታገኘው ከፍተኛ ገቢ በተጨማሪ ለተሳላሚዎችና ጎብኚዎች በሚሰጠው ያልተከለሰ የታሪክና የትውፊት ማብራሪያ ምእመኖቿን ታገለግላለች፡፡
 • በተሳላሚነት ስም የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ነን እያሉ በፖለቲካ ስደተኝነት ስም የሚቀሩ ዜጐችን ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡
 • በተለያዩ የግል አስጐብዎች በምእመናን ስም እየሄዱ በዚያው በመቅረት ካለ ፈቃድ በሚኖሩ ሕገ ወጥ ስደተኞች የተነሣ የእስራኤል መንግሥት በገዳማችን ላይ የሚያሳድረውን ጥላቻ ያስወግዳል፡፡
 • ቤተ ክርስቲያናችን በቱሪዝም ዘርፉ ላይ በመሥራት ሀገራዊ የልማት ተሳትፎዋን ትገልጽበታለች፡፡

 

 

ሊገጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች

እንደ ልኡኩ ምልከታ ቤተ ክርስቲያናችን ቱሪዝምን በዋናው መ/ቤት በመምሪያ ደረጃ በመክፈቷ በእጅጉ ትጠቀማለች እንጂ ምንም ተጐጂ አያደርጋትም፡፡ ይኹን እንጂ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በዓመት ሁለት ጊዜ በሚደረገው የመሳለም መንፈሳዊ ጉዞ አጋጣሚውን ተጠቅመው በዚያው የሚቀሩ ተሳላሚዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በመኾኑም የጉዞውን ዓላማ ለመጠበቅና በዚህም ሳቢያ ከሚመጣው ዕንቅፋት ለመጠበቅ መፍትሔ ማበጀት ይገባል፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦች

ከላይ የተገለጹትን ችግሮች ለመፍታት ልኡኩ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን አስቀምጧል፡፡ ይህም በሚደረገው ጉዞ፡-

 • ለተጓዡ የዕድሜ መነሻ በመገደብ ከ50 ዓመት በላይ እንዲኾን ማድረግ፤
 • ከኀምሳ ዓመት በታች ለኾነ ተጓዥ በቂ የማስያዣ ገንዘብ እንዲሁም የማይንቀሳቀስ ንብረት በዋስትና እንዲያሲዝ ማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላሉ፡፡

የቱሪዝሙ ክፍል ሌሎች ጠቀሜታ

ይህ የቱሪዝም መምሪያ እያደገና እየተስፋፋ ሲሄድ በሀገር ውስጥ ያሉ ጎብኚዎችን እንዲሁም ከኢየሩሳሌም ውጪ በመላው ዓለም የሚገኙ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በአስጐብኚነት እያመጣ ሀገሪቱንና ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያብስጐበኝ ይኾናል፡፡ በቅድሚያ ግን የበይ ተመልካች ኾና ያሳለፈችው ዘመን በቅቶ በኢየሩሳሌም ጉብኝት ተጠቃሚ እንድትኾን ማስቻል ነው፡፡ ልኡኩ በእስራኤል ቆይታው ምእመናን በኢየሩሳሌም የአጭር ቀናት የመሳለምና የጉብኝት ቆይታቸው ከገበያ እና አልባሌ ጉዳዮች ይልቅ ሃይማኖታዊ የቅድስና መካናትን መጎብኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲናችንን እምነት፣ ሥርዐት፣ ታሪክና ትውፊት ጠብቆ የሚያስጐበኝ ባለሞያ በመመደብ ካሉት አስጐብኚ ድርጅቶች በላቀና በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ለመስጠት ስለሚቻልበት ኹኔታ ልኡኩ አጽንዖት ሰጥቶበታል፡፡

Letter to the Jerusalem Team 02Letter to the Jerusalem Team

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: