የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን እንዲጀምር ታዘዘ

 • ትእዛዙ በዋና ሥ/አስኪያጁ መተላለፉ የጥቂት ጳጳሳት ዐምባገነንነት ማየሉን አረጋግጧል
 • ዕጩዎች ‹‹ልዩነት በሌለው ድምፅ እንዲቀርቡ ተወስኗል›› መባሉ ሐሰት ነው!!
 • የጥር 6 አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ ዝግጅት በተለያዩ ሰበቦች ለማሰናከል እየተሞከረ ነው
 • ከአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ዋነኞቹ ሓላፊነቱን ለመቀበል አልፈቀዱም/አልወሰኑም

ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ፣ ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱን ለማጠናከር የተመረጡ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም ሌሎችም ብፁዓን አባቶች ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 ቀን 2005 ዓ.ም ባካሄዱት የእኵለ ቀን ስብሰባ የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ እንዲጠራ ወስነዋል፡፡ ምልአተ ጉባኤውን ለአስቸኳይ ስብሰባ መጥራት ያስፈለገው ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡

በቅድሚያ÷ በማክሰኞው የቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ስብሰባ መቅድሙና ዋና ዋና ሐሳቡ እንጂ ዋናው ይዘቱ ያልተደመጠውን የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን ሪፖርት አዳምጦ ለመምከር፣ የሰላምና አንድነት ጉባኤውን በአዲስ መልክ ለማቋቋም ወይም ነባሩን በተጨማሪ ቁጥር ለማጠናከር እንዲሁም በቀጣዩ የሰላም ጉባኤ ላይ መክሮ ለመወሰን ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ÷ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡን ምልአተ ጉባኤው በአግባቡ በተጠበቀበት ኹኔታ ለማጽደቅ ነው፡፡ ከዚህም ጋራ በሕገ ደንቡ መሠረት ‹‹ልዩነት በሌለው የምልአተ ጉባኤው ድምፅ ተቋቁሟል›› ስለሚባለው የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ኹኔታ ለመወሰን ነው፡፡

ከአስመራጭ ኮሚቴው በፊት የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን ሪፖርት ማዳመጥና የሰላም ጉባኤውን ውጤት መጠበቅ ይገባል በሚል አቋም የያዙ ብፁዓን አባቶች እንደሚተቹት÷ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ በጸደቀበት የስብሰባ ሥነ ሥርዐት በትንሹ ከ16 ያላነሱ የቅ/ሲኖዶሱ አባላት አልተሳተፉም፤ እንዲሳተፉም አልተደረገም፡፡ በስብሰባው ያልተሳተፉት ብፁዓን አባቶች በሕገ ደንቡ መሠረታዊ አንቀጾች ላይ መሠረታዊ ተቃውሞ/ልዩነት አላቸው፡፡

ከዚህም ባሻገር ከአምስት ያልበለጡ ከሦስት ያላነሱ የፓትርያሪክ ዕጩዎችን የሚያቀርበው አስመራጭ ኮሚቴ ሲቋቋም ምልአተ ጉባኤው ‹‹ልዩነት በሌለው ድምፅ›› እንደወሰነ ተደርጎ በሥያሜው ደብዳቤ ላይ መጻፉ ፍጹም ሐሰት (fallibility) ነው፡፡ መወሰኑ ቀርቶ ኮሚቴው የተቋቋመበት አወዛጋቢ ስብሰባ ሲካሄድ÷ ከውይይቱ ራሳቸውን ያገለሉ፣ በውይይቱ ተሳትፈው ተቃውሟቸውን የገለጹ፣ ከውሳኔው በኋላም በቃለ ጉባኤው ላይ የአቋም ልዩነታቸው እንጂ ፊርማቸውን ለማስፈር ያልፈቀዱ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአስመራጭ ኮሚቴው አባልነት ቢመረጡም የተመረጡበትን ደብዳቤ ያልተቀበሉ፣ በተግባርም እንደማይሳተፉ በግልጽ ያሳወቁና እስከ አሁን ውክልናውን ለመቀበል ያልወሰኑ የሚበዙበት መኾኑ የጉዳዩን አንገብጋቢነት ያመለክታል፤ የምልአተ ጉባኤውን መጠራትም በግድ አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ባለው እውነታ÷ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ እና ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የአስመራጭ ኮሚቴው አባል ኾነው መመረጣቸውን ለመቀበል አልፈቀዱም፡፡ ‹‹የላክኹት መላክተኛ ሳይመለስ በመልእክቱ ላይ አልወስንም›› በሚል የተቃወሙት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ወደ ሰሜን አሜሪካ አምርቶ የነበረው ልኡክ ሪፖርቱን ሳያቀርብ አስመራጭ ኮሚቴ መቋቋሙን በጽኑ ከመቃወም አንሥቶ ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንዲሰጥ በብርቱ ተሟግተዋል፡፡ የልዩነት አቋማቸው በቃለ ጉባኤ እንዲሰፍር አስታውቀዋል፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴው አባል ኾነው የተመረጡበትን ደብዳቤም እንደማይቀበሉ፣ በተግባርም እንደማይሳተፉ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የአስመራጭ ኮሚቴው አባል ተደርገው የተመረጡት ግልጽ ተቃውሟቸውን እያሰሙ በነበረበት ኹኔታ ነው፡፡ ከታዋቂ ምእመናን መካከል አቶ ዓለማየሁ ተስፋዬ፣ ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ፣ አቶ ታቦር ገረሱ (የታዋቂው አርበኛው ዳጃዝማች ገረሱ ዱኪ ልጅ) በአባልነት መመረጣቸውን ጨምሮ በአጠቃላይ ሂደቱ ላይ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በርካታዎች ናቸው፡፡

በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 6/1/ሀ መሠረት ከ13 የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት መካከል አንድ የሰንበት ት/ቤት፣ አንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባል እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡ ይኹንና ‹የሰንበት ት/ቤት እና የማኅበረ ቅዱሳን ተወካዮቹ› ከተቋሞቹ ዕውቅና ውጭ እንዴት እንደተመረጡ፣ ከጉዳዩ አወዛጋቢነት የተነሣም ተወካዮቹ የማንን አቋም እንደሚያራምዱ ግልጽ ባለመኾኑ ለአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ ለክፍለ ከተሞች የሰንበት ት/ቤቶች ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ለአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች ሥራ አመራሮች እና ለማኅበረ ቅዱሳን አባላት በየደረጃው በየዕለቱ የሚጎርፉት ጥያቄዎችና በመካከላቸውም የሚነሡት ክርክሮች ከቀን ወደ ቀን እየተጠናከሩ ናቸው፤ በሂደትም ወደ መከፋፈል ደረጃ እንዳያደርሱ እያሰጉ ናቸው፡፡

እንግዲህ ይህን ያህል ውዝግብ በዐይናችን ፊት ፈጦ እየታየ ባለበት ወቅት ነው የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ሥራቸውን እንዲጀምሩ የሚያሳስብ ደብዳቤ የጻፉት፡፡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ዛሬ፣ ታኅሣሥ 26 ቀን 2005 ዓ.ም በስማቸው ተፈርሞ በወጣውና ለ13 የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት በጻፉት የማሳሰቢያ ደብዳቤ÷ የኮሚቴው አባላት ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተገኝተው ሥራቸውን እንዲጀምሩ አዝዘዋል፤ ደብዳቤውም ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ግልባጭ መደረጉ ተመልክቷል፡፡Letter to the committees

የዜናው ምንጮች ደብዳቤው በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ እንዲጻፍ ሂደቱን ሲያቀላጥፉ ካረፈዱት መካከል÷ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስንና ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን በዋናነት ይጠቅሳሉ፡፡ አንዳንድ ሹማምንት ወደ ዐቃቤ መንበሩ ጽ/ቤት ገባ ወጣ ሲሉ መታየታቸው፣ የእነ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ የጽ/ቤት ሽርጒድም የምንጮቹ ትዝብት ነው፡፡

13ቱ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት የተመረጡበት ደብዳቤ የዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ፊርማና ቲተር አርፎበት በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ በየአድራሻቸው ወጪ ተደርጎ እንደነበር የሚያስታውሱ የመንበረ ፓትርያሪኩ ተቺዎች÷ የዛሬው ደብዳቤ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ወጪ እንዲኾን መደረጉ ዐቃቤ መንበሩና ዋና ጸሐፊው በጉዳዩ ላይ የጠለቀ ልዩነት እንዳላቸው አልያም ጠንቃቃ አቋም ለመውሰዳቸው አስረጅ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡ ተቺዎቹ እንዳሉት በተለይም ‹‹ዕርቁ ይቅደም›› የሚለውን አቋም የያዙት ብፁዕ ዋና ጸሐፊው÷ የዕርቀ ሰላም ልኡኩን ሪፖርት በተሟላ ይዘቱ ማድመጥና መወሰን የሚገባው፣ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕጉ መታየትና መጽደቅ ያለበት፣ የአስመራጭ ኮሚቴው ጉዳይ ለአጀንዳነት የመቅረብ አግባብነት ያለው የሰላም እና አንድነት ጥረት ውጤት ከታወቀ በኋላ መኾን እንዳለበት በተደጋጋሚ በመናገር ላይ ናቸው፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ እስከ ጥር 30 ቀን ድረስ ለ6ው ፓትርያሪክ ምርጫ ከአምስት ያልበለጡ ከሦስት ያላነሱ ዕጩዎች የሚያቀርብ አስመራጭ ኮሚቴ ያቋቋመው ታኅሣሥ 6 ቀን ሲኾን ለአስመራጭ ኮሚቴው መቋቋም መሠረት የኾነውን የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ ያጸደቀው ግን ታኅሣሥ 8 ቀን ነበር፡፡ ቀድሞም ይኹን ዛሬ ለአስመራጭ ኮሚቴው አባላት የተሰራጩት ደብዳቤዎች አነስተኛ የማይባሉ ተመሳሳይ ግድፈቶችና ድግግሞሽ የታዩባቸው ናቸው፡፡ ይኸውም በጥቂት ብፁዓን አባቶች ዘንድ የተያዘውን ከልክ ያለፈ ጥድፊያ፣ እውነቱን ለመናገር ደግሞ ለብዙኀኑ አገልጋይና ምእመን ያለውን ንቀት እንደሚያሳይ ተጠቅሷል፡፡

ጥር 6 ቀን ሞላውን ቅ/ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ጥር 8 ቀን አስመራጭ ኮሚቴው ሥራ እንዲጀምር ማሳሰብ ምን ማለት ይኾን? በርግጥ አስመራጭ ኮሚቴው በተቋቋመ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ኹኔታ አሟልቶ በቅ/ሲኖዶስ ካስወሰነ በኋላ ሥራውን እንደሚጀምር በምርጫው ሕገ ደንብ ተደንግጓል፡፡ ይኸው የምርጫ ሕገ ደንብ ግን ከጸደቀበት የስብሰባ ሥነ ሥርዐት አንሥቶ ገና ብዙ ጥያቄዎች በራሳቸው በቅ/ሲኖዶሱ አባላት የሚነሡበት ነው ተብሏል፡፡ ከምርጫውም በፊትና በላይ የሚቀድም፣ ለጥር 16 ቀን የሚጠበቅ፣ ለብዙኀን የሰላምና አንድነት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የሎሳንጀለሱ ጉባኤ አበው አለኮ!?

ለጥቂቶች ጥር 6 ቀን ለተጠራው ምልአተ ጉባኤ እንደነገሩ የተያዘውን የቅ/ሲኖዶሱን ጽ/ቤት ቅድመ ዝግጅት በመጥቀስ አስመራጭ ኮሚቴው ጥር 8 ቀን ሥራውን እንዲጀምር ማሳሰቢያ መሰጠቱ አያስደንቃቸውም፡፡ በአስቸኳዩ ስብሰባ ‹‹የሚመጣ አዲስ ነገር የለምና፡፡›› ሌሎችም ስብሰባው ራሱ በተሟላ ቁጥር መካሄዱን ይጠራጠራሉ፡፡ ‹‹የተቀጠረው ቀን አመቺ አይደለም፤ ለበዓል [ለከተራ – ጥምቀት] የቀረበ ነው፤ ብዙዎቹ አባቶች (በተለይ የባሕር ማዶዎቹ) የሚገኙ አይመስለንም›› የሚሉት ተቺዎች፣ ውሳኔው ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ የጥሪው ምክንያት ተገልጦና አጀንዳው ተዘርዝሮ በደብዳቤ መሰራጨት ሲገባው በስልክ ብቻ እየተላለፈ ለሚገኘው መልእክት እኩል ትኩረት/ክብደት እየተሰጠው እንዳልኾነ ይናገራሉ፡፡

ስለዚህም ‹‹ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት ዕርቁ ይቅደም›› የሚል ተማኅፅኗቸውን የሚያስተጋቡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን÷ የጥር 6ቱ አስቸኳይ ነገር ግን ታሪካዊና ወሳኝ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ከወዲሁ የተፈጠሩበት ተግዳሮቶች፣ ተንኰሎች፣ ማዳከሚያዎች በደቂቁ እንዲታረሙ፣ ብፁዓን አባቶችም ተገቢው መረጃና የተሟላ ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲዘጋጁ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ጥረትና ግፊት እንዲያደርጉ ጥሪ ተላልፎላቸዋል፡፡

Advertisements

4 thoughts on “የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን እንዲጀምር ታዘዘ

 1. Anonymous January 5, 2013 at 11:52 am Reply

  Abu kelemtos ena abune samuall men honew men asbew new endih mihonut sil betkrstian ena miamnu ayasbum way ways mekarI tefa way

 2. anonymous January 5, 2013 at 3:06 pm Reply

  ግሩም ወቅታዊ ዘገባ ተዋቸው ይሩጡ የእነርሱ ሩጫ የእግዚአብሔርን ትዕግስት ሊቀድም አይችልም

 3. Anonymous January 8, 2013 at 4:31 pm Reply

  Hulum lebetecristian asebewu kehone melkam new, negergen leseltan kehone gena crestian ayedelum malet new woyim crestena alegebachewum.

 4. Anonymous January 12, 2013 at 12:56 pm Reply

  kiristina yelikane phaphasatu bicha adelem yehulachinim enji ,telat libachinin eyaye kebete kiristiyan awutito yerasu lidergen new. endih kehone bitsuan likawuntin be eju asgebituwal!!! be tselot enitga. mi’emenan eniwekibachew; likane phaphasatin eyamogosu ye mengist kadre adereguwachew enyan ye enisun metfonet eyesebeku ke kidist bet liyawetun new!!!!!!! astewulu menafikan min yadergu endeneber, kesawustin ,menekosatin and etc eyatlalu sint wegen kenesu hone;se’ali lene kidist

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: