በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ርእሰ መንበርነት የተመራው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የዕርቀ ሰላም አጀንዳዎችና አቋሞች

  • ‹‹[ዕርቀ ሰላሙ] – የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነትና ሰላም እንደሚጠብቅና የሰላም ወዳዱን ሕዝበ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታ እምነታችን የጸና ነው፡፡››

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 ቀን 2005 ዓ.ም እንደሚያካሂድ በሚጠበቀው ስብሰባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ከኅዳር 26 – 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ ለሦስተኛ ጊዜ ባዘጋጀው ጉባኤ አበው ላይ የተሳተፈውን የዕርቀ ሰላም ልኡካን ሪፖርት ያዳምጣል፤ ከጥር 16 – 18 ቀን 2005 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ በካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ የተቀጠረው ወሳኙ የዕርቀ ሰላም ጉባኤም በመልካም ስለሚቋጭበት ኹኔታ መክሮ የሚበጅ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ የተስፋ ጭላንጭሉ አለ፡፡

የሰላም ልኡካኑ ሪፖርት መቅረብ ከነበረበት ጊዜ በጣም የዘገየ መኾኑ አያከራክርም፡፡ መዘግየቱ የተፈጠረው ግን ልኡኩ በሰሜን አሜሪካ ሁለት አህጉረ ስብከት ውስጥ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከአስተዳደሩና ምእመናኑ ጋራ የገቡበትን ችግር ፈትቶ እንዲመጣ በተሰጠው ተጨማሪ ተልእኮ ሳቢያ እንደኾነ ተገልጧል፡፡ የልኡካኑ የደርሶ መልስ ጉዞ ትኬትም ይህንኑ ተጓዳኝ መርሐ ግብር ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነበር፡፡

ለልኡካኑ መቆየትና ለሪፖርቱ መዘግየት የሚጠቀሰው ምክንያት ይኸው እንደኾነ ልኡካኑ ለቅዱስ ሲኖዶሱ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡ ልኡካኑ በቆይታቸው ባከናወኗቸው ተግባራት ምን ያህል ውጤታማ ነበሩ የሚለው ደግሞ ስለ ሪፖርቱ በሚካሄደው ውይይት የሚወሰን ይኾናል፡፡

የልኡካኑን መድረስና ሪፖርታቸውን በመጠባበቅ መካከል ቅ/ሲኖዶሱ ያከናወነው ተግባርና ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ግን የማክሰኞውን ስብሰባ በውጥረት የተሞላ ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ከሳምንት በላይ ጊዜ ወስዶ በጸደቀው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ ጠቅላላ  ይዘት፣ ረቂቁ በታየበት የስብሰባ ሥነ ሥርዐት እና የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን አኳያ ዳግመኛ ውይይት የሚቀሰቅሱ ነጥቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህም ባሻገር የምልአተ ጉባኤው አባላት ክፉኛ የተከፋፈሉበት፣ የዕርቀ ሰላም ልኡካኑም የተቃውሞ መግለጫ የሰጡበት፣ ከተሠየሙት አባቶችና ግለሰቦችም የሚበዙት ለመቀበል ያልፈቀዱት የአስመራጭ ጉባኤው መቋቋም ዐቢይ የመነጋገሪያ ነጥብ እንደሚኾን ይጠበቃል፡፡ ከትላንት በስቲያ ምሽት ‹‹ወደመጣኽበት እንድትመለስ ተወስኗል›› በሚል ትኬት ተቆርጦላቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተደረጉት የሰላምና አንድነት ጉባኤው አባል ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ጉዳይ የምልአተ ጉባኤውን አባላት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጠያይቅ ይጠበቃል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ሰላም እንደሚያረጋግጥ የታመነበት የዕርቅና ሰላም ሂደት በወሳኝ ምዕራፍ ላይ በሚገኝበትና ከዚህም አኳያ ‹‹ከፓትርያሪክ ምርጫው ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉ ወገኖች ድምፅ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሚያስተጋባበት ወቅት አገልጋዩና ምእመኑ ከማክሰኞው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ብዙ ይጠብቃል፡፡ የዕርቀ ሰላም ሂደቱ÷ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነትና ሰላም እንደሚጠብቅና የሰላም ወዳዱን ሕዝበ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታ በአገልጋዩና ምእመኑ ውስጥ ያለው ጽኑ እምነት በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አባላትም ዘንድ እንዳለ ምልአተ ጉባኤው በየካቲት ወር 2003 ዓ.ም ለዕርቀ ሰላሙ የለያቸው የውይይት አጀንዳዎችና በአጀንዳዎቹ ላይ የያዛቸው አቋሞች ያረጋግጣሉ፡፡

የአጀንዳዎቹና አቋሞቹ ይዘት ምንም ቢኾን ምልአተ ጉባኤው የዕርቀ ሰላሙ ሂደት ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነትና ሰላም እንደሚጠብቅና የሰላም ወዳዱን ሕዝበ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታ›› በግልጽ ያስቀመጠው እምነቱ እዚያው ሳለ የችግሩን አስከፊነት የሚያጠይቅ በመኾኑ ዛሬም በተባበረ ድምፅ ሊጠብቀው የሚገባ ነው፡፡ ዛሬም ለዚህ እምነቱ ተገዥ ኾኖ የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ሰላም ለሚያረጋግጠው አጀንዳ ቅድሚያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፤ እንጠብቃለን፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ርእሰ መንበርነት የተመራው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለዕርቅና ሰላም ጉባኤው ያዘጋጃቸው የውይይት አጀንዳዎች እና በአጀንዳዎቹ ላይ የያዛቸው አቋሞ

 

1.  በስደት በሚገኙት አባቶች ላይ በተላለፈው ቃለ ውግዘት የቤተ ክርስቲያን አንድነት ተቆርቋሪዎች ሁሉ በችግር ላይ ይገኛሉና ዕርቀ ሰላሙ ከተፈጸመ በኋላ የተላለፈው ቃለ ውግዘት እንዲነሣ ኾኖ የሰላሙና የዕርቁ ውይይት እንዲቀጥል

 

2.  ዐራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ  ተመልሰው በጡረታ መልክ እየተረዱ በአዲስ አበባ በመረጡት ቦታ ተወስነው ይቀመጡ

 

3.  በስደት የሚገኙ የቀድሞ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ቅ/ሲኖዶስ    በሚመድባቸው ሀገረ ስብከት ይሥ

 

4.  በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ በውጭ ሀገር የተሠየሙ ኤጲስ ቆጶሳት ቀኖናውን በቀኖና አሻሽሎ ቅ/ሲኖዶስ በሥራ ይመድባቸው፡፡

ሙሉ ይዘቱን ከዚህ በታች ይመልከቱ

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን              ቁጥር – 138/812/2003

        ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት                                           ቀን – 6/7/2003 ዓ.ም

 

ለሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን    

የሰላምና አንድነት ጉባኤ አስተባባሪ                        

ሰሜን አሜሪካ

በሀገር ውስጥ በሚኖሩት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በውጭ አገር በስደት በሚገኙት አባቶች መካከል ያለው ችግር በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ የሚያደርጉ ከቀደምት ብፁዓን አባቶች ሦስት እና ከሊቃውንት አንድ፡-

1)  ብፁዕ አቡነ ገሪማ  

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ

የዓለም አብያተ ክርስቲያን ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቢሮ ዋና ጸሐፊና የድሬዳዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ – በሰብሳቢነት

2)  ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ

የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ – በአባልነት

3)  ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ረዳትና የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ – በአባልነት

4)  ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ

በጠቅላይ ቤተ ክህነት በመንፈሳዊ የሥራ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ – የኮሚቴው አባልና ጸሐፊ በመኾን እንዲሠሩ፤

በሁለቱም ወገኖች ዕርቀ ሰላም እንዲፈጠር ጥረት የሚያደርጉ የታመነባቸው ሦስት ታዋቂ ሽማግሌዎች፡-

1)  ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም

2)  ቀኛዝማች ዘውዱ አስፋው

3)  ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ የዕርቀ ሰላሙ አደራዳሪ ሽማግሌዎች ኾነው እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተሠይመዋል፡፡

የውይይቱ አጀንዳዎች

ከተፈጠረው የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ግድፈት የተነሣ

1)  በውጭ አገር በስደት በሚገኙት አባቶች ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈው ቃለ ውግዘት ባለመነሣቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ተቆርቋሪዎች የኾኑት ሁሉ በችግር ላይ የሚገኙ ስለኾነ ዕርቀ ሰላሙ ከተፈጸመ በኋላ የተላለፈው ቃለ ውግዘት እንዲነሣ ኾኖ የሰላሙና የዕርቁ ውይይት እንዲቀጥል፤

2)  ሰላምን ለማስገኘት የተደረገው ጥረት ለሠመረ ውጤት ከበቃ በኋላ ዐራተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያሪክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው አስፈላጊው ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመቻችቶላቸው በጡረታ መልክ እየተረዱ ሕክምናም ኾነ ሌላ አገልግሎት በቅርብ ማግኘት እንዲችሉ በአዲስ አበባ በመረጡት ቦታ በጸሎት ተወስነው እንዲቀመጡ፤

3)  በሦስተኛውና በአራተኛው ፓትርያሪኮች አንብሮተ እድ በሀገር ውስጥ የተሠየሙት የቀድሞ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚመድባቸው ሀገረ ስብከት እንዲሠሩ፤

4)  ዐራተኛ ፓትርያሪክ በነበሩት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ በውጭ አገር የተሠየሙት ኤጲስ ቆጶሳትን ቀኖናውን በቀኖና አሻሽሎ በቅዱስ ሲኖዶስ በሥራ እንዲመድባቸው፡፡

የሰላምና አንድነት ጉባኤ አስተባባሪ በተዘጋጁት አጀንዳዎች መሠረት ግራ ቀኙ የኖርዌ ቤተ ክርስቲያን በምታዘጋጀው በኖርዌ ወይም በደቡብ አፍሪካ ከሁለቱ በአንዱ እንዲወያዩ ኹኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

ስለዚህ የመወያያው አጀንዳ የተዘጋጀበትን 4 ገጽ ቃለ ጉባኤ ከዚህ ጋር የላክን መኾናችንን እየገለጽን የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ሰላም እንደሚጠበቅና የሰላም ወዳዱ ሕዝበ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታ እምነታችን የጸና ነው፡፡

                                                              እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

                                                                           አባ ጳውሎስ (ዶ/ር)

                                                        ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

                                               ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

                                                 የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት

                                                የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት

ግልባጭ

  • ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ልዩ ጽ/ቤት
  • ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
  • ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ የዕርቀ ሰላም ኮሚቴው ሰብሳቢ

         አዲስ አበባ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: