ስለ ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴው

  • ኮሚቴው በኮሚቴነቱ ተሟልቶ ይቀጥል ይኾን? 

ከታኅሣሥ መጀመሪያ አንሥቶ ከሳምንት በላይ ስለ ፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ ረቂቅ ሲመክር የሰነበተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ታኅሣሥ 8 ቀን 2005 ዓ.ም ሕገ ደንቡን አጽድቋል፡፡ በዘጠኝ ገጾች የተካተተውና 15 አናቅጽ ያለው ይኸው ሕገ ደንብ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ምርጫ የ2005 ዓ.ም ሕገ ደንብ›› ተብሎ ሊጠቀስ እንደሚችል የሕገ ደንቡ የመጀመሪያ አንቀጽ ይገልጻል፡፡

በሕገ ደንቡ አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 1(ሀ) የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ÷ ከሊቃነ ጳጳሳት 4፣ ከገዳማት አበምኔቶች 2፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ በየደረጃው ባለው መዋቅር ውስጥ ከሚያገለግሉት መካከል የተመረጡ 2 ሠራተኞች፣ 3 ምእመናን፣ 1 የሰንበት ት/ቤት ወጣት እና 1 የማኅበረ ቅዱሳን አባል በድምሩ 13 አባላት በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት እንደሚቋቋም ይደነግጋል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና ጸሐፊም በቅዱስ ሲኖዶሱ እንደሚመደብ በዚሁ ንኡስ አንቀጽ (ሐ) ላይ ተመልክቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ቅዱስ ሲኖዶስ የኮሚቴውን ሥራ በበላይነት እንደሚቆጣጠር፣ እንደሚከታተል፣ በሕገ ደንቡ ያልተሸፈኑ ጉዳዮች ሲገጥሙም መመሪያ እንደሚሰጥ ተገልጧል፡፡

በሕገ ደንቡ አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 2(ሀ) መሠረት ኮሚቴው በተቋቋመ በአንድ ወር ውስጥ ለሥራው የሚያስፈልጉትን ግብአቶች፣ የምርጫውን ቦታ፣ ቀንና ሌሎች ከምርጫው ጋራ የተያያዙ ጉዳዮችን በሙሉ ከዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ጋራ አዘጋጅቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ አስወስኖ ተግባሩን እንደሚያከናውን ተመልክቷል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ታኅሣሥ 6 ቀን በዋለው ጉባኤው ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ከሦስት ያላነሱ ከአምስት ያልበለጡ ዕጩ ሊቃነ ጳጳሳት ለውድድር እንዲቀርቡ ወስኗል፡፡ ኮሚቴው እስከ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ዕጩዎቹን ለምልአተ ጉባኤው እንዲያቀርብ የታዘዘበት ደብዳቤም በቁጥር 208/49/2005 በቀን 11/4/2005 ዓ.ም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ አማካይነት ወጥቶ ለ13 የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ተሰራጭቷል፡፡

ኮሚቴው በምልአተ ጉባኤው ከተቋቋመ ሁለት ሳምንት ያለፈው ቢኾንም የመንበረ ፓትርያሪክ ምንጮች እንደሚሉት እስከ አሁን ድረስ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ እና ጸሐፊ መርጦ መደበኛ ተግባሩን ለመጀመር በሚያስችለው ኹኔታ ውስጥ አይደለም የሚገኘው፡፡ በምትኩ ለአስመራጭ ኮሚቴ አባልነት ከተጠቆሙት ውስጥ የተመረጡበትን ደብዳቤ ያልተቀበሉና ለመቀበልም ፈቃደኛ ያልኾኑ፣ ቢቀበሉም በተግባር በመሳተፉ ላይ የሚያመነቱና ተወክለውበታል የሚባለውን ተቋም ይኹንታ ያላገኙ አባላት እንደሚበዙበት ታውቋል፡፡

ለዚህም ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም፤ የሎሳንጀለሱ የሰላምና ዕርቅ ጉባኤ ውጤት ይታወቅ›› በሚል ከውስጥ የአስመራጭ ኮሚቴውን አለወቅቱ መሠየም ፊት ለፊት ከመቃወም ጀምሮ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ የመጣው የቅ/ሲኖዶስ አባላት፣ ከውጭም ለምርጫው የሚደረገው ዝግጅት እንዲቆም በተለያዩ መንገዶች እየተገለጸ የሚገኘው የአገልጋዮችና ምእመናን ድምፅ ተጠቃሽ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ይህም በይበልጥ የሎሳንጀለሱ አራተኛ ዙር የዕርቅና ሰላም ጉባኤ ቀናት እየቀረበ በመጣ ቁጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ለአስመራጭ ኮሚቴው አባላት የጻፈውን ደብዳቤ ሙሉ ይዘት ለትክክለኛ እና የተሟላ መረጃዎ ይኾን ዘንድ ከዚህ በማስከተል አቅርበነዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

        ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት

       

        ለብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ

             የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ

        ለብፁዕ አቡነ ቄርሎስ

             የሰሜን ወሎና ዋግ ሕምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

        ለብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ

             የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

        ለመልአከ ምሕረት ዓምደ ብርሃን ገብረ ጻድቅ

             የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊ

        ለሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ

             የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ

        ለፀባቴ ኀይለ መስቀል ውቤ

             የደብረ ሊባኖስ ገዳም አስተዳዳሪ

        ለንቡረ እድ ዕዝራ ኀይሉ

             የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ

        ለቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ

        ለአቶ ዓለማየሁ ተስፋዬ

        ለአቶ ባያብል ሙላቴ

        ለዲያቆን ኄኖክ ዐሥራት

        አዲስ አበባ፤

ለ6ው ፓትርያሪክ ምርጫ ከሦስት ያላነሱ ከአምስት ያልበለጡ ዕጩ ሊቃነ ጳጳሳት ለውድድር እንዲቀርቡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ታኅሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ጉባኤ ልዩነት በሌለው ድምፅ ወስኖአል፡፡

ስለዚህ እናንተ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስመራጭ ኮሚቴ ኾናችሁ የተመረጣችኹ ስለኾነ ለ6ው ፓትርያሪክነት ምርጫ ዕጩ ኾነው የሚቀርቡ ከሦስት ያላነሱ ከአምስት ያልበለጡ ተወዳዳሪ ዕጩ ሊቃነ ጳጳሳትን፡-

  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች
  • ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎች
  • ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን
  • ከገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች
  • ከማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን
  • ከገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች
  • ከሰንበት ት/ቤት መንፈሳውያን ወጣቶች

በሚሰጥ ጥቆማ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙትን ለ6ው ፓትርያሪክ ምርጫ ተወዳዳሪ የሚኾኑ ከሦስት ያላነሱ ከአምስት ያልበለጡ ዕጩ ሊቃነ ጳጳሳት እስከ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንድታቀርቡ የተወሰነ መኾኑን እናስታውቃለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

                                                         አባ ናትናኤል

                                              የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

                                    ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ግልባጭ

  • ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ጽ/ቤት
  • ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

አዲስ አበባ

Picture 009

Picture 010

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: