ቅ/ሲኖዶስ የቁሉቢ ደ/ኀ/ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በቦርድ እንዲተዳደር ወሰነ

  • በየክብረ በዓሉ ከሚሰበሰበው እስከ 24 ሚልዮን ብር የገዳሙ ገቢ አህጉረ ስብከት፣ ኮሌጆችና ተቋማት በበጀት ይደጎማሉ
  • ገዳሙ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ደረጃ የተቋቋመ የንዋየ ቅድሳት ማደራጃ ቢኖረውም ሒሳቡ በፓትርያሪኩ ልዩ ወጪዎች ሥር ተካትቶ ከቁጥጥር ውጭ ተደርጎ ቆይቷል
  • የቁሉቢ ቅ/ገብርኤል ገዳም ጽላት ከታቦተ ጽዮን ጋራ ከመጡት ጽላት አንዱ መኾኑን ያውቃሉ?
  • በቁሉቢ የቅ/ገብርኤል ክብረ በዓል የቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ትኩረት ይሰጠው!!

በምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት የሚገኘው የርእሰ አድባራት ቍሉቢ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በሚመራ አጠቃላይ ቦርድ እንዲተዳደር ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡ ውሳኔው የተላለፈው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 እና ሐምሌ 19 ቀን በሚውለው ክብረ በዓል ከተሳላሚው ምእመን የሚሰበሰበው በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ፣ ንዋየ ቅድሳትና ወርቅ በአግባቡ ተስብስቦ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ስለሚደግፍበት ኹኔታ በተወያየበት አጀንዳ ነው፡፡

በስእለት ሰሚነቱ እና በዕፁብ ድንቅ የተኣምራት ዝናው በውጭ ሰዎችና በሌሎች እምነቶች ተከታዮች ዘንድ ሳይቀር ከሚታወቀው የቍሉቢ ደ/ኀ/ቅ/ገብርኤል ገዳም በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰበሰበውን ገንዘብ፣ ንዋየ ቅድሳት እና ወርቅ በዐቢይ ኮሚቴአስቆጥሮ ገቢ የሚያደርገው በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የተቋቋመው የቍሉቢ ንዋየ ቅድሳት ማደራጃ የተሰኘው አካል ነው፡፡ ንዋየ ቅድሳቱ ዐቢይ ኮሚቴው በሚያወጣው ተመን መሠረት እንደ ሚሸጡ፣ ገንዘቡ ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ በጀት ለተያዘላቸው አህጉረ ስብከት፣ መንፈሳዊ ኮሌጆች እና ሌሎች ተቋማት እንዲደርስ መደረጉ በዓመታዊው የመ/ፓ/አጠ/ሰ/መ/ጉ የሚቀርቡት የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርቶች ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት ያህል ንዋየ ቅድሳት ማደራጃው በ2003 ዓ.ም በጀት ዓመት ብር 28,786,658.02 ገቢ አድርጎ ከወጪ ቀሪ ብር 3771905.71 እንደነበረው፤ በ2004 በጀት ዓመት ደግሞ ብር 17,113,302.21 ገቢ አድርጎ ከወጪ ቀሪ ብር 5647335.20 እንዳለው ሪፖርቶቹ ያመለክታሉ፡፡

የቁሉቢ ደ/ኀ/ቅዱስ ገብርኤል ገዳም

የቁሉቢ ደ/ኀ/ቅዱስ ገብርኤል ገዳም

የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች ግን ክብረ በዓሉን ከማስፈጸም ጀምሮ በስእለት ሰሚው ታቦት ስም የሚገኘው ገቢ የሚሰበሰብበትና ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ ለምዝበራ የተጋለጠ እንጂ በማደራጃው ሪፖርቶች ላይ እንደተገለጸው አለመኾኑን ይናገራሉ፡፡ በተለይም የቀድሞው ፓትርያሪክ÷ ክብረ በዓሉን የሚያስፈጽሙና የገቢ ቆጠራውን የሚያካሂዱ የማደራጃውን ዐቢይ ኮሚቴ አባላት በራሳቸው በመመደብ፣ ቆጠራው ተጠቃሎ ገንዘቡና ንዋየ ቅድሳቱ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ከመላኩ በፊት እና ከተላከም በኋላ አስተዳደሩን በፓትርያሪኩ ልዩ ወጪዎች ሥር በማካተትና ከቁጥጥር አገልግሎቱ ውጭ በማድረግ ለብክነት ሲዳረግ መቆየቱን የምንጮቹ ገለጻ ያመለክታል፡፡

ለዚህ ዐይነቱ ብልሹ አሠራር ተጋልጠው ከቆዩት የቤተ ክርስቲያናችን አቅም ፈጣሪ የልማት ተቋማት መካከል÷ የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት፣ የተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት ርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ እንደሚገኙበት ምንጮቹ አያይዘው የገለጹት የዜናው ምንጮች÷ የቍሉቢ ደ/ኀ/ቅ/ገብርኤል ገዳም በአጠቃላይ ቦርድ ለመምራት ቅዱስ ሲኖዶሱ ስላሳለፈው ውሳኔ የተለያዩ ትችቶችን ይሰነዝራሉ፡፡ በ31ው የመ/ፓ/አጠ/ሰ/መ/ጉባኤ ላይ ሐሳቡ ቀርቦ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘውና የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሚያሠራ መንገድ ተጠንቶ እንዲቀርብለት መመሪያ ከሰጠበት ማእከላዊ የፋይናንስ አስተዳደር አንጻር የአጠቃላይ ቦርዱ መቋቋም አጋዥ ሊኾን እንደሚችል ተስፋ የሚያደርጉ እንዳሉ ሁሉ ከገዳሙ አስተዳደርና ለቦርድ አባልነት ከተመረጡት ሰዎች በመነሣት ‹‹ተስፋው በከንቱ ነው›› ሲሉ የሚተቹም አልጠፉም፡፡

በቦርድ አባላቱ አሠያየምና ከተሠየሙት አባላትም መካከል ከቀድሞው ፓትርያሪክና ከዚያም በፊት በነበራቸው ሓላፊነት ‹‹የጥቅመኞችና የመዝባሪዎች አለቃ ናቸው›› በመኾናቸው ከ18 ዓመታት በላይ በሥራ አስኪያጅነት ከቆዩበት ድርጅት ውጭ ተደራራቢ ሥልጣን የሚሰጣቸውንና ከ70 ዓመት በላይ በሚቆጠረው ዕድሜያቸው እንኳ የአቡነ ጳውሎስ የጡረታ ማዕበል ‹ያለፋቸውን› እንደ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል ያሉ የሥራ ሓላፊዎችን ተቺዎቹ በዋነኛ አስረጅነት ይጠቅሳሉ፡፡

ቅዱስ ሰኖዶስ ቦርዱን እንዲመሩ ከመደባቸው የምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጋራ በተለያዩ ሓላፊነቶችና በአባልነት እንዲሠሩ ከመረጣቸው ዐሥር ግለሰቦች መካከል÷ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል (የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ) በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢነት፣ መጋቤ ሠናያት ኀይለ ማርያም ገብረ ሚካኤል (የምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ) በቦርዱ ጸሐፊነትና አባልነት፣ መልአከ ኀይል ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ማርያም (የቁ/ደ/ኀ/ቅ/ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ) በአስረጅነትና በአባልነት ይገኙበታል፡፡ የተቀሩት የቦርድ አባላትም መልአከ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎሬዎስ (የገዳማት መምሪያ ዋና ሓላፊ)፣ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ(የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ)፣ መ/ር አባ ኪዳነ ማርያም ደስታ (የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ጸሐፊ)፣ ዶ/ር ስመኝ ታፈሰ (ከሐሮማያ ዩኒቨርስቲ)፣ ሊቀ ኅሩያን ጥበቡ ጌጤ፣ ዲያቆን ድንበሩ ሰጤ እና ዲያቆን ገዳሙ አበበ መኾናቸው ተገልጧል፡፡

በተያያዘ ዜና÷ ከነገ በስቲያ ታኅሣሥ 19 ቀን 2005 ዓ.ም በሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል በዓል አጋጣሚ የወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን ዓለም አቀፍ አጀንዳ የኾነው የሰላምና አንድነት ጉዳይ ክብረ በዓሉ ደምቆ በሚከበርባቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌሉና መዝሙሩ ማእከላዊ መልእክት እንዲኾንና ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል፡፡ በተለይም በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ተሳላሚ ሕዝብ ከሀገር ውስጥና ከውጭ በሚገኝበት የቍሉቢ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም÷ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም ጸሎት ከማድረግ አንሥቶ ከበዓሉ አንድ ቀን ቀድሞ በተለያዩ መንፈሳውያን ማኅበራት በሚካሄዱት የምእመናን ጉባኤያት ስለ ዕርቀ ሰላሙ መረጃና ግንዛቤ የሚሰጡ፣ ስለ ምእመናን ድርሻ የመንፈስና የተግባር አንድነት የሚፈጥሩ መልእክቶች በማስተላለፍ ረገድ መምህራነ ወንጌል እንዲተባበሩ ተጠይቋል፡፡

በቆየው ልማድ መሠረት ከክብረ በዓሉ ሁለት ቀን ቀደም ብለው ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ በዛሬው ዕለት ወደ ድሬዳዋ ያመሩት ዐቃቤ መንበረ መንበረ ፓትርያሪኩ÷ በክብረ በዓሉ ላይ በሚገኙበት፣ ሚዲያውም በተወሰነ መልኩ ትኩረት በሚሰጥበት አጋጣሚ ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚለው ምእመን ድምፅ እንዲሰማ ድጋፍ ሰጥቶ መንቀሰቀሱ በርግጥም ተገቢ ነው፡፡

ታኅሣሥ 19 ቀን የራማው ልዑል ቅዱስ ገብርኤል ሠለስቱ ደቂቅን ከነደደው እሳት ያወጣበት ቀን መታሰቢያ ነው፡፡ ይህን አስደናቂ የመልአኩን ሥራ ለመዘከርና እግዚአብሔር በቅዱስ ገብርኤል አማካይነት በሰጠን ቃል ኪዳኑ ለመማፀን ዛሬ በምንሰበሰብበት በቅዱሱ የቍሉቢ ተራራ÷ የእውነት አምላክ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያስታግሥልን፣ ሰላሙንና አንድነቱን እንዲሰጠን እንለምነዋለን፡፡

በቀድሞው አጠራር የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩት ልዑል ራስ መኰንን በአርባ የቁም ከብት ከባላባቶች በገዙት ቦታ ቅዳሴ ቤቱ በሐምሌ ወር 1879 ዓ.ም በድንኳንና በመቃኞ የተከበረው የቍሉቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን÷ ከገጠር ቤተ ክርስቲያን ሥሪት ወደ ደብር የተለወጠው በስእለት ሰሚነቱ በመላው ኢትዮጵያ መታወቅ በጀመረበት በ1884 ዓ.ም ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ገዳማት አንዱ ኾኖ በገዳም ሥርዐት እንዲተዳደር የተወሰነው ደግሞ መንፈሳዊ አገልግሎቱ፣ ገቢረ ተኣምራቱ እና ታሪካዊነቱ በሀገር ውስጥና በውጭ እየገነነ ከመጣበትና አሁን ቆሞ የሚታየው ሕንፃ÷ በግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ፈቃድ፣ በሁለተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ (በወቅቱ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ) መመሪያ ሰጭነት፣ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በሥራ ሚኒስቴር በኩል በመደበው ተቆጣጣሪ አማካይነት በ1957 ዓ.ም በተጠናቀቀበት ወቅት እንደነበር የገዳሙ ታሪክ ያስረዳል፡፡

የርእሰ አድባራት ቍሉቢ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አጭር ታሪክ

ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 461 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት የሚገኝ ገዳም ነው፡፡ የገዳሙን አመሠራረት በተመለከተ በብዙ ሊቃውንት እንደሚተረከው÷ በዘጠነኘው መ.ክ.ዘ ዮዲት ጉዲት ተነሥታ አብያተ ክርስቲያናትን ስትመዘብር፣ ክርስቲያኖችን ስትገድልና መጻሕፍትን ስትቆነጻጽል ንጉሥ አንበሳ ውድም በአኵስምና በአካባቢዋ የነበሩ ታቦታትንና ንዋያተ ቅድሳትን በመያዝ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ዝዋይ መጣ፡፡

አባ ሌዊ ከሰባት ቀን ሱባኤ በኋላ ታቦተ ቅዱስ ገብርኤልን ይዘው ወደ አኵስም ሲጓዙ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ ‹‹እኔ ወደማሳይኽ ቦታ ታቦቱን ይዘኽ ሂድ›› አላቸው፡፡ አባ ሌዊም ታቦቱን ይዘው ተከተሉትና ወደ ቍሉቢ ደረሱ፡፡ ለአባ ሌዊም የተፈቀደላቸው ቦታ ይህ መኾኑን ታቦቱም በኋላ ዘመን ለሕዝቡ ድንቅ ሥራ እንደሚሠራ ቅዱስ ገብርኤል ነግሯቸው ተሰወረ፡፡ አባ ሌዊ በቦታው ለ130 ዓመታት ያህል አገልግለው በንጉሥ ግርማ ሥዩም ዘመነ መንግሥት ታኅሣሥ 14 ቀን ዐርፈዋል፡፡

በግራኝ አሕመድ ወረራ ብዙ ካህናት ከሰሜን ኢትዮጵያ (ምናልባት በደቡብ ጎንደር አካባቢም ተመሳሳይ ታሪክ ስለሚነገር ከዚያው ሳይኾን እንደማይቀር ይገመታል) ታቦታትንና ንዋያተ ቅድሳትን ይዘው ሲጓዙ ቁሉቢ ደረሱ፡፡ መልአከ ገነት መብረቁ፣ መምህር የማነ አብ፣ አባ ተከሥተ ሥሉስ የተባሉ ካህናት ከተነጠፈ ድንጋይ ላይ የተጻፈ ነገር ያገኛሉ፡፡ ጽሑፉም ታቦተ ቅዱስ ገብርኤል በስውር መቀመጡን፣ ልዩ ልዩ ተኣምራት እንደሚፈጸምበት፣ ወደፊት ታላቅ ቤተ መቅደስ እንደሚሠራበት፣ አባ ሌዊ ታቦቱን እንዴት ወደዚህ እንዳመጡት የሚገልጽ ነበር፡፡ እነርሱም ይህን ታሪክ ይዘውት በነበረው በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ ኅዳግ ጻፉት፡፡ ወደ ደሴተ ዝዋይ ሲደርሱም መጽሐፉን በዚያ አኖሩት፡፡

st._gabrielልዑል ራስ መኰንን ከዝዋይ ደሴት መጽሐፈ ቀሌምንጦስን አስመጥተው ሲያነቡ የቍሉቢ ቅ/ገብርኤልን ታሪክ በማግኘታቸው የቅዱስ ገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን ለማነፅ ተነሡ፡፡ ልዑል ራስ መኰንን በአካባቢው የአየር ንብረት ተማርከው፣ የአስተዳደራቸውም ማእከል በቍሉቢ አቅራቢያ ራስ ከተማ እየተባለ የሚጠራው ቦታ ስለነበር በስፍራው ቤት ሠርተው ነበር፡፡ ልዑሉ ቍሉቢ ገብርኤል ከመትከላቸው በፊት ቦታው የአካባቢው ጎሳዎች የግጭት መናኸርያ ነበር፡፡ ታዲያ ልዑሉ ‹‹ሰላምን በአካባቢው ከመሠረትኽ በቦታው በስምኽ ቤተ ክርስቲያን አሠራለኹ›› ብለው እንደተሳሉም ይነገራል፡፡

የተሳሉት በመፈጸሙ የቅዱስ ገብርኤል ታቦት የት እንዳለ ሲያፈላልጉ ቡልጋ ኢቲሳ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አካባቢ ልዩ ስሙ አዥጎቤ (እጅጉ) ካህናተ ሰማይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አባ ዱባለ በሚባሉ መናኝ መነኮስ ሐላፊነት ለዓመታት የተቀመጠ ታቦተ ቅዱስ ገብርኤል መኖሩ ተነገራቸው፡፡ ልዑል ራስ መኰንን ለአባ ዱባለ መልእክት ስለላኩባቸው ከሐረር ከመጡት ካህናት አማካይነት የቅዱስ ገብርኤልን ታቦት ላኩ፡፡ ልዑል ራስ መኰንንም ከነሠራዊታቸው ሸንኮራ ድረስ ሄደው ታቦቱን በመቀበል የካቲት 24 (ሐምሌ 19 ቀን የሚልም አለ) 1879 ዓ.ም ታቦቱ ቍሉቢ ገባ፡፡

ከ1879 – 1884 ዓ.ም በድንኳንና በመቃኞ ከቆየ በኋላ በጽድና በዝግባ ከተሠራ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ እስከ 1954 ዓ.ም ቆይቷል፡፡ የጽድና ዝግባው ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ የተጣለው ሐምሌ 19 ቀን 1883 ዓ.ም ሲኾን ሥራው ተጠናቆ የተባረከው ደግሞ ታኅሣሥ 19 ቀን 1884 ዓ.ም በግብጻዊው ጳጳስ በአቡነ ማቴዎስ ነው፡፡ ቦታውን ከባላባቶች የገዙት በአርባ የቁም ከብት ነው፡፡ በመጀመሪያ ሲተከል በገጠር ቤተ ክርስቲያን ሥሪት ሲኾን በኋላ ግን በስእለት ሰሚነቱ በመላው ኢትዮጵያ እየታወቀ ስለመጣ ደብር ኾኗል፡፡

አሁን የሚታየው ሕንጻ በዘመናዊ ፕላን የተሠራው ከ1954 – 1957 ዓ.ም ነው፡፡ የሥነ በዓሉ አፈጻጸም በሬዲዮና በቴሌቪዥን ስለሚተላለፍም በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ምእመናን በየዓመቱ በገዳሙ እየተገኙ በዓሉን ለማክበር፣ በረከቱን ለመሳተፍና ገቢረ ተኣምራቱን ለማስተላለፍ አመቺ መንገድ ተፈጥሯል፡፡
የአሁኑ ሕንጻ ሥራው የተዋጣለት በዋናነት በእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድና በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ነው፡፡ በሥራ አመራር ሰጭነት በጊዜው የሐረርጌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ በኋላ ሁለተኛው ፓትርያሪክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፕላኑ በጥንቃቄ እንዲዘጋጅ አድርገው ከንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ አቅርበው ሥራው እንዲፈቀድ አድርገዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በሥራ ሚኒስቴር ተቆጣጣሪነት እንዲሠራ ሲያደርጉ በአካልም ከስፍራው እየተገኙ መመሪያ ይሰጡ እንደነበር የገዳሙ መዛግብትና አበው ያስረዳሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ሥራ በተገቢው ኹኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ ታቦተ ሕጉ ወደ አዲሱ ቤተ መቅደስ ሲገባ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፣ ልዩ ልዩ ባለሥልጣኖችና ሚኒስትሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡ ከዚሁ ደረጃ ከደረሰ በኋላ መሠረታዊ ዓላማውን ማራመድ ስለሚገባው በ1957 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ገዳማት እንደ አንዱ ሲሠራ የገዳሙ መተዳደሪያ ደንብም ተቀርጾለታል፡፡

ምንጭ፡-

  • ፈለገ ሕይወት መጽሔት፤ መሪጌታ ዘገብርኤል ወልደ ሰንበት፤ የቍሉቢ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አመሠራረት፤ ሐምሌ/ነሐሴ 1993 ዓ.ም
  • ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤ የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች፤ 1999 ዓ.ም፤ ገጽ 203 – 205
Advertisements

One thought on “ቅ/ሲኖዶስ የቁሉቢ ደ/ኀ/ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በቦርድ እንዲተዳደር ወሰነ

  1. Anonymous December 27, 2012 at 1:50 pm Reply

    It is a very nice short version history of Kulubi Gabreiel. I wish you had mentioned the name of the Priest who went and brought the Arc. There were four of them!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: