የቅ/ሲኖዶሱ አባላት በውሳኔያቸው ተከፋፍለዋል

 • የዕርቀ ሰላሙ ልኡካን በሲኖዶሱ ውሳኔ ላይ የወሰዱት አቋም በመንሥኤነት ተጠቅሷል
 • ‹‹ይኾናል ብለን አንጠብቅም፤ ኾኖ ከተገኘ በጣም እንቃወማለን›› /አቡነ አትናቴዎስ/
 • ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ከሲኖዶሱ ስብሰባና ውሳኔዎች ራሳቸውን አግልለዋል
 • ዋና ጸሐፊው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ አልኾኑም
 • ማኅበረ ቅዱሳን በዕርቀ ሰላሙ እና በፓትርያሪክ ምርጫ አጣባቂኝ ውስጥ ገብቷል

የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ትላንት፣ ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አጽድቆ ምርጫውን የሚያስፈጽም 13 አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ሠይሟል፡፡ የኮሚቴው አባላት ከቅ/ሲኖዶስ አባላት፣ ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ መምሪያ ሓላፊዎች፣ ከገዳማት አበምኔቶች፣ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ ከመንፈሳውያን ማኅበራት እና ከታዋቂ ምእመናን ‹‹የተውጣጡ ናቸው›› ተብሏል፡፡

የኮሚቴውን መቋቋም ተከትሎ ለዕርቀ ሰላሙ ንግግሩ ወደ አሜሪካ የተላኩትና በቅ/ሲኖዶሱ የተሰጣቸውን ተጨማሪ የሰላም ተልእኮ ለመፈጸም በዚያው ከሚገኙት ሦስት ብፁዓን አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ÷ ትላንት ሌሊቱን ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ እና ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ጋራ በስልክ ተነጋግረዋል፡፡ በጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በደብዳቤ መላካቸውንና በዳላሱ የሰላም ጉባኤ በወጣው የጋራ መግለጫ መሠረት ዕርቀ ሰላሙን ከሚያደናቅፉ ተግባራት ለመቆጠብ ተስማምተው መፈረማቸውን ያስታወሱት ብፁዕነታቸው÷ ቅ/ሲኖዶሱ የልኡኩን ሪፖርት ሳያዳምጥና የሎሳንጀለሱን የሰላም ጉባኤ ውጤት ሳይጠብቅ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን እንደማይቀበሉት ማስታወቃቸው ተዘግቧል፡፡

ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ እና ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ

ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ እና ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ

‹‹ወደ አገራችን ተመልሰን ሰላም ለጠማው ሕዝብ መግለጫ እንሰጣለን፤›› ያሉት ብፁዕነታቸው÷ ውሳኔው የማይታረም ከኾነ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከሚያውክና ለሰላሟ ከማይጨነቅ ስብስብ ጋራ እንደማይቀጥሉ ለዐቃቤ መንበሩ አስጠንቅቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ይህንኑ አቋማቸውን ዛሬ፣ ታኅሣሥ 11 ቀን ማምሻውን በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በተደመጠው ቃላቸው በይፋ አሰምተዋል፡፡ ትላንት ሌሊቱን ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ጋራ የተደረገው የብፁዕነታቸው ውይይት በመግባባት የተካሄደ ቢኾንም ከዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ጋራ የተደረገው ግን ባለመግባባት መቋጨቱ ነው የተሰማው፡፡

ይኸው የዕርቀ ሰላም ልኡካኑ ፈጣን ማሳሰቢያ የፈጠረው ተጽዕኖ ይመስላል ለዛሬ ከሰዓት በኋላ በቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ እንዲሰጥ ተቀጥሮ  ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል

የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ የዜናው ምንጮች እንደገለጹት÷ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ለጋዜጣዊ መግለጫው ለመቅረብ ፈቃደኛ አልኾኑም፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋራ መጣላት አልፈልግም›› ያሉት ብፁዕነታቸው÷ በጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጋዜጣዊ ጉባኤ ላይ ‹‹አምስት ብለን ስድስት እንጂ ወደ አራት አንመለስም›› የሚለው ንግግራቸው ያስከተለባቸው ትችት ሕዝባዊ ድጋፉ እየተጠናከረ የመጣውን የዕርቀ ሰላም ጉባኤ የሚያደናቅፈውን የሲኖዶሱን ውሳኔ የመግለጥ ድፍረት አሳጥቷቸዋል፡፡ ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበር ይመለሱ የሚለውን እቃወማለኹ እንጂ ዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንዲሰጠው እፈልጋለኹ›› ያሉት ብፁዕነታቸው ጋዜጣዊ መግለጫውን እንዲሰጡ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ዳግመኛ ቢታዘዙም ፈቃደኛ ሳይኾኑ መቅረታቸው ተገልጧል፡፡ የሲኖዶሱን ውሳኔ ለሚዲያ አካላት የመግለጽ ሓላፊነት በብፁዕ ዋና ጸሐፊው ላይ ብቻ ሳይኾን በራሳቸው በዐቃቤ መንበሩ ላይም መታየቱ ውሳኔው በውጫዊ ጫና ስለመተላለፉ ተጨባጭ ማስረጃ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

‹‹የዕርቀ ሰላም ልኡኩን እንጠብቅ፤ ሪፖርቱን እንስማ›› የሚል የአቋም ልዩነት ቢኖራቸውም በአስመራጭ ኮሚቴው ውስጥ እንዲገቡ ከተደረጉት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ጋራ ተመሳሳይ አቋም የያዙት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ትላንት በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ ማጽደቅና በአስመራጭ ኮሚቴ ማቋቋም እንዲሁም በዛሬው ስብሰባ ሳይገኙ ቀርተዋል፤ ፊርማቸውን አለማስፈራቸው ታውቋል፡፡ እንደ ስብሰባው ምንጮች መረጃ አቡነ ጎርጎሬዎስ ብፁዕነታቸውን አግባብተው ለማስፈረም ጥረት ቢያደርጉም ‹‹ብንታገሥ ምን አለበት›› የሚሉት ብፁዕነታቸው በአቋማቸው በመጽናታቸው የዘለፋ ቃል ደርሶባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል በተቋማዊ መንገድ ያልወከለው የሥራ አመራር ጉባኤ አባሉ በአስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ የተካተተው ማኅበረ ቅዱሳን በፓትርያሪክ ምርጫ ሂደቱ በመሳተፍና ዕርቀ ሰላሙን በማስቀደም መካከል አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተገልጧል፡፡ የቀጣዩ የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ውጤት እስኪታወቅ አስመራጭ ኮሚቴው እንዳይቋቋም ዐቃቤ መንበሩንና ሌሎቹንም ብፁዓን አባቶች ለማግባባት በማኅበሩ አመራሮች በኩል ጥረት የተዘገበ ቢኾንም ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንና አንዳንድ ጳጳሳት ከመንግሥት ጎን ኾነው ቤተ ክርስቲያኗን እየከፋፈሏት ነው›› በመንበረ ፓትርያሪኩ ዙሪያ ተበትኖ ማደሩ ተመልክቷል፡፡ በማኅበሩ በኩል በጉዳዩ ላይ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም፡፡

በደረሰን መረጃ መሠረት የኮሚቴው አባላት ስም ዝርዝር፡-

ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

1)  ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ 2) ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ 3) ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ 4) ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ናቸው፡፡

ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ሁለት መምሪያዎች፤

5) ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ – የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ዋና ሓላፊ

6) መጋቤ ምስጢር ዓምደ ብርሃን – የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሓላፊ

ከታላላቅ ገዳማት እና አድባራት

7) ፀባቴ አባ ኀይለ መስቀል ውቤ – የደብረ ሊባኖስ ገዳም አበምኔት

8) ንቡረ እድ አባ ዕዝራ – የአኵስም ጽዮን ንቡረ እድ

ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

9) ዲያቆን ኄኖክ ዐሥራት

ከማኅበረ ቅዱሳን

10) አቶ ባያብል ሙላቴ

ከታዋቂ ምእመናን

11) አቶ ዓለማየሁ ተስፋዬ – ከኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት

12) ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድ

13) አቶ ታቦር ገረሱ ናቸው፡፡

Advertisements

7 thoughts on “የቅ/ሲኖዶሱ አባላት በውሳኔያቸው ተከፋፍለዋል

 1. Hello December 20, 2012 at 10:00 pm Reply

  Thanks for you Info HaraZeTewahido. Can you put the link for Abune Atnathewos’s interview in VOA?

 2. haratewahido December 20, 2012 at 10:16 pm Reply

  Thank you for your recommendation, we put it therein the content.

 3. geezonline December 21, 2012 at 1:54 am Reply

  [audio src="http://www.voanews.com/mp3/voa/africa/amha/amha1800aTHU.mp3" /]

 4. Ytb December 21, 2012 at 5:44 am Reply

  ኦርቶዶክሳዊነት ወዴት ገባ? አቦ አቦ መባልን መሽሽ ወዴት ገባ? ራስን ከክብር ከስልጣን ማራቅ ወዴት ገባ? ወዴት ገባ? ስለልጆቹስ የሚገደው አባት ወዴት ጠፋ? ስለምእመናን ምቾት እድሜህን ሁሉ በጉስቁልና የኖርክ ዮሃንስ አፈወርቅ ሆይ እስኪ ተናገርና እንስማህ? ስለእርቅ ምን ያክል ዋጋ ትከፍል ነበር? ስለምእመናንስ አንድነት ምን ያክል ዋጋ ትከፍል ነበር? ስለክርስትናስ ክብር ምን ያክል ዋጋ ትከፍል ነበር? አባታችን ተናገረንና እስኪ እንፅናና ፤ በእኛ ቤት ግን ከእርቅ ይልቅ የስልጣን ጥማቱ አይሏል ፡ ከምእመናን አንድነት ይልቅ የራስን ሹመት ማዳበር አይሏል ፡ ከክርስትናው ክብር ይልቅ የቤተመንግስቱ ክብር በልጧል ፤ በእኛ ቤት እንዲህ ሆኗል ፤ ያ ስልጣንን ስለአለመፈለግ ወደገዳም ሽሽቱ ኦርቶዶክሳዊው ትህትና ቀርቷል ፡ ሁሉም ራሱን ይመርጣል ፡ ሁሉም ምረጡኝ ይላል ፡ ሁሉም ድጋፍን ይሻል ፤

  ፅኑ ሰማእት አቡነ ጴጥሮስ አባታችን ሆይ ፦ እስኪ የክርስትናውን ዋና አላማ አስተምረን ፤ በመንግስት እጅ ጥምዘዛ ክርስቶስ ይካዳል እንዴ? በክፉ የዲያቢሎስ ሽንገላ ክርስትና ይላላል እንዴ? አለማዊ ምቾትና ኦርቶዶክሳዊው መምህርነት በምን ይዛመዳሉ? አባታችን ሆይ ፦ የክርስቶስን መስቀል ይዞ ከእርቅ ሽሽቶ እንዴት ይሆናል? እረኛ ሆኖ ሳለ በጎች ሲበተኑ መተባበር ፡ በጎች ሲጠፉ አለመፈለግ እንዴት ይስማማል? ሰላማዊ ክርስቶስን እየሰበኩ ከሰላም መራቅ ምን ይባላል? ትሁት ክርስቶስን እየሰበኩ ራስን መሾም ምን ይባላል? አባታችን ፦ ተመሳስሎ ስለመኖርማ ከፋሽስት ክብር ቀርቦለወት አለነበረምን? ክርስቶስን ስለማክበር የእርስወን ክብር ሽሿት እንጂ ፤ ስልጣንስ ቀርቦለወት አልነበረምን? መደለያ ቀርቦለወት አልነበረምን? በልብወ ያለው የክርስቶስ ፅናት ፡ የምእመናን ፍቅር ግድ አለወት እንጂ ፤ አባታችን ፦ ዛሬ ግን ይህን አናይም ፤ ለእኛ ለምእመናን አብነት ሊሆን የሚወድ ትሁት አባት ራቀብን ፤ ሹመት ሽልማትን ንቆ ለክርስትናው ዘብ የሚቆም እውነተኛ እረኛ ማየት አልቻልንም ፤ የቤተ መንግስት መደለያ የማያጓጓው ፡ የቤተ መንግስት ቁጣ የማያስበረግገው ፅኑ አባት ማየት አልቻልንም፡፡

  “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” ሐዋ.20:28

 5. eth December 21, 2012 at 9:43 am Reply

  ሐራ ተዋህዶ አገልግሎታችሁ ለቤተ ክርስቲያን የቆማችሁ ይመስላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወቅታዊ መረጃዎችንም ማግኘት የምትችሉ መሆኑንም ተገንዝበናል፡፡ ስለዚህ የሚደረጉ መሰናክሎችንና ዝግጅቶችን በሙሉ ለምዕመናን በሚገባ ሁኔታና አዘጋገብ በማቅረብ ትብብራችሁን ታደርጉ ዘንድ እናሳስባለን፡፡
  የሚወጡ መረጃዎች ግን የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ለማምጣት መሆናቸው ጥንቃቄ ቢደረግበት አምላካችን በጸጋ የሚቀበለው አገልግሎት ይሆናል፡፡

 6. Fil December 21, 2012 at 5:56 pm Reply

  በዚህ ለአንድነቱ መምጣት ወሳኝ በሆነ ስዓት ፓትርያርክ ለመምረጥ የሚደረገው ሩጫ ቤተ ክርስቲያንን ለሚያፈርሱ ሰዎች ዶማ ከማቀበል አልፎ ከሚያፈርሱት ጎን ተሰልፎ ማፍረስ ነው።

 7. Mebrat Aklilu December 22, 2012 at 1:28 am Reply

  በእውነቱ ከሆነ ይህ እጅግ እጅግ አሳዛኝ እና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸለምተኛ ጊዜ ሊባል የሚችል ነው፡፡ አበው ሊቃነ ጳጳሳት (መላዉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት) በዚህች ወሳኝ ወቅት መንጋውን ከመበተን አደጋ የመታደግ ታላቅ ኃላፊነት ያለው በእናነት ላይ ነው እና እባካችሁ ከምንም ከማንም በላይ እናንተን ለዚህች ቀን እግዚአብሔር እንደሾማችሁ ፤ በመልካም ተጋድሎ ያለፉትን አበው ትውልድ ልትመስሏቸው ይገባል፡፡ እኛም ምዕመናን ከቅዱሳን አበው መልካም ተጋድሎ ጎን በጸሎትና ኃሳባችንን በመለገስ ብሎም በያለንበት ማድረግ የምንችላቸውን በጎ ተጽዕኖዎች ከማድረግ አንቆጠብ፡፡
  ክፉው ስጋት ተወግዶ መልካሙን ጊዜ እንዲመጠልን እግዚአብሔር ይርዳን ! እመብርሃን የአዳም ተስፋው ቤተክርስቲያናችንን እና ህዝቦቿን ታደጊን ፡፡ አሜን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: