ዕጣው በምርጫ ለመተካቱ መንግሥት በአባቶች ላይ የፈጠረው ጫና ጎልቶ እየተጠቀሰ ነው

  • ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ ለቪ.ኦ.ኤ በሰጡት ቃለ ምልልስ በርካታ አባቶች ተረብሸዋል
  • የውጭ ዜግነታቸውን ስለሚተዉ ጳጳሳት አንቀጽ ተጨምሯል
  • የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ቁጥር ወደ 13 ዝቅ ተደርጓል

መንግሥት በተስፋ ከሚጠበቀው የዕርቀ ሰላም ንግግር ይልቅ ለቀጣዩ ፓትርያሪክ ምርጫ ትኩረት እንደሚሰጥ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የዕርቀ ሰላም ንግግሩ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት በ‹‹ፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ›› ሳቢያ በተፈጠረው የሚዲያ ምልልስ÷ ዐቃቤ መንበሩ ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የመመለስ ኹኔታ በቀጭኑ ሽቦ በታዘዙት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ እንዲያስታወቁ የተደረገበት መንገድ አንድ አስረጅ ነው፡፡ ከዚያም ወዲህ ግዘፍ ነስቶ መልክ አውጥቶ የታየው የመንግሥት እጅ ደግሞ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በፓትርያሪክ ሥያሜ ሂደቱ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተመራጩ ፓትርያሪክ በዕጣ ስለሚለይበት አሠራር አንቀጽ ወስኖ ካለፈ በኋላ፣ የዕጣው ውሳኔ ተገልብጦ አላስፈላጊ የውጭ ተጽዕኖ ለማሳደር (ለማጭበርበር) የበለጠ ዕድል በሚሰጠው በምርጫ ሥርዐት ሙሉ በሙሉ እንዲተካ መደረጉ ነው፡፡

በአግባቡ የተደራጀ መልክ ይዞ፣ በመንበረ ፓትርያሪኩ በተሰማሩ የመንግሥት ሰዎች ምክር እየተመራ ተደርጓል በተባለው በዚህ የዕጣ ተቃዋሚ ብፁዓን አባቶች እንቅስቃሴ÷ የዕጣውን አሠራር ደግፈው የተሟገቱ አባቶች አቋማቸውን እንዲቀይሩ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጫና ተደርጎባቸዋል፡፡ ‹‹መንግሥት በካርድ ይመረጥ የለም ወይ፤ እኛ ምንድን ነን?›› እስከማለት ደርሰው የዕጣ ተቃዋሚዎቹን ቡድን የሚመሩት፣ ቡድኑን መምራት ብቻ ሳይኾን የዕጣ አሠራርን የሚደግፉ አባቶችን እየለዩ የሚጠቁሙት ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ ቀዳሚው ናቸው፡፡

ከእርሳቸውም ጋራ በቀደመው ዘገባችን ከጠቀስናቸው ውጭ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሚገኙ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እና ብፁዕ አቡነ አብርሃም ስለተለያየ ምክንያት ዕጣውን በመቃወም የማሳመን (የውተውታ) ሥራ ሠርተዋል፡፡ በውተወታው ጫና የተነሣ ቢያንስ በምርጫው እኵል ድምፅ የሚያገኙ አባቶች በዕጣ የሚለዩበት አንቀጽ እንዲወሰን የተሟገቱ እንደ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ያሉ አባቶች ሳይቀር በመጨረሻ ወደ ዕጣ ተቃዋሚዎች ጎራ መቀላቀላቸው ታውቋል፡፡

የቀደመው የዕጣው ውሳኔ ተገልብጦ በምርጫ ከመተካቱ ሁለት ቀን አስቀድሞ ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 5 ቀን 2005 ዓ.ም፣ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት የዕርቀ ሰላሙን የጋራ መግለጫ አስመልክቶ ካቀረባቸው ተወያዮች አንዱ ከኾኑት ዲ/ን ኢንጅነር ዓባይነህ ካሴ ጋራ የተካሄደውን ቃለ ምልልስ ተከትሎ የተስተዋለው መረበሽ፣ ለዕጣው ተቃዋሚዎችና ለመንግሥት ጫና ምቹ ኹኔታ የተፈጠረበት ሌላው ሰበብ እንደኾነ ተዘግቧል፡፡

ዲ/ን ዓባይነህ በቃለ ምልልሳቸው ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ወደ መንበራቸው መመለስ የተጣሰውን ቀኖና ሊያስተካክለው ይችላል›› ማለታቸው ጥቂት በማይባሉ ብፁዓን አባቶች ዘንድ መረበሽን ፈጥሯል ተብሏል፡፡

መረበሹን ያመጣው÷ ‹‹የዲ/ን ዓባይነህ የግል አስተያየት የማኅበረ ቅዱሳን ይፋዊ አቋም ነው›› ከሚል መነሻ የተወሰደው የሊቃነ ጳጳሳቱ አረዳድና ግንዛቤ ነው ተብሏል፡፡ ከእኒህም ለመጥቀስ ያህል÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን አቡነ መርቆሬዎስን መልሶ በመንበሩ ለማስቀመጥ ሕዝብን ሊያነሣሣብን/ሊቀሰቅስብን ነው፤ በእኛ በኩል የቀኖና ጥሰት የሚባል ነገር የለም፤ በእኛ በኩል የተጣሰ ቀኖና አለ ከተባለ የእኛ የጵጵስና ሹመት ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፤ በስደት ባሉት አባቶች ላይ የተላለፈው ውግዘት አልተነሣም፤ ውግዘቱ ባልተነሣበት ኹኔታ ዲ/ን ዓባይነህ ሁለቱ ወገኖች የአንድነት አገልግሎት የፈጸሙበትን ኹኔታ ታላቅ ርምጃ ነው ብሎ መናገር አልነበረበትም፤›› የሚሉትና የመሳሰሉት አረዳዶችና ግንዛቤዎች ናቸው ተብሏል፡፡

የዕጣውን አሠራር በተመለከተ ቀደም ብሎ የተላለፈውን የሲኖዶሱን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርጫ የለወጠው ጠንካራ እንቅስቃሴ የተጀመረው÷ የሬዲዮው ውይይት በተላለፈ ማግሥት – እሑድ፣ ታኅሣሥ 6 – በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ በሚኖሩ አባቶች ላይ የተደረገው የጳጳሳት ቡድን የተደራጀ ዘመቻ መኾኑ ተዘግቧል፡፡ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ዕርቀ ሰላሙን በመደገፍ ስም አቡነ መርቆሬዎስን ወደ መንበር ለመመለስ ሕዝብን ሊያነሣሣብን ነው፤ በዕርቀ ሰላሙና አቡነ መርቆሬዎስን ወደ መንበር በመመለስ መካከል በይፋና በግል የተምታታ መረጃ እየሰጠ ሊከፋፍለን ነው›› በሚሉ ማመኻኛዎች የታገዘው ይኸው የተደራጀ እንቅስቃሴ በዋናነት የተመራው ቀደም ሲል በተጠቀሱት ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት – አቡነ ጎርጎሬዎስ፣ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ አቡነ ሳዊሮስ – ነው፡፡

‹‹የገዢው ግንባር አባላት ናቸው፤ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ አቋም የሚይዙት ድርጅታዊ መመሪያ እየተቀበሉ ነው›› በሚባሉት በእኒህ ሊቃነ ጳጳሳት አስተባባሪነት የተካሄደው ይኸው እንቅስቃሴ÷ የዲ/ን ዓባይነህን የሬዲዮ ቃለ ምልልስ ሰበብ በማድረግ ይጠናከር እንጂ ዋና ግቡ በእንጥልጥል የቀሩ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡን ጉዳዮች በቶሎ ጨርሶና አስመራጭ ኮሚቴውን በተፋጠነ ኹኔታ ሠይሞ የምርጫ ዝግጅቱን መጀመር ማእከል ያደረገ ነበር ተብሏል፡፡

የእንቅስቃሴው ብርቱ ግፊት የፈጠረው ጫና ‹‹ወደ አሜሪካ ለዕርቀ ሰላም ንግግር የላክናቸው ልኡካን ተመልሰው ሪፖርታቸውን ማዳመጥና ስለ ወርኀ ጥር የሎሳንጀለስ የሰላም ጉባኤ መምከር ይገባናል፤ ልኡካኑ በምርጫ ሕጉ ላይ ሐሳባቸውን የመስጠት፣ በአስመራጭ ኮሚቴው ውስጥም የመሳተፍ ዕድላቸውን ሊነፈጉ አይገባም፤ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየም የሰላም ጉባኤውን የጋራ ስምምነት ይጥሳል፤ ልኡካኑ የፈረሙባቸውን ስምምነቶች የሚፃረሩ ተግባራት መፈጸም አይገባንም፤›› በሚል ትዕግሥት እንዲደረግና የሰላም በር እንዳይዘጋ ሲወተውቱ የነበሩ አባቶች አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ ኾነዋል፡፡

በዲ/ን ዓባይነህ የቪ.ኦ.ኤ ቃለ ምልልስ ሰበብነት በጦዘውና እንደ እውነቱ ከኾነ ከፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ ጋራ ምንም ግንኙነት ሊኖረው በማይችለው ጉዳይ በተጠናከረው ግፊት የማኅበረ ቅዱሳን አመራሮችም ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጀምሮ ለሊቃነ ጳጳሳቱ የበኩላቸውን ማብራሪያ ለመስጠት መጣራቸው ነው የሚነገረው – ‹‹አትከፋፍሉን›› ከሚለው ኀይለ ቃል በቀር ያገኙት አጥጋቢ ነገር ባይኖርም፡፡ ማኅበሩ በስብሰባ አዳራሽ ስለ ገዳማት ያዘጋጀው ዐውደ ጉባኤ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ከተገኙት ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ አቡነ ጎርጎሬዎስ ሲናገሩ÷ ‹‹እንቅደም እንቅደም አትበሉ፤ አባቶችን አስቀድማችኹ እንከተል ስትሉ አብረን መሥራት እንችላለን›› ማለታቸው ውጥረቱን የሚያስተረጉም ኾኖ ተጥቅሷል፡፡

ከዚህም በተያያዘ በአንዳንዶቹ የማኅበሩ አመራር አባላት ዘንድ ዲ/ን ዓባይነህ በማኅበሩ ውስጥ ያላቸውን ሓላፊነት ጠቅሰው በመናገራቸው አንዳች ርምጃ መውሰድ ማኅበሩ በዕርቀ ሰላሙ እና በአቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበር መመለስ መካከል ፈጥሮታል የሚባለውን ውዥንብር ለማጥራት የሚረዳ መስሎ ታይቷቸዋል፡፡ የአራተኛውን ፓትርያሪክ ወደ መንበር መመለስ የተጣሰውን ቀኖና ለማረም (የቀኖና ጥሰት ስለ መኖሩ የተለያዩ አቋሞች ቢታዩም) እንደ አንድ አማራጭ ብቻ ያቀረቡት ዲ/ን ዓባይነህ÷ በቀጣይነት ያቀረቧቸውን ቀሪ ሁለት አካሄዶች (የእንደራሴ መሠየም አልያም በአንድነት ቀጣዩን ፓትርያሪክ መሾም) ለማየት የፈለገ ወገን አለመታየቱ ግን አሳዛኝ ነው፡፡

በእሑድ ሰንበት በተደረገው እንቅስቃሴ መሠረት በቀጣዩ ቀን ሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በተደረገው የሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በቀዳሚነት በማኅበረ ቅዱሳን የሚደገፈው የዕጣ አሠራር ውሳኔ ተሽሮ በምርጫ እንዲተካ ተደረገ፡፡ ‹‹የብጥብጥ ያህል በተካሄደው የቀትር በፊት የሲኖዶሱ ውሎ ውሳኔው ወደ ምርጫ ሥርዐት እንዲገለበጥ አደረጉ፤›› ይላሉ የስብሰባው ምንጮች፡፡

Advertisements

One thought on “ዕጣው በምርጫ ለመተካቱ መንግሥት በአባቶች ላይ የፈጠረው ጫና ጎልቶ እየተጠቀሰ ነው

  1. Hello December 21, 2012 at 5:50 pm Reply

    Please put the link of Dn. Abayneh’s interview in VOA.
    When you do a reference for some sources, please put the address for the source (provided that, If you know it) . This would increase the reputation of the news and the blog too.

    May God give us Unity!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: