ለዕርቀ ሰላሙ ሥምረት ሕዝበ ክርስቲያኑ የማንንም ተጽዕኖ ሳይፈራ በአንድነት እንዲንቀሳቀስ ጥሪ ቀረበ

 • ‹‹ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት የመነኰሳት ብቻ አይደለችም፤ ምእመናን እንደ ምእመንነታቸው ሊደመጡ ይገባል፡፡››
 • ‹‹ሁለቱም አካላት በደልንና ቅድመ ኹኔታን ትተው፣ ፍቅርን አስቀድመው፣ ለተጣሰው ቀኖና የጋራ ሓላፊነት ወስደው አንድነታቸውን ከመለሱ በኋላ ዐቃቤ መንበር መርጠው ፓትርያሪክ ለመሾም ምንም የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡››

በሰሜን አሜሪካ በስደት ላይ ከሚገኙት ብፁዓን አባቶች ጋራ ሲካሄድ የቆየው የዕርቀ ሰላም ንግግር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት÷ የቤተ ክርስቲያን አንድ አካል የኾኑት ሀገር ውስጥም በውጭም የሚኖሩ ምእመናንና ምእመናን በጎ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚያስችል፣ መግባባት የሰፈነበት የተግባር እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡ የቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም የአባቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም የሚል መልእክት የተላለፈበት ይኸው ጥሪ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናንና ምእመናት በሚኖሩባቸው አካባቢዎችና በሚያገለግሉባቸው መድረኰች የዕርቀ ሰላሙ ሂደት ይሠምር ዘንድ ከጸሎት ባሻገር ጠንካራ ተጽዕኖ ለመፍጠር በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የማንንም አካል ጫና መስጋት እንደማይገባቸው ጠይቋል፡፡

Dn. Eng Abayneh

ዲያቆን ኢንጅነር ዓባይነህ ካሴ

የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ምሽት፣ ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም፣ በዳላስ ቴክሳስ ስለወጣው የዕርቀ ሰላም ተነጋጋሪዎች መግለጫና በቤተ ክርስቲያን የሰላም ኹኔታ ላይ አስተያየታቸው ከሰጡ ሁለት ተጠያቂዎች አንዱ የኾኑት በማኅበረ ቅዱሳን የኤዲቶሪያል ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዲያቆን ኢንጅነር ዓባይነህ ካሴ÷ የዳላሱ ውይይት ሂደትና ውጤት ተነጋጋሪ ወገኖች የተስማሙባቸውንና ያልተስማሙባቸውን ጉዳዮች በአንድ መድረክ ለይተው፣ በሰነድ አስደግፈው መግለጫ ያወጡበት በመኾኑ ካለፉት ጉባኤያት ይልቅ የተሻለ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ መግለጫው በይዘቱ መጪው ጉባኤ በተስፋ እንዲጠበቅ በማድረግ ለሰላም ተጨማሪ ዕድል የሰጠ፣ ‹‹አምስት ብለን ስድስት እንጂ ወደ አራት አንለመስም›› በሚል በቅዱስ ሲኖዶሱ ጸሐፊ በተሰጠው መግለጫ መሠረት ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ሹመት ከሚደረገው ዝግጅት ታቅቦ ለመቆየት ባለው አስተዋፅኦ ሌሎችንም አዲስ ሐሳቦች ለማጤንም በሩን የከፈተ በመኾኑ ‹‹እመርታ የታየበት ነው›› ብለዋል፡፡

የዳላሱ ውይይት ከቀደመው የአሪዞና ውይይት የተለየ የሰላምና አንድነት አዝማሚያ እንዳልታየበት በመጥቀስ ከጥር 16 – 18 ቀን 2005 ዓ.ም በካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ እንዲካሄድ የተያዘው ቀጠሮ ምን ዐይነት የተጨበጠ ተስፋ እንደተሰነቀበት የተጠየቁት ዲ/ን ዓባይነህ÷ እስከ ጥር አጋማሽ ድረስ ያለውን ከአንድ ወር ያላነሰ ጊዜ ከግምት በማስገባት በሚከናወኑ ‹‹ተኣምራዊ ጣልቃ ገብነቶች›› ይኹኑ ‹‹ሰብአዊ ጥረቶች›› ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም የሚበጅ አንዳች ውጤት ሊገኝ እንደሚችል ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በዲ/ን ዓባይነህ ተስፋ እስከ ቀጣዩ ጉባኤ መዳረሻ የተኣምራት አምላክ የኾነው እግዚአብሔር÷ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ ስምምነት ሊደረስበት ይችላል፤ ምእመናንም የጋራ እንቀስቃሴያቸውን አጠናክረው ተጽዕኗቸውን ለማሳደር ያስችላቸዋል፡፡ ‹‹በአገር ቤት ፓትርያሪክ መርጦ ለድርድር ወደ ሎሳንጀለስ መሄድ የማይኾን ነገር ነው፤›› ያሉት ዲ/ን ዓባይነህ÷ በሁለቱም ወገኖች በጋራ የተጣሰውን ቀኖና ሊመልሰው የሚችለው በዋናነት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ‹‹ወደ መንበር መመለስ ነው›› ብለዋል፡፡

የአምስተኛውን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ኻያ የፕትርክና ዓመታት በመጥቀስ አራተኛውን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ወደ መንበር በመመለስ ላይ ቴክኒካል ጥያቄ ስለሚያነሡ ወገኖች የዲ/ን ዓባይነህ ምላሽ÷ ‹‹ፍቅር አመክንዮ ወይም ታሪክ ሳይኾን በደልን መተው፤ ጽሕፈት፣ ስብከትና ንግግር ሳይኾን የክርስቶስን ኣሰረ ፍኖት ተከትሎ ሰላምን በአርኣያነት የመመሥረትን ተግባር ብቻ የሚሻ ነው፤›› የሚል ነው፡፡

ወደ መንበር የመመለሱ ኹኔታ ተቀባይነት ባያገኝ እንኳ ‹‹ፍርድ ከእግዚአብሔር ነው›› ብለው ለ21 ዓመታት በአርምሞ የተወሰኑት ራሳቸው አቡነ መርቆሬዎስ÷ ቤተ ክርስቲያንን ለመጥቀም ከማሰብ ያለማንም ተጽዕኖ በራሳቸው ድምፅ መንበሩን በፈቃዳቸው እንደለቀቁ አስታውቀው በሚደረስበት ስምምነት መሠረት መንበሩ በእንደራሴ ተጠብቆ ሊቆይ የሚችልበት ሥርዐት እንዳለም ዲ/ን ዓባይነህ አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በተጣሰበት ወቅት የነበሩ ወገኖች በዚህም በዚያም መኖራቸውን  ዲ/ን ዓባይነህ አስታውሰው፣ ሁሉም ወገኖች በደልንና ቅድመ ኹኔታን ትተው፣ ፍቅርን አስቀድመው፣ በጋራ ለጣሱት ቀኖና የጋራ ሓላፊነት ወስደው አንድነታቸውን ከመለሱ በኋላ ‹‹ዐቃቤ መንበር መርጠው ፓትርያሪክ ለመሾም ምንም የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡››

ፍቅርን በመመሥረትና ሰላምን ከማጽናት አኳያ ሁለቱም ወገኖች ትልቁን ርምጃ የተራመዱበት ኹኔታ በዳላሱ ውይይት መታየቱ ከዚህ በኋላ የሚያዳግት ነገር ይኖራል ብለው እንዳይጠብቁ እንዳረጋቸው ሰባኬ ወንጌሉ ለሬዲዮው ተናግረዋል፡፡ ታላቁ ርምጃ በውግዘት የተለያዩት አባቶች አብረው ጸሎተ ኪዳን ማድረሳቸው፣ በጸሎተ ቅዳሴው መተባበራቸውና ሥጋ ወደሙን መሠዋታቸው ነው፡፡ ይህ የአንድነት አገልግሎት በውግዘት በተለያዩ አባቶች መካከል ‹‹እግዚአብሔር ይፍታሕ›› ሳይባባሉ ሊፈጸም ስለማይችል ውግዘቱ ለመፈታቱ አስረጅ ነው -በዲያቆን ዓባይነህ እምነት፡፡ ቀኖናው በቀኖና ተሻሽሎ ውግዘቱ ቀድሞ ተነሥቷል፤ ከሁለቱም ወገኖች የሚጠበቀው ጉዳይ ‹‹ለእግዚአብሔር ሕግ፣ ለቤተ ክርስቲያን ቀኖና መገዛት ነው፡፡››

በሁለቱም ወገኖች የሚነሣው የመንበር ጥያቄ ቀደም ሲል በተገለጹት አማራጮች የሚታይበት አገባብ እንደተጠበቀ ኾኖ ከዚያም በፊትና በላይ ግን ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም!!›› የሚለው ጥያቄ በአራቱም ማእዝናት የሚገኙ ምእመናን አሰምተው የሚጮኹለት ጉዳይ በመኾኑ ጩኸታቸው ሊደመጥ እንደሚገባ ዲ/ን ዓባይነህ በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡ ‹‹ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳትና የመነኰሳት ብቻ አይደለችም›› ያሉት ሰባኬ ወንጌሉ ምእመናን እንደ ምእመንነታቸው ሊደመጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅ፣ በምዕራብ ያለው ሕዝበ ክርስቲያን ‹‹እገሌ አይምራን ወይም እገሌ ይምራን›› ሳይኾን ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንዲሰጥ በሚማፀንበትና ተማኅፅኖውንም ከቀን ወደ ቀን በልዩ ልዩ መንገዶች እየገፋበት ባለበት ወቅት፣ ‹‹ብፁዓን አባቶቻችን እገሌ ይኹን፣ እገሌ አይኹን የሚሉት ማንን ሊመሩ ነው?›› በማለት ዲ/ን ዓባይነህ ይጠይቃሉ፡፡ ዲ/ን ኢንጅነር ዓባይነህ በአገር ቤት ይኹን በባሕር ማዶ የሚገኘው ምእመን ዕርቀ ሰላሙ የአባቶች ጉዳይ ነው ብሎ መቀመጥ እንደማይገባው ያስጠነቅቃሉ፡፡ መንቀሳቀስ፣ መነጋገር፣ መግባባት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ፡፡

ይህም ሲባል ምእመኑ ዕርቀ ሰላሙን በተመለከተ ማድረግ የሚገባው እንቅስቃሴ የአቤቱታ ማሰባሰቢያ ደብዳቤዎችንና ፊርማዎችን ለአባቶች ከማቅረብ አልያም የሕዝብ አስተያየት ማሰባሰቢያ ጥናቶችን ከመተንተን ያለፈ ሊኾን እንደሚገባው የሚያመለክት ነው፡፡ ሩቅ ሳንሄድ በ2005 ዓ.ም ጥቅምት ምልአተ ጉባኤ ‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› በሚል በተለያዩ ወገኖች የቀረቡ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የምእመናን የተማኅፅኖ ፊርማዎች የተሰባሰቡባቸውና ከምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባ መጀመር በፊት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የደረሱ የተማኅፅኖ ደብዳቤዎች ከጠረጴዛው ላይ ሳይነሡ ስብሰባው ያበቃበትን ቸልተኝነት መጥቀስ ይበቃል፡፡

የስብሰባው ምንጮች በወቅቱ እንደተናገሩት÷ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ የተማኅፅኖ ደብዳቤዎቹን ሰብስበው አንሥተው ወደላይ እያሳዩ ቢያንስ መግለጫዎቻቸው እንዲነበብ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ የተደረገበት ኹኔታ÷ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ሲባል ከተማኅፅኖ ደብዳቤና ከሕዝብ አስተያየት ትንተናዎች በላይ ጠንካራ ነገር ግን በጎ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል የአገልጋዮችና ምእመናን ንቅናቄ ማቀጣጠል ለጥያቄ የማይቀርብ፣ ቀጠሮም ሊሰጠው የማይገባ መኾኑን ነው፡፡

ዲያቆን ኢንጅነር ዓባይነህ ካሴ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ እንደገለጹት÷ መግባባት በተመላበት መንፈስ በሚደረግ መነጋገርና መንቀሳቀስ የሚካሄደው የአገልጋዮችና ምእመናን ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ከማንም ተጽዕኖ ይመጣል ብሎ መስጋት ተገቢ አይደለም፡፡ ዕርቀ ሰላሙ የሥልጣን ጥማት የተጠናወታቸው የውስጥ ቡድኖችና ከተለያየ ዓላማ በመነሣት እኒህን ቡድኖች የሚያግዙ የውጭ አካላት የሚፈጥሩት መሰናክል እንዳለበት በግልጽ የታየ ነው፡፡ ኾኖም ዲ/ን ዓባይነህ እንዳሉት መስጋት አያስፈልግም፡፡ ለምን? ጥያቄው የቤተ ክርስቲያን ሰላም ነውና ንቅናቄውም ሰላማዊ ነው፤ ጥያቄው የቤተ ክርስቲያን አንድነት ጉዳይ ነውና ንቅናቄውም ከነውጥ የጸዳ ነገር ግን አገልጋዩ በአገልጋይነቱ ምእመኑም በምእመንነቱ የድርሻቸውን በመግባባት፣ በመነጋገር የሚወጡበት፣ በከፍተኛ አመራሩ ላይ ጠንካራና በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩበት የተግባር ጥያቄ ነው፡፡

ዲ/ን ዓባይነህ በውይይታቸው ማሳረጊያ፣ ‹‹ከቤተ ክርስቲያን የሚቀድም ምንም ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለወርኀ ጥሩ የሎሳንጀለሱ ወሳኝ የሰላም ጉባኤ በርትቶ እንዲጸልይ ተማፅነዋል፡፡ ወርኀ ጥር ሩቅ አይደለም፡፡ በመኾኑም በዲ/ን ዓባይነህ አባባል ‹‹ንግግርን፣ ስብከትን፣ ጽሑፍን ብቻ ሳይኾን ማድረግን የግድ ለሚለው›› የሎሳንጀለሱ የሰላምና ዕርቅ ጉባኤ በጎና ትርጉም ያለው ጠንካራ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ እንቅስቀሴዎችን ለማካሄድ እንነሣ! ዛሬውኑ! አሁኑኑ! ! !

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ከኅዳር 25 – 30 ቀን 2005 ዓ.ም (December 5 – 9, 2012) በዳላስ፣ ቴክሳስ ለሦስተኛ ጊዜ ባዘጋጀው ጉባኤ አበው ላይ ከኢትዮጵያ እና ከሰሜን አሜሪካ በቅዱስ ሲኖዶስ ተሠይመን በተላክን የሰላም ልኡካን የተሰጠ የጋራ መግለጫ

Advertisements

11 thoughts on “ለዕርቀ ሰላሙ ሥምረት ሕዝበ ክርስቲያኑ የማንንም ተጽዕኖ ሳይፈራ በአንድነት እንዲንቀሳቀስ ጥሪ ቀረበ

 1. ecabod Tesfaye December 19, 2012 at 7:00 am Reply

  ok tell us what to do ? i mean you have explained that we are expected to express our feeling but you didn’t show us the way. organize us and let us do something to keep our church .specially those of us who are in Ethiopia are doing nothing other than posting on social networks so pls do smttttttttt.

 2. muse December 19, 2012 at 11:12 am Reply

  4ኛው ፓትርያሪክ ለመመለስ ታቅዶ ከሆነ በጣም ስህተት ነው እሳቸው በኣገር ክህደት ሊከሰሱ የሚገባቸው ወነጀለኛ ናቸው! ካገራችን ቀንደኛ ጠላት ከሆነው የኤርትራ መንግስት በመተባበር ጦርነት ያወጁ ስለ ሆነ ነው!

 3. Getnet Mesfin December 19, 2012 at 12:32 pm Reply

  @Muse Who you are? Where are you from?

 4. demeke December 20, 2012 at 5:36 am Reply

  Amlake kidusan cher wore yaseman!!!

 5. my God December 20, 2012 at 11:29 am Reply

  ቀፎ ! ከሀዲስ አንተ ስብከትህ በሙሉ በመንግስት የወያኔ መጽሐፍ የተጠመቅህ ስለሆንክ መንግስት በየሚዲያውና በየፍርድ ቤቱ የሚያነሳው የሀገር ክህደት ወንጀል ማለትህ አይገርምም፡፡ብዙ ልታናግረኝ ነው እንጂ ጠፍቶህ ከሆነ ጠይቅ ዘላለም ደንቁረህ ከምትቀር እወቅ ተረዳ፡፡

 6. Kostentinos zewdie December 21, 2012 at 10:41 am Reply

  Hara zetewahido Be organized ,Please continue in this manner!

 7. k/maryam December 21, 2012 at 1:20 pm Reply

  kedmiya labet kerestiyan andente enaseb lylawe terf new E/r yerdan

 8. […] ዓባይነህን ያነጋገሩ ሲኾን በዛሬው ዕለት ማምሻውን ደግሞ ዲ/ን ዓባይነህ ለቪ.ኦ.ኤ የሰጡት ቃለ ምልልስ ማኅበሩን እንደማይወክልና የግላቸው መኾኑን በድረ ገጹ […]

 9. […] ዓባይነህን ያነጋገሩ ሲኾን በዛሬው ዕለት ማምሻውን ደግሞ ዲ/ን ዓባይነህ ለቪ.ኦ.ኤ የሰጡት ቃለ ምልልስ ማኅበሩን እንደማይወክልና የግላቸው መኾኑን በድረ […]

 10. […] ዓባይነህን ያነጋገሩ ሲኾን በዛሬው ዕለት ማምሻውን ደግሞ ዲ/ን ዓባይነህ ለቪ.ኦ.ኤ የሰጡት ቃለ ምልልስ ማኅበሩን እንደማይወክልና የግላቸው መኾኑን በድረ ገጹ […]

 11. […] ዓባይነህን ያነጋገሩ ሲኾን በዛሬው ዕለት ማምሻውን ደግሞ ዲ/ን ዓባይነህ ለቪ.ኦ.ኤ የሰጡት ቃለ ምልልስ ማኅበሩን እንደማይወክልና የግላቸው መኾኑን በድረ […]

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: