የእግዚአብሔር ጣት ወይስ የመንግሥት እጅ?

  • ተመራጩን ፓትርያሪክ በዕጣ የመለየቱ አሠራር በምርጫ ሳይተካ አይቀርም
  • ውሳኔው ያስቀየሩት የመንግሥት ድጋፍ አላቸው የሚባሉ አባቶች ናቸው ተብሏል
  • የአስመራጭ ኮሚቴ ሥያሜ ከሎሳንጀለሱ ጉባኤ በኋላ እንዲኾን እየተጠየቀ ነው

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለፕትርክና በዕጩነት ከቀረቡ ሦስት አባቶች አንዱ በዕጣ እንዲለዩ ቀደም ሲል በሕጉ ረቂቅ የሠራው ድንጋጌ ተሽሮ አሠራሩ በምርጫ እንዲተካ መወሰኑ ተሰማ፡፡ በብዙዎች ዘንድ ድጋፍ ያገኘው የዕጣው አሠራር ተሰርዞ በምርጫ ሥርዐት እንዲተካ ያደረገው ውሳኔ የተላለፈው÷ በፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ላይ ሲወያይ የሰነበተው ምልአተ ጉባኤው በምርጫ ሕጉ ላይ ለመፈራረም የረቂቁን የመጨረሻ ይዘት እየተናበበ ባለበት ወቅት በተነሣ ክርክር ነው፡፡

ክርክሩን አሥነስተው የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔ ያስለወጡት ቀድሞም ለዕጣ አሠራር ጠንካራ ተቃውሞ የነበራቸው ብፁዓን አባቶች ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በቆየን የተቀደሰ ሐዋርያዊ ትውፊትና የፓትርያሪክ ምርጫ ሂደቱን ከወገንተኝነትና ከውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት (ከመንግሥት ተጽዕኖ) ለመከላከል ያስችላል ተብሎ የታመነበት ዕጣ÷ ተመራጩ ፓትርያሪክ የሚለይበት የመጨረሻ አሠራር እንዳይኾን በመቃወም ውሳኔውን ካስገለበጡት ብፁዓን አባቶች መካከል÷ ለቀጣይ ፕትርክና የመንግሥት ድጋፍ እንዳላቸው በብዙ የተወራባቸው አባቶች የሚገኙበት መኾኑ የምልአተ ጉባኤውን አባላትና የሂደቱን ተከታታዮች ክፉኛ አሳዝኗል፡፡ ማሳዘን ብቻ ሳይኾን አንዳንድ የምልአተ ጉባኤው አባላት ከእኒህ ብፁዓን አባቶች ጋራ በተግሣጽ እና በኀይለ ቃል የታጀበ ምልልስ ውስጥ ለመግባት እንደዳረጋቸው ተገልጧል፡፡

Ab Hizkiel

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል

የዕጣው አሠራር ግንባር ቀደም ተቃዋሚዎች ኾነው የቀረቡት የምሥራቅ ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስና ከእርሳቸውም ጋራ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ናቸው፡፡ ከእኒህ ብፁዓን አባቶች ጋራ በአቋማቸው የሚተባበሩ ሌሎቹ የዕጣው አሠራር በቂ ድጋፍ እንዳይኖረው በአርምሟቸው አግዘዋቸዋል፡፡

የዕጣ ተቃዋሚዎች ባለፈው ሳምንት በምርጫ ሕጉ ረቂቅ ላይ በመከራከሪያነት ካቀረቧቸው ነጥቦች መካከል÷ ፓትርያሪክን በምርጫ የመሠየም አሠራር በሌሎችም አብያተ ክርስቲያንም መኖሩን፣ ቤተ ክርስቲያናችን

የቀደሙትን አምስት ፓትርያሪኮች የሠየመችው በምርጫ ሥርዐት መኾኑንና ይህን ልምድ በዕጣ መለወጥ የቀድሞውን አሠራር እንደ ሥርዐት ጥሰት እንደሚያስቆጥረው፣ የምርጫው ሥርዐት ካህናትና ምእመናን በግልጽ የሚያውቁትና በመተማመን የሚሳተፉበ

ከማድረግ አንጻር እንደ ስጋት የሚነሡበትን የወገንተኝነትና የውጭ አካላት አላስፈላጊ ተጽዕኖ አስመራጩን አካል በማቋቋም ወቅት በሚፈጸም ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ መቀነስና ማስወገድ እንደሚቻል፣ ይህም ባይኾን ስጋቶቹ በዕጣውም ፈጽሞ ሊወገዱ የማይችሉና ሊያጋጥሙ የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም (የአሁኑ የግብጽ – ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ምርጫ ሥርዐት ሕጸጾች ናቸው የተባሉት ሳይቀሩ በምሳሌነት ቀርበዋል) የሚሉት ነበሩ፡

Ab Saweros

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

ባለፈው ሳምንት እኒህ መከራከሪያዎች ምላሽ አግኝተው በምልአተ ጉባኤው የተቋጩባቸው ነጥቦች÷ የፓትርያሪክ ሥያሜ ሂደቱ ምርጫን ፈጽሞ ከሥርዐቱ ውጭ እንደማያደርግና በዕጩነት ከሚቀርቡት አምስት/ሰባት ብፁዓን አባቶች መካከል የመጨረሻዎቹ ሦስቱ የሚለዩት በምርጫ መኾኑን፣ ያለፉት ቅዱሳን ፓትርያሪኮች የምርጫ ሂደቶች ሐሜትና ትችት ያላጣቸው መኾናቸው፣ ዕጣ የመንፈስ ቅዱስ ምርጫ የሚታወቅበትና የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚገለጽበት በመኾኑ የሚሉት ነበሩ፡፡

በዛሬው ዕለት ከቀትር በፊት በነበረው የምልአተ ጉባኤው ውሎ የምርጫ ሕጉን የማጽደቅ ሂደት ወደኋላ የተመለሰበት የዕጣው ተቃዋሚዎች መከራከሪያ ደግሞ÷ ለመጨረሻ ዕጩነት ከበቁትና ባገኙት የድምፅ ቅደም ተከተል መሠረት ከአንድ እስከ ሦስት ከሚለዩት አባቶች መካከል በምርጫው በአንደኛ ደረጃ አልፎ የመጣው ዕጩ ‹‹ዕጣው ባይወጣለትና ቢከሰንስ›› የሚል መላ ነው፡፡ የተከራካሪዎቹን አባቶች የቀድሞ አቋም ያስቀየረው ይህ ‹ስጋት› በአንዳንድ የምልአተ ጉባኤው አባላት ትችት÷ ‹‹ዕጣው ለማን እንደሚወድቅ አይታወቅም፤ ‹ላልተፈለገው› ዕጩ ቢኾንስ›› የሚል ‹‹የመንግሥት ምክር/እጅ›› ያለበት የሚመስል ነው፤ መከራከሪያው በይዘቱ ‹‹ከመንፈስ ቅዱስና ከብዙኀን ፈቃድ ይልቅ የመንግሥትን ፍላጎት ለማስፈጸም ጥረት የተደረገበት፣ መንፈሳዊነትም ምክንያታዊነትም የሚጎድለው ነው፤›› ተብሏል፡፡ብፁዕ አቡነ ሉቃስ

ከዚህ ስጋት መሰል ‹መላ› በትይዩ ቆመው ተከራካሪዎቹን ሲሞግቱና ሲገሥጹ ከዋሉት ብፁዓን አባቶች መካከል÷ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ እና ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ያሉት አባቶች÷ ‹‹በዕጣው ለእግዚአብሔር ዕድል ፈንታ እንስጠው እንጂ፤›› በሚል ከቅዱስ መጽሐፍና ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እየጠቀሱ ለማስረዳት ጥረት ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹ተጭናችኹ የመጣችኹትን አታራግፉብን›› የሚልም ተግሣጽ ተሰምቷል፡፡ ይህም ሁሉ ኾኖ እስከ ቀትር ድረስ የስብሰባው ውሎ አንቀጹ የዕጣ(ን) አሠራር በመሻር የምርጫን አሠራር በማጽደቅ ሳይቋጭ እንዳልቀረ የስብሰባው ምንጮች ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡ አዲሱን ውሳኔ በርግጠኝነት ለማወቅ የሚቻለው ምልአተ ጉባኤው በሌሎች አንቀጾች ቀደም ሲል በተደረሱት ስምምነቶች መሠረት አልተካተቱም ያላቸው ሐሳቦች በአግባቡ ተካተው ረቂቁ በነገው ዕለት ለዳግመኛ እይታ ሲቀርብ ነው ተብሏል፡፡

118ውን የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ በዕጣ የተመረጡበትን ሂደት የቢቢሲው ዘጋቢ “የእግዚአብሔር ጣት” (God’s Hand) ብሎታል፡፡ ዕጣን የሚቃሙት የእኛ አባቶች ከ“እግዚአብሔር ጣት” ይልቅ ለመንግሥት ተጽዕኖ “የተመቸ ነው” የሚባለው የምርጫ ሥርዐት መርጠው ይኾንን?

በሌላ በኩል ምልአተ ጉባኤው የምርጫ ሕግ ረቂቁን ካጸደቀ በኋላ አስመራጭ ኮሚቴ እንደሚሠይም ተጠቁሞ የነበረ ቢኾንም ጉዳዩ ከጥር 16 – 18 ቀን 2005 ዓ.ም በካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ ከሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ንግግር ውጤት በኋላ እንዲታይ የሚመክሩ ብፁዓን አባቶች መሰማታቸው ተዘግቧል፡፡ ይህም በዕርቀ ሰላሙ የጋራ መግለጫ መሠረት÷ ‹‹ሁሉም ወገኖች ሂደቱን ከሚያደናቅፉ ተግባራት እንዲቆጠቡ የተደረሰበትን ስምምነት ከመጠበቅ አንጻር የመነጨና ቅ/ሲኖዶሱን በስምምነት ጥሰት ከማስወቀስ ለማዳን የተነሣ የመጣ ሐሳብ ነው›› ተብሏል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: