ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም የቅ/ሲኖዶሱን ትዕግሥት እየተፈታተኑ ነው

 • ሚኒስትሩ በቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኦርቶዶክስ ትክክል ነው የሚል የለም፤›› በማለት ምልአተ ጉባኤውን ተዳፍረዋል
 • መንግሥት በአክራሪነት ምንነት ላይ ሁሉን የሚያግባባ፣ በጥናት የተደገፈ ትርጓሜ እንዲያስቀምጥ ተጠይቋል
 • ‹‹ሁሉም ሃይማኖቶ እኵል ናቸው ተብሎ ለእኛ [ለቅ/ሲኖዱሱ አባላት] አይነገርም!!›› /ብፁዕ አቡነ አብርሃም/
 • ‹‹መቻቻል እየተበደሉ ነው ወይ? የራስን ሃይማኖት ከጥቃት መከላከልስ አክራሪነት ነው ወይ?›› /ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ/
 • ‹‹ወላይታ፣ ጂንካ ስትሄዱ ባለሥልጣኖቻችኹ የፖሊቲካ ሥራ ብቻ አይደለም የሚሠሩት፤ የእምነታቸውንም ሥራ ነው የሚሠሩት›› /ብፁዕ አቡነ ኤልያስ/
 • ‹‹የኦርቶዶክሱና የሙስሊሙ እንጂ የፕሮቴስታንቲዝሙ አክራሪነት እየተሸፋፈነ ነው፡፡ /ታዛቢዎች/

ከወቅቱ ብሔራዊ አደጋዎች (በመንግሥት አነጋገር የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ መሰናክሎች) አንዱ÷ ‹‹የኪራይ ሰብሳቢዎችና የከሰሩ ፖሊቲከኞች መጠጊያና ምሽግ ነው›› የሚባለው ‹‹የሃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት›› እንደኾነ መንግሥት በተለያዩ መድረኰች ይናገራል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በየካቲት ወር፣ 2004 ዓ.ም ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ለኾኑ የብዙኀን መገናኛ ዘጋቢዎች በተዘጋጀ ጋዜጣዊ ጉባኤ ላይ÷ ጎሰኝነት (ጠባብነት) አሁንም ዋነኛ ችግር ቢኾንም በመዳከም ላይ እንዳለና ከእርሱ ይልቅ በእምነቶች ልዩነት ሳቢያ የሚፈጠረው ውዝግብ (contention) በመገንገን ላይ መኾኑን ገልጸዋል፤ መንግሥታቸውም በችግሩ ምንጭ፣ በሚያስከትለው አደጋና በመሠረታዊ መፍትሔው ላይ ውዝግቡን አስወግዶ መግባባት ለመፍጠር እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

meles-zenawi

አቶ መለስ ዜናዊ

በራሳቸው በአቶ መለስ ይዘጋጁ የነበሩት የግንባሩ ጽሑፎች÷ በብሔር ጥያቄ ዙሪያ ‹‹የጥፋት እንቅስቃሴ ለመፍጠር የሚሞክሩ ጠባብ ኀይሎች›› ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሥር እየሰደደ በመጣ ቁጥር በይበልጥ ሃይማኖትን በመሣሪያነት መጠቀማቸው እንደማይቀር ‹‹የኦነግ ሰዎች የሚያንቀሳቅሱት ነው›› የሚሉትን ሃዋርጅያ የተሰኘ ‹‹የሙስሊም አክራሪዎች›› እንቅስቃሴ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ ጽሑፎቹ እንደ ኦነግ ያሉት የተቃውሞ ኀይሎች የሚያነሡት የብሔር እኵልነትና በሌሎቹም ወገኖች የሚቀነቀነው የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄዎች በሕገ መንግሥታዊ መርሖዎች ምላሽ ያገኙበት ‹‹ምቹ ሕጋዊና ፖሊቲካዊ ኹኔታ መፈጠሩን›› ያትታሉ፡፡

በአንጻሩ ለሃይማኖት እኵልነትና ነጻነት ‹‹የተፈጠረውን አመች ሕጋዊና ፖሊቲካዊ ኹኔታ›› በመጠቀም ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶች ለመቀስቀስ የሚሞክሩ ኀይሎችን ማየትና መስማት የተለመደ መኾኑን ሰነዶቹ ያመለክታሉ፡፡ በሃይማኖት ሽፋን ለሚፈጠር ግርግር÷ ‹‹የከሰሩ ፖሊቲከኞችን፣ ኪራይ ሰብሳቢዎችን፣ አገሪቱን የክርስትናና እስልምና የፍልሚያ አውድማ ለማድረግ የሚሹ የየራሳቸው አጀንዳ ያላቸውን የውጭ ኀይሎች›› በዋነኛ ጠንሳሽነትና አራማጅነት የሚፈርጁት ጽሑፎቹ፣ ‹‹ለግርግሩ አመቺ ኹኔታ ይፈጥራሉ›› ከሚላቸውና በተጨማሪነት ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል ‹‹በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ አንዳንድ የመንግሥት ሓላፊዎች›› ይገኙበታል፡፡

እንደ ጽሑፎቹ ገለጻ÷ ሃይማኖታዊ አምልኳቸው በመንግሥታዊ አገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ጣልቃ የሚገባባቸው የመንግሥት ሓላፊዎች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ ናቸው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከሃይማኖት ተጽዕኖ ነጻ መኾን ያለበትን መንግሥት የሃይማኖት መሣሪያ ለማድረግ በሚካሄደው ጥረት እኒህ ሓላፊዎች ሰለባ ኾነዋል፡፡

ለዚህ ገለጻ ተብሎ ባይኾንም ከጥቅምት 6 – 11 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደው 31ው የመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ተጠቃሎ የቀረበው የአህጉረ ስብከት ሪፖርት ይህን ሐሳብ የሚደግፍ ነው – ‹‹የባዕድ እምነት ተከታይ የኾኑ ባለሥልጣናት በመንግሥት ስም በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርጉት ተጽዕኖና አድልዎ፤ በብሔራዊ በዓላችን ላይ ሌላ በዓል እንዲከበር መደረጉ፤ የመናፍቃንና ሙስሊሞች ጠብ አጫሪነት አለመገታት፤. . .፡፡›› /2005፣ ገጽ 32 እና 33/

ድርጊቱ ‹‹ፍትሕ አልቦነት፣ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭት ለመቀስቀስ የሚያሤሩ ኀይሎችን የሚያግዝና የችግሩን ትክክለኛ አፈታት የሚያወሳስብ›› እንደኾነ የግንባሩ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ መፍትሔው የመንግሥት ሓላፊዎቹ÷ ‹‹ሥራቸውን በሕገ መንግሥቱ መሠረት መፈጸማቸውን ማረጋገጥ›› እንደኾነም ተመልክቷል፡፡ ጽሑፎቹ÷ አክራሪነትን ከአስተዳደራዊ ትግል ይልቅ በአስተሳሰብ (በፖሊቲካዊ መልኩ) በመፋለም ተሳስተው የተቀላቀሉ ብዙኀንን ከዋነኞቹ አንቀሳቃሾች የመነጠልና በሕገ ወጥ ተግባራቸው ተጠያቂ የማድረግ ተልእኮ ዋነኛው የግንባሩ ካድሬዎች ሥራ መኾን እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተዘጋጁ በሚነገርላቸው በእኒህ የግንባሩ የኢንዶክትሬኔሽን ሰነዶች መነሻነት÷ ‹‹በሃይማኖት ተቋማት የፖሊቲካ ዓላማን ለማራመድ የሚደረገውን ሙከራ በማክሸፍ ሃይማኖትን ከፖሊቲካ መነጠል›› በሚል ከአብያተ እምነት መሪዎች ጀምሮ በየደረጃው ካሉት የየእምነቱ ሠራተኞችና ተከታዮች ጋራ ውይይቶች እየተካሄዱ ቆይተዋል፤ እየተካሄዱም ነው፡፡ ከውይይት መድረኰቹ የሚበዙት ግን የግንባሩ ሰነዶች እንደሚሉት፣ ‹‹አክራሪነትን ከፀረ ዴሞክራሲያዊነትና ፀረ ልማት ባሕርይው በመነሣት መታገል›› ሳይኾን ኾነ ተብሎ ሃይማኖታዊ ይዘት በሚሰጣቸው ስልታዊ ፍረጃዎችና ውግዘቶች የተመሉ የመኾናቸው አጋጣሚ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

በሐምሌ/ነሐሴ፣ 2001 ዓ.ም ለኅትመት የበቃው የአዲስ ራእይ፣2 ዓመት ቅጽ 2 ቁጥር 6 እትም መጽሔት÷ ‹‹ልማት፣ ዴሞክራሲና የሃይማኖት አክራሪነት›› በሚል ርእስ ባሰፈረው ጽሑፍ÷ ‹‹አክራሪነትን የምንፈርጀው ከልማትና ዴሞክራሲያዊ መሥመራችን ተነሥተን በመኾኑ እንደ ኢሕአዴግ አክራሪነትን ስንታገል በሃይማኖታዊ ክርክር እንካሰላንቲያ ውስጥ መግባት አንችልም፤ አይገባም፡፡ ያንን መሥራት የሚችሉትና የሚገባቸው የሃይማኖት መሪዎችና ሊቃውንት ናቸው፡፡ እኛ ከሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥቱ በሃይማኖት ዙሪያ ካስቀመጣቸው መርሖዎች በመነሣት ነው ልንፋለም የምንችለው፡፡›› ይላል፡፡ /ገጽ 40/

Ethiopia


ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም

ኢሕአዴግ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን በሚያነሣባቸው በዚሁ የንድፈ ሐሳብ መጽሔቱ ሌላው ገጽ ላይ÷ ‹‹ብዙዎቹ የሃይማኖት እምነቶች ብቸኛውና ትክክለኛው እምነት የእኛ እምነት ነው›› ብለው ማመናቸው ‹‹ዴሞክራሲ ከሁሉም ሃይማኖቶች ጋራ አብሮ የሚራመድ ለመኾኑ አስረጅ ነው፤›› ይላል፡፡ ዜጎች የሌላውን የእምነት ነጻነት ማክበር አለባቸው ሲባል ሌላው ዜጋ የሚከተለው እምነት ተገቢ ወይም ትክክለኛ ነው ብለው ማመን አለባቸው ማለት እንዳልኾነ፤ ብቸኛው ትክክለኛው እምነት የእኔ ነው ማለት ከዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ውጭ እንዳልኾነ ሊሠመርበት እንደሚገባ እትሙ አጽንኦት ሰጥቶበታል – ‹‹የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ተከታይ ብቸኛው ትክክለኛ ሃይማኖት የእኔ ነው፤ ካቶሊኩ፣ ፕሮቴስታንቱ፣ ሙስሊሙ፣ ዋቄ ፈታው. . .ወዘተ ትክክለኛ እምነቶች አይደሉም ብሎ ሊያምን ይችላል፡፡ ሌሎችን እምነቶች የሚከተሉ ሰዎች ተመሳሳይ አቋም ሊኖራቸው ይችላል፡፡›› /ገጽ 28 – 29/

ስለ አክራሪነት ኢሕአዴግ ችግሩን ከያዘበትና ስለ ችግሩ ከሚናገርበት በመነሣት ይህን ሁሉ ለማለት የተገደድነው የግንባሩን ኅትመት ለማስተዋወቅ አልያም በየመድረኵ የሰማናቸውን ዲስኩሮች በመድገም አንባቢውን ለማሰልቸት አይደለም፡፡ አበው ‹‹ከአያያዝ ይቀደዳል፤ ከአነጋገር ይፈረዳል›› እንዲሉ÷ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር የኾኑት ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም በመካሄድ ላይ በሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ልዩ ስብሰባ ላይ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ ከቀትር በኋላ ድንገት በመገኘት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሱትን ሊሞግቱ የሞከሩበት መንገድ ቢያሳዝነን እንጂ፡፡

የስብሰባው ምንጮች እንደሚያስረዱት ሚኒስትሩ በቅ/ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ የተገኙት፣ ለጊዜው በዐቃቤ መንበሩና ምናልባትም በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዕውቅና ነው ተብሎ በግምት ከታሰበው ውጭ ምልአተ ጉባኤው ባልተነጋገረበትና በማያውቀው መርሐ ግብር ነው፡፡ ምልአተ ጉባኤው መርሐ ግብሩን ባያውቀውም ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩን በመጫን፣ ወይም ዐቃቤ መንበሩ ወደው እንደገቡበት በታመነ ድራማ የመንግሥት ፍላጎትን ማስፈጸም እንደሚቻል በዕርቀ ሰላሙ ንግግር ሰሞን ከ‹‹ፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ›› ጋራ በተያያዘ በታዘብነው የሚዲያ ምልልስ ከእኚሁ ሚኒስትር በስልክ ተሰጥቷል በተባለ ቀጭን ትእዛዝ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በሰጡት ቃል እንዲገቡ የተደረገበትን አጣብቂኝ ብዙዎች በማስረጃነት ያቀርባሉ፡፡

በዚሁ ዐይን የቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አመራር በተሰበሰበበት ምልአተ ጉባኤ የመንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን መገኘታቸው ብዙም አያስገርም ይኾናል፡፡ የሚያስገርመው ግን÷ ሚኒስትሩ በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ላይ ከሌሎች አራት ሹሞቻቸው ጋራ ያለአጀንዳ በድንገት ተገኝተው የተናገሩት ሙግት አዘል ቃል መድረኩን የማይመጥን፣ በምትኩ የቅዱስ ሲኖዶሱን አባላት በእጅጉ ያስቆጣና የሌላ ፍላጎት ሽፋን ሊኾን እንደሚችል ጥርጣሬን ያጫረ ነበር፡፡

የሚኒስትሩም ይኹን አብረዋቸው የተገኟቸው ባልደረቦቻቸው ንግግር በሰላምና አክራሪነት ጉዳዮች ላይ ያተኰረ ነበር ቢባልም በይዘቱ በየመድረኩ ከሚባለው የተለየ አቀራረብ ይኹን መረጃ አልነበረውም፡፡ ‹‹አክራሪነት በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ አለ፤›› አሉ ሚኒስትሩ፡፡ ለዚህም በኦርቶዶክሱም በሙስሊሙም ውስጥ አሉ ያሏቸውን ቡድኖች ጠቀሱ፡፡ የኦርቶዶክሱ ‹‹አክራሪ ቡድን›› በስም ተለይቶ ባይጠቀስም ‹‹በጣት ጠቁሞ የማሳየት ያህል ማንን እንደሚመለከት ግልጽ ነበር፤›› ይላሉ የስብሰባው ምንጮች፡፡ በምንጮቹ ግንዛቤ የፈረደበት ማኅበረ ቅዱሳን ነበር!! የሙስሊሙን ለማወቅ አዳጋች አልነበረም፡፡

ሚኒስትሩ ‹‹የሙስሊሞቹን አክራሪዎች›› በስም እየጠሩ ዘረዘሯቸው፡፡ ስሙ በግልጽ ያልተጠቀሰው ‹‹የኦርቶዶክሱ ቡድን››÷ ከየት እንደሚመጣ የማይታወቅ ገንዘብ እንዳከበተ ሚኒስትሩ ተናገሩ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሱትንም ሲያሳስቡ፣ ‹‹እናንተን አባቶችን ለመምራት የሚሻ፣ የገቢ ምንጩ የማይታወቅ ኀይል አለ፤ በዚህ ረገድ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፤›› አሉ፡፡ በስብሰባው ተሳታፊዎች ትዝብት፣ ሚኒስትሩ አክራሪነትን በመዋጋት ስም ያለመረጃ ያወረዱት የተለመደ ውንጀላ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ብሎጎች በማኅበረ ቅዱሳንና በቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን አገልጋዮችና ምእመናን ላይ ያለማቋረጥ ከሚያዘንቡት ክስ ጋራ ተመሳሳይ መኾኑ አስደናቂ ነው፡፡

አክራሪነትን ብዙኀኑ በሚግባባበት አፍራሽ መልኩና ይዘቱ ለይቶ አጥብቆ መኰነንና በተግባርም መቃወም አንድ ቁም ነገር ነው፡፡ ሚኒስትሩም ይኹኑ ጥቂት ባልደረቦቻቸው ‹‹በኦርቶዶክስ ክርስትና ውስጥ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋራ በማስሳሰር ይንቀሳቀሳል ስለሚሉት አክራሪ ቡድን›› ገለጻ የሚሰጡበት መንገድ ግን፣ ቀደም ሲል በግንባሩ ጽሑፎች የተጠቀሱትን ብያኔዎች የሚፃረር፣ ከአንድ ወገን ብቻ በእኵይ ዓላማ የሚቀርቡ ክሦችን (ለምሳሌ፡- ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ በቤተ ክህነቱ ውስጥና ዙሪያ ከተሰለፉ ጥቅመኛ ቡድኖችና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ብሎጎች) መነሻ የሚያደርግ፣ በአንዳንዶች ጠንካራ ትችትም ሚኒስትሩና ከባልደረቦቻቸውም አንዳንዶቹ የሚያራምዱት የፕሮቴስታንት እምነት አስተምህሮ የሚጫነው ነው፡፡

ይኸው ተጽዕኖ በየክልሉ በአጀንዳው ላይ በሚዘረጉ መድረኰች ጎልተውና ተደጋግመው መታየታቸው÷ በግንባሩ ያላቸውን የአባልነትና አመራርነት ሚና ከመንፈሳዊ አገልግሎት ጋራ አስማምተው አገራቸውንም ቤተ ክርስቲያናቸውንም የሚያገልግሉ ኦርቶዶክሳውያንን ክፉኛ እንዳሸማቀቀ፣ አንዳንዶቹም ‹‹ከሁለቱ አንዱን ምረጡ›› በሚል እስከመገደድና ከሥራ ገበታቸውም ለመልቀቅ እስከ መገደድ የደረሱበት መኾኑ ሚኒስትሩና የሚኒስቴሩ ሓላፊዎች የሚያውቁት ነው፡፡ እርምት የተደረገባቸው መድረኰች ግን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

በምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ላይ አክራሪነት ተብሎ በመንግሥት የሚገለጸው አስተሳሰብና ተግባር በግንባሩ ጽሑፎች ላይ እንደተመለከተው÷ ‹‹ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ ይፈጥረዋል ከሚባለው መሰናክል አኳያ›› ሳይኾን በሃይማኖታዊ ይዘቱ መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርጎ ለማስረዳት የተሞከረበት ድፍረት ተስተውሏል፡፡ የእምነት ብዝኀነትን አስመልክቶ ሁሉም የየራሱን ማምለክ እንዳለበት ከባለሥልጣናቱ የቀረበው ማብራሪያ፣ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኦርቶዶክስ ትክክል ነው የሚል የለም፤›› ዐይነት ለአንበሳ ሥጋን የመምተር መቃጣት ነበር፡፡ ማብራሪያውን በቀጥታ ለመቃወም የተነሡት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ እጆች ብዙ ቢኾንም አዝማሚያው ያላማራቸው ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ በሰዓት እጥረት አመካኝተው ወዲያው ውይይቱ እንዲዘጋ አድርገዋል፡፡

የዕለቱን ኹኔታ የሚብራሩ የስብሰባው ምንጮች እንደገለጹት÷ የሚኒስትሩ አመጣጥና ስለ ‹‹ሰላምና አክራሪነት›› የተሰጠው ገለጻ ለምልአተ ጉባኤው አባላት አልተዋጠላቸውም፡፡ ከእነርሱም አንዱ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ለሚኒስትሩና ለባልደረቦቻቸው በሰጡት አስተያየት÷ ቤተ ክርስቲያን ለአገሪቱ ያበረከተቻቸውን አስተዋፅኦዎች በመዘርዘር ታሪካዊነቷንና ታላቅነቷን አውስተዋል፤ በማያያዝም ባላገርነቷ ተሰርዞ ‹‹ትላንት ከመጡት ጋራ ሁሉ›› የማስተካከሉ አቀራረብ በየትም የሌለና ተገቢ እንዳልኾነ ተችተዋል፡፡ ‹‹ለእኛ ሁሉም ሃይማኖት እኵል ናቸው ተብሎ ሊነገረን አይገባም›› ሲሉም የሚኒስትሩ አነጋገር ‹‹በጣም ዘግናኝ›› እንደነበር መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹የእኵልነት ጉዳይ ከተነሣስ›› አሉ ብፁዕነታቸው ‹‹ለሸሪዓ ፍ/ቤቶች የምትመድቡት በጀት ለእኛ ይቅርብንና ሕንፃዎቻችንን መቼ መለሳችኹ?››

ብፁዕ አቡነ አብርሃም

ብፁዕ አቡነ አብርሃም

የወላይታ ሶዶ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በበኩላቸው÷ ‹‹መቻቻል ማለት ጥቃት እየደረሰብን ነው ወይ? ጥቃት ሲደርስስ የራስን ሃይማኖት መከላከል አክራሪነት ነው ወይ?›› በማለት የአክራሪነት ትርጉምና መገለጫ ተደርገው የቀረቡ አስረጅዎችን ሞግተዋል፡፡ የሰሜን ኦሞና ደቡብ ኦሞ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ያቀረቡት የአህጉረ ስብከታቸው መረጃም አንዳንድ የመንግሥት ሓላፊዎች ሥልጣናቸውን መሣሪያ በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ላይ በደል ስለመፈጸማቸው የቀረቡና መንግሥትም ያመነባቸውን ሪፖርቶች የሚያስረግጥ ነው – ‹‹እኛን መጠበቅ የሚገባው ፖሊስ እኛን ገድሎ ነው የሄደው፤ ወደ በወላይታ፣ በጂንካ ባለሥልጣኖቻችኹ የፖሊቲካ ሥራ ብቻ አይደለም የሚሠሩት፤ የእምነታቸውን ሥራ ጭምር ነው የሚሠሩት፡፡››

ምልአተ ጉባኤው በቀጣዩ ቀን ውሎው በሚኒስትሩና ባልደረቦቻቸው አመጣጥ ላይ ባደረገው ውይይት፣ በቀድሞው ፓትርያሪክ ዘመን ይደረግ እንደነበረው፣ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለይም በሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ እየመጡ ያሻቸውን መለፈፍ ‹‹ከአባ ጳውሎስ ዘመነ ጋራ ያበቃ መኾኑን ሊያበቃም እንደሚገባ›› መናገራቸው ተዘግቧል፡፡

በያዝነው ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ ላይ መንግሥት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ሠራተኞች ጋራ ባካሄደው ተመሳሳይ ውይይት÷ አክራሪነትን ለመዋጋት እየተባለ ያለፈውን ሁሉ በመጥፎ መፈረጅ፣ አንዱ እምነት ከሌላው የበለጠ የተጎዳ እያስመሰሉ በተለየ መንገድ የመጥቀም ወገንተኝነት (reverse discrimination) መፍትሔ እንደማይኾን፣ የፕሮቴስታንት እምነት ከአክራሪነት ነጻ የኾነ ይመሰል ኦርቶዶክስ ክርስትናና እስልምና ብቻ በምሳሌነት የሚጠቀስበት አቀራረብ እንዲታረም፣ መንግሥት ራሱ ከኢትዮጵያዊው ሃይማኖተኝነት ጋራ የማይጣጣም ‹‹የዓለማዊነት (secular humanism) እና የልማታዊነት አክራሪነት ዝንባሌ›› እንደሚታየበትና አክራሪነት አንድን ነገር አጥብቆ መውደድ አለመኾኑን፣ አክራሪነት ከጋዜጣና መጽሔት ጠለቅ ባሉ ማስረጃዎች በምርምር ተደግፎ ሁሉም በሚቀበለው መልኩ እንዲቀርብ የሚመለከቱ ጥያቄዎች መነሣታቸው ተገልጧል፡፡

Advertisements

6 thoughts on “ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም የቅ/ሲኖዶሱን ትዕግሥት እየተፈታተኑ ነው

 1. Ben December 18, 2012 at 12:53 am Reply

  ሰውዬው ጴንጤዎቹ የሰጡትን ቤተ ክርስቲያኗን የማፍረስ ተልዕኮ ለመወጣት የሚታትር አክራሪ ነው። በውጪው አለም የክርስቲያን አክራሪ የሚለው ስም ከጴንጤዎቹ ጋር የተጣበቀው ካቶሊኮቹ ላይና ሌላው ሰው ላይ በሚያደርጉት ድርጊት ነው። ይሄ ደሞ አሁን ስልጣኑን ተጠቅሞ ቀስ በቀስ የቤተ ክርስቲያኗን ህልውና ለማናጋት ይጥራል። ትናንት ፈረሰች ልትጠፋ ነው ያሏት ቤተ ክርስቲያን እያበበች፥ ወንጌልን አታውቅም ይሏት የነበሩት ዛሬ ወጣቶቿ የወንጌል ገበሬ መሆናቸው አስፈርቷቸዋል። ስለዚህ በቻሉት አጋጣሚ ካላፈረስኩ ቢል ምን ይገርማል? የሚገርመው እሱን ስብሰባቸው ውስጥ ማስገባታቸው ነው። ሰውየው የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ ነው። በቅርቡ ጁነዲንን ይከተላል።

 2. shifera December 19, 2012 at 7:39 am Reply

  he stupid, min agebaw

 3. my God December 20, 2012 at 10:48 am Reply

  የአሁኑ ይባስ እምነት ፕሮፖጋንዳ መሰለው እንዴ ቅዱሳን ላይ አፉን የሚከፍተው ዘንዶው አፉን ከፍቶ ቅዱሳንን ተሳደበ ዘለፈ ቢባል ይገልጸው ይሆን? በቀልን ለእግዚአብሔር እንተወው ጣታቸውን የቀሰሩ ሰዎች ዋጋቸውን ያገኟታል፡፡የመንደር የቀበሌ የማሟያ ምርጫ መሰለው በስልጣን ቢሆንማ ኑሮ ……………ማን ለሞት ይገዛ ነበር አንተም ከሰዎች እንደ አንዱ፡፡ተቅበዝብዘህ እንዳትጠፋ አትቅና አይ ዶክተር ድንቄም ዶክተር ራስህን አወረድህ ለነገሩ የኢህአዴግ ማዕረግ ራሱን ለመካብ የሰጠህ መጠሪያ ማዕረግ መሰለኝ እንጂ በትምህርቱ ያለፍክ አይመስልም፡፡

 4. firew December 21, 2012 at 10:43 am Reply

  manem yefelegewun yawura muya beleb new … emenetachenen manem endefelege lisadeb yechelal ya malet kemamilek yagidenal malet aydelem…… bizu asache endale kamenen lemen enerebeshalen….

 5. Anonymous December 30, 2012 at 5:52 am Reply

  Geta Firdun endeyeseraw yisetal kemalet lela min yibalal.Get Ethiopian Yitebik!!!!!!

 6. kidus January 25, 2016 at 5:40 am Reply

  hello Bawza

  Dehab-AD is new advertising agency website in Ethiopia we work with
  advertisers and website owners
  we want to post banners on your website and pay you by pay per impression
  (ppc ) method
  the banners are going to be about Ethiopian company’s and their products we
  have a good payment for the ppc more than Google adsens and we don’t force
  you to post banners you don’t want
  our website will start work soon we need to setup on agreement before the
  website and some other processes are finished

  we are happy if you work with us
  Thanks,

  kidus CEO
  Dehab-AD

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: