በመጨረሻ÷ ተመራጩ ፓትርያሪክ በዕጣ ይለያል!

 • የፓትርያሪኩ ዜግነት ኢትዮጵያዊ ብቻ እንዲኾን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል
 • የገዳም መነኵሴ ከዕጩነት እንዲወጣ መደረጉ እያነጋገረ ነው

በፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ላይ በመወያየት ላይ የሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ልዩ ስብሰባ÷ በምርጫው ሂደት ፓትርያሪኩ በመጨረሻ የሚለይበት ሥርዐት ዕጣ እንዲኾን ወሰነ፡፡

ምልአተ ጉባኤው ውሳኔውን ያስተላለፈው፡-

 • በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ አባቶች ለሐዋርያዊ አገልግሎት በዕጣ የተመረጡበትን የተቀደሰ ትውፊት (ግብ. ሐዋ.1÷13) መነሻ በማድረግ፣
 • ሥርዐቱ የመንፈስ ቅዱስ ምርጫ የሚገለጽበት መኾኑን በማመን፣
 • በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ ከሢመተ ፕትርክናና ጵጵስና ጋራ ተያይዞ ስለ ዕጣ አገልግሎት የሰፈረውን ድንጋጌ በማጤን፣
 • የምርጫውን ሂደትና ውጤት በወገንተኝነትና በዝምድና ትስስር ከሚመጣ ሐሜት እንዲሁም ከተለያዩ የውጭ ተጽዕኖዎችና ጣልቃ ገብነቶች ለመጠበቅ፣
 • በካህናትና ምእመናን ዘንድ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ይኾን ዘንድ

  በቅብጥ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያሪክ ምርጫ በዕጣ ሲለይ

  በቅብጥ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያሪክ ምርጫ በዕጣ ሲለይ

እንደኾነ የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች ለሐራ ዘተዋሕዶ አስረድተዋል፡፡ በምርጫ ሕግ ረቂቁ አንቀጽ 9 ንኡስ አንቀጽ 12÷ አስመራጭ ኮሚቴው በምስጢራዊ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዐት መሠረት አብላጫ ድምፅ ያገኘውን ዕጩ ፓትርያሪክ ስምና ሌሎቹንም ተወዳዳሪዎች ባገኙት ድምፅ ቅደም ተከተል መሠረት በጽሑፍ አዘጋጅቶና በቃለ ጉባኤ ተፈራርሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በማቅረብ እነርሱም እንዲፈርሙበት እንደሚደረግ፣ በንኡስ አንቀጽ 13 ደግሞ÷ የምርጫው ጠቅላላ ውጤት ለሕዝብ እንደሚገለጽ አመልክቶ ነበር፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በትላንት፣ ታኅሣሥ 4 ቀን 2005 ዓ.ም ውይይቱ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ግን በረቂቁ አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 2፣ ፊደል ተ.ቁ(ረ) መሠረት ከሦስት ያላነሱ ከሰባት ያልበለጡ ዕጩዎች ከቀረቡ በኋላ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ ኾኖ ከሕዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ይመረምራል፤ በመጨረሻም ለፓትርያሪክነት ይበቃሉ ተብለው የታመነባቸውን አምስት ዕጩዎች ዝርዝር ከትምህርት ደረጃቸው፣ ችሎታቸውና ልምዳቸው ጋራ ይፋ አድርጎ የምርጫውን ቀን ያሳውቃል፡፡ ከአምስቱ ዕጩዎች ሦስቱ በምርጫ ሥርዐት ከተለዩ በኋላ ለፓትርያሪክነት የሚበቃውን ዕጩ ከሦስቱ ለመለየት ተአማኒነትንና ግልጽነትን በተከተለ አኳኋን የዕጣ አሠራር ተግባራዊ ይኾናል፡፡

በረቂቅ ሕጉ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 1÷ ለፓትርያሪክነት የሚቀርበው ዕጩ ተወዳዳሪ ኢትዮጵያ ዜግነት ያለው ብቻ እንዲኾን ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ቢጠቀሱም የአንቀጹ ተቀባይነት ግን ብዙም አከራካሪ እንዳልነበር ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በራሱ እሴት መኾኑን፣ ኢትዮጵያዊነት ከኦርቶዶክሳዊነት ጋራ ጥብቅ ቁርኝት ያለው መኾኑን፣ ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ግዴታዎች አኳያ የቤተ ክርስቲያኒቱ ርእሰ አበው በዜግነቱ የተለየ መኾኑ ሊፈጥር የሚችለውን መወሳሰብ፣ በቀደመ ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ የነበሩ አባቶች ዜግነታቸውን የቀየሩበት ምክንያት ለትውልዱ መልካም አርኣያነት የሌለው መኾኑ ከመመዘኛ መስፈርቱ መነሻዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ውሳኔው ለተወዳዳሪነት ይበቃሉ ከተባሉትና የመንግሥትንም በሢመት ቀደምትነት ያላቸውን የአንዳንድ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ድጋፍ አግኝተዋል የተባሉትን ብፁዕ አቡነ ማቲያስን ከዕጩነት ማውጣቱ ቅሬታ ያሳደረባቸው ወገኖች አልጠፉም፡፡

በሌላ ዜና÷ በረቂቁ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 2 እና 3÷ ከኤጲስ ቆጶሳት፣ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ለዕጩነት መቅረብ ከሚችሉት ተወዳዳሪዎች መካከል የገዳም መነኵሴ እንዲካተት የቀረበው ሐሳብ እንዲወጣ መደረጉ የሂደቱን ተከታታዮች አሳዝኗል፡፡ ለአንቀጹ መውጣት በምክንያትነት ቀርቧል የተባለው በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 11 ላይ÷ ዕጩ ተወዳዳሪው ‹‹መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመፈጸም ብቁ የአስተዳደር ችሎታና ልምድ እንዲኖረው›› በተቀመጠው መመዘኛ መሠረት መኾኑ ተገልጧል፡፡ እውን በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በሥራ ችሎታቸው እና ልምዳቸው በኤጲስ ቆጶስነት ሀገረ ስብከትን ከሚመሩ አባቶች ያነሱ፣ ታላላቅ ገዳማትንና አድባራትን በአበምኔትን ይኹን በእልቅና የሚመሩ አበው መነኵሳት ይጠፋሉን? ወይስ እንደሚባለው ከመነኵሴ ጋራ ተወዳድሮ ለማሸነፍ የማይቻል ኾኖ ነው?

የዕጩ ተወዳዳሪዎች አነስተኛ ዕድሜ መጽሐፈ ዲድስቅልያው ለኤጲስ ቆጲስነት በሚያስቀምጠው መነሻ መሠረት 50 ዓመት እንዲኾን ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡ በዚህም በረቂቁ የተቀመጠው የ45 ዓመት መነሻ ተለውጧል፡፡ የዕድሜ መስፈርቱ መጨረሻ እስከ 80 ዓመት እንዲዘልቅ ቢደረግም ወሰኑን ማስቀመጥ በብዙኀኑ የምልአተ ጉባኤ አባላት አስተያየት አስፈላጊ ኾኖ አለመገኘቱ ተጠቁሟል፡፡

ዕጩው በዘመናዊ ትምህርት ዲፕሎማ እንዲኖረው የሚጠይቀው መስፈርት የአብነት ትምህርቱንና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መውጣትን እንደበቂ በመውሰድ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ 19 አባላት በሚኖሩት አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ ‹‹2 የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች›› እንዲገቡ ተብሎ በረቂቁ የቀረበው ቁጥር ‹‹አንድ ከሰንበት ት/ቤት፣ አንድ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሰጠችው ዕውቅና መሠረት በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥር ኾኖ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ከሚገኘው ከማኅበረ ቅዱሳን›› እንዲኾን በምልአተ ጉባኤው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የሕጉ ረቂቅ ለሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ለካህናትና ለምእመናን ተሳትፎ ዝግ በተደረገበት ኹኔታ በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል፡፡ ሕጉ በካህናትና ምእመናን ዘንድ አመኔታ የሚኖረው ቋሚና ወጥ የቅዱስ ፓትርያሪክ ምርጫ ሥርዐት ሊያሰፍን ከኾነ፣ የበለጠ ጊዜ እንዲሰጠው አሁንም ለምልአተ ጉባኤው አባላት የሚቀርበው ምክርና አስተያየት እንደቀጠለ መኾኑ ተዘግቧል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ለዕርቀ ሰላም የተላከው ልኡክ ሪፖርቱን ባላቀረበበት ኹኔታ በቀጣይ ሳምንት ሰኞ አስመራጭ ኮሚቴ ሊሠይም እንደሚችል መነገሩም ተስፋ ሰጪ መኾኑ በተነገረው የዕርቀ ሰላም ሂደት ላይ የበለጠ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥርና ያልተፈለገ ውጤት እንዳያመጣ የተለያዩ ስጋቶች በመደመጥ ላይ ናቸው፡፡

Advertisements

One thought on “በመጨረሻ÷ ተመራጩ ፓትርያሪክ በዕጣ ይለያል!

 1. Anonymous December 17, 2012 at 1:19 pm Reply

  are you sure that the pop is going to be chosen by lottery method? i found this contradictory with what Adiss admass had reported.

  Apart from this Bert!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: