የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ላይ መወያየት ጀምሯል

 • በረቂቅ ላይ ተጨማሪ የውይይት መድረኰች እንዲዘጋጁ ጠንካራ ፍላጎት እየታየ ነው
 • ለሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያው የተሠየመው ኮሚቴ በሰው ኀይል ተጠናክሯል
 • የገዳም መነኵሴ በፓትርያሪክ ዕጩነት ለማቅረብ የሚያስችል አንቀጽ ተካቷል

 

የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት በሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ እና በፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ዝግጅት ላይ ለመነጋገር ለኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ተቀጥሮ የነበረውና ትላንት ከቀትር በኋላ የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ልዩ ስብሰባ ዛሬ፣ ታኅሣሥ 2 ቀንም 2005 ዓ.ም ቀጥሎ ውሏል፡፡

ምልአተ ጉባኤው በትላንት ጠዋት ውሎው የስብሰባው ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ የተመለከተው÷ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያውን ሂደት ሲሆን ዝግጅቱ በውሳኔው መሠረት ተከናውኖ ባለመቅረቡ ኮሚቴውን በተጨማሪ የሰው ኀይል ማጠናከር አስፈልጓል፡፡ ስለሆነም ቀደም ሲል የኮሚቴው አባላት የነበሩት አራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሁለት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና አንድ ከፍተኛ የሕግ ባለሞያ እንደተጠበቁ ኾኖ ኮሚቴውን በማማከር ሲያግዙ የነበሩ ሌሎች ሁለት የሕግ ባለሞያዎች በአባልነት እንዲጨመሩ ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፡፡abew

ምልአተ ጉባኤው በትላንቱ የቀትር በኋላ ውሎው ያዳመጠው በተሳታፊዎች ቁጥር ልክ ተባዝቶ እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ በንባብ የቀረበለትን በ15 አናቅጽ የተከፋፈለ ባለዘጠኝ ገጽ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ነው፡፡ ዛሬ፣ ታኅሣሥ 2 ቀን 2005 ዓ.ም ለግማሽ ቀን በረቂቁ ላይ በዝግ ሲወያይ የቆየው ቅዱስ ሲኖዶሱ÷ ተሲዓት በኋላ ከመመሪያና ከድርጅት ሓላፊዎች፣ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች እና ከማኅበረ ቅዱሳን ድንገተኛ ጥሪ የተደረገላቸው ሦስት ሦስት ተወካዮች በተገኙበት ውይይቱን ቀጥሎ አምሽቷል፡፡

የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ አርቃቂ ኮሚቴው አባል በኾኑት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ተሰጠ በተባለው ሐሳብ መነሻነት በድንገተኛ የስልክ ጥሪ የተሰባሰቡት ተወካዮቹ በረቂቁ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ የተደረገው አስቀድመው ሰነዱን የማጥናት ዕድል ሳያገኙ በድንገት መኾኑ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ ሂደቱን አሳታፊ ከማድረግ አንጻር ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ሙከራ ጨርሶ የሚነቀፍ ባይኾንም በሚገባ የተጠና፣ የምሁራኑ፣ የአገልጋዩና ምእመኑ አመኔታ የተቸረው የፓትርያሪክ ምርጫ ለማካሄድ ግን ያስችላል ተብሎ ፈጽሞ አይታሰብም፡፡

በመኾኑም ሕጉ በሐሜት እንደሚነገረው ‹‹በኾነ ግለሰብ ልክ የተሰፋ›› ሳይሆን የመንበረ ተክለ ሃይማኖትን ክብር የሚጠብቅ፣ ለቤተ ክርስቲያናችንን አንድነትና ሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ረጅም ታሪኳን የሚመጥን ወጥና በቋሚነት የሚያገለግል ይኾን ዘንድ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ ምሁራን፣ አገልጋዮችና ምእመናን በሰፊው የሚሳተፉበት ሊኾን ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የዛሬውን ድንገቴ መድረክ እንደ በቂ በመውሰድ አስመራጭ ኮሚቴ ሠይሞ እንደሚነሣ የሚጠበቀው ቅዱስ ሲኖዶስ ተጨማሪ መድረክ በሚመቻችበት ኹኔታ እንዲያስብበት በመንበረ ፓትርያሪኩ ውስጥና ዙሪያ ሂደቱን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡

ይህም ኾኖ በተሲዓት በኋላው የአስተያየት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ በድንገትም ቢኾን የተሰነዘሩት ሐሳቦች የሚናቁ እንዳልኾኑ ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ  አስተያየቶቹና ትችቶቹ ‹‹ይመዝገቡ›› ከሚለው ትእዛዝና አልፎ አልፎ በተጋባዦቹ መካከል ከታዩ ክርክሮች ውጭ ግን ጥልቀት ያለው ውይይት ለማድረግ አለመቻሉ ተዘግቧል፡፡ ክርክር ከተካሄደባቸው ወይም አወያይ ከነበሩት የሕጉ ረቂቅ ክፍሎች መካከል÷ የፓትርያሪኩን ዜግነት፤ ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃና የቋንቋ ክህሎት፤ ሥርዐተ ምንኵስና፣ የዕጩዎች አቅራቢ ኮሚቴ እና የአስመራጭ ኮሚቴ መለያየት እና አደረጃጀት፤ ዕጣ(ን) እንደ ሥርዐት ስለ መቀበል፤ የምእመናን አወካከል፣ ተሳትፎ እና የመንግሥት ሚና የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ዜግነትን በተመለከተ በ1991 ዓ.ም ጸድቆ በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ምዕራፍ አምስት፣ አንቀጽ 18 ንኡስ አንቀጽ 3(ለ)÷ የኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫ አስመልክቶ ባሰፈረው ድንጋጌ÷ ‹‹በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የኾነ÷ ባይኾንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ ኾኖ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ጠንቅቆ ያወቀ›› የሚለው አማራጭ በኮሚቴው በቀረበው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ውስጥ የለም፡፡ በምትኩ በረቂቁ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ ለዕጩነት የሚቀርበው አባት በዜግነቱ የግድ ኢትዮጵያዊ መኾን እንደሚገባው ነው ያስቀመጠው፡፡

ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡ ጥቂቶቹን ለማውሳት ያህል÷ ከቤተ ክርስቲያን ኵላዊነት አንጻር በትውልዳቸው የሌላ አገር ኾነው በዜግነታቸውም የተለዩ አባቶች በኦርቶዶክሳዊነታቸው እስከታመነባቸው ድረስ ኹኔታው ሊጤን እንደሚችል ግንዛቤ ተወስዷል፤ ነገር ግን ‹‹ባለንበት ጊዜ እንደ ቀድሞው ዘመን /እንደ ተሰዓቱ ቅዱሳን/ ይህ ኹኔታ ተሟልቶ ስለማይገኝ››፣ ‹‹ኦርቶዶክሳዊነት ከኢትዮጵያዊነት ጋራ ባለው ጥብቅ ትስስር››፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት  በምርጫው ለዕጩነት ይበቃሉ ተብለው የሚታሰቡትና የውጭ ዜግነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ብፁዓን አባቶች ዜግነታቸውን የቀየሩበት ምክንያት ለትውልዱ መልካም አርኣያነት የሌለው በመኾኑ››፣ ‹‹ፓትርያሪኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመወከል ከመንግሥት እና በውጭ ግንኙነት ረገድ በሚያደርገው እንቅስቃሴ በዜግነቱ ሳቢያ የሚነሡ ግልጽና ታሳቢ ስጋቶች›› የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

Aba mati

ብጹእ አቡነ ማትያስ

አንዳንድ ተቺዎች ግን÷ በረቂቁ የፓትርያሪኩ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ብቻ እንዲኾን የታሰበው÷ ዕርቀ ሰላሙ በመልካም ተከናውኖ በውጭ የተሾሙት አባቶች የሚሳተፉበት ኹኔታ ቢኖር ዕድሉን ለማጥበብ፣ ያም ባይኾን በአገር ውስጥ በተወዳዳሪነት ስማቸው የሚነሡ ጥቂት ብፁዓን አባቶችን /በተለይም ቀዳሚው የመንግሥት ምርጫ ናቸው የሚል ዘገባ የወጣባቸውን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ ፕትርክና ውግዘት ተላልፎባቸው እንደነበር የሚነገርላቸውን በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስን/ በዕጩነት እንዳይካተቱ ለመከላከል እንደኾነ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህም አኳያ ይህ አንቀጽ መንግሥትንና የሐሳቡን ደጋፊዎች እንዳስቆጣም እንዳስከፋም እየተነገረ ነው፡፡

ዕድሜን በተመለከተ÷ በመጽሐፈ ዲድስቅልያ የተመለከተው የዕድሜ መነሻ ኀምሳ ዓመት ኾኖ የመጨረሻ ገደብ የለውም፡፡ በሕግ ረቂቁ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 4 ላይ ግን ዕድሜው ከ45 ዓመት ያላነሰ ከ70 ዓመት ያልበለጠ መኾን እንደሚገባው ተገልጧል፡፡ የዕድሜው መነሻ በመጽሐፈ ዲድቅልያ ከተቀመጠው ማነሱ፣ በሥርዐት መጽሐፉ የሌለው የዕድሜ ጣሪያ መቀመጡም በዕጩነት ከሚታሰቡ አንዳንድ አባቶች (ለምሳሌ አቡነ ማቲያስ ከ70 ዓመት ዕድሜ በላይ ናቸው) አንጻር አሁንም ተመሳሳይ ጥያቄ አሥነስቷል፡፡

በዚሁ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 2 ላይ ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ፣ ኤጶስ ቆጶስ ወይም የገዳም መነኵሴ በፓትርያሪክ ዕጩነት ሊቀርብ እንደሚችል ይገልጻል፡፡ የገዳም መነኵሴው ፈጽሞ ያላገባ ድንግል (ከግቢ በኋላ ያልመነኰሰ ለማለት ነው)፣ ዕድሜው ከ45 ዓመት በላይ ሊኾን እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡ በ1991 ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የዕድሜ ክልል የተወሰነው ከ45 – 60 ድረስ ነው፡፡ ሥርዐተ ምንኵስናን በሚመለከት ረቂቁ በአንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 3÷ በፓትርያሪክ ዕጩነት የሚቀርበ የገዳም መነኵሴ በመነኰሰበት ገዳም ከሰባት ዓመት በላይ ያገለገለ መኾን እንደሚገባው ያስቀምጣል፡፡ ቀደም ሲል ባገለገሉት የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቦች እስከ ዐሥራ አምስት ድረስ በመነኰሱበት ገዳም ማገልገልን መሠረት ያደረጉ አንቀጾች ነበሩ፡፡

በዚህ አንቀጽ ፈጽሞ ያላገባ ድንግል መነኵሴ በዕጩነት እንዲካተት መደረጉ ብዙዎችን አስደስቷል፡፡ ከወዲሁም በምንኵስናቸው የተመሰገኑ አበውን ከማሰብ አልፈው በስም መጥራት የጀመሩም አልጠፉም፡፡ ይኹንና መመዘኛው በመነኰሱበት ገዳም የተጠቀሰውን ያህል ዕድሜ ባይቀመጡም በምንኵስናቸው (በንጽሕናቸው)ና በሊቅነታቸው ታውቀው፣ ጉባኤ ዘርግተው ደቀ መዝሙር በማውጣት፣ በማኅበራዊ ኑሮና በመንፈሳዊ አስተዳደር የታወቁ አበውን ሊያገል እንደሚችል ተሰግቷል፡፡

የምርጫ ሕግ ረቂቁ የትምህርት ደረጃንና የቋንቋ ክህሎትን በተመለከተ÷ በአንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 5÷ ‹‹ትምህርተ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠንቅቆ ያወቀ፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጽኑዕ የኾነ፣ በቅድስና ሕይወቱና በግብረ ገብነቱ የተመሰገነ›› መኾን እንደሚገባው ያዝዛል፡፡ በንኡስ አንቀጽ 6 ዕጩው÷ ‹‹ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ት/ቤቶች በአንድ ትምህርት የተመረቀ ወይም ሁለገብ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያለው ኾኖ ከከፍተኛ የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋማት ወይም በዘመናዊ ትምህርት ቢያንስ ዲፕሎማ ያለው›› መኾን እንደሚገባው መመዘኛው ይዘረዝራል፡፡

በቋንቋ ክህሎት ረገድ በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 10÷ የቤተ ክርስቲያኗ ቋንቋ የኾነውን የግእዝ ቋንቋ ጠንቅቆ ያወቀ፣ ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች አማርኛንና ቢቻል ከሌሎች ቋንቋዎች አንዱን ወይም ከዚያ በላይ የሚያውቅ ኾኖ በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ቢያንስ በአንዱ በብቃት መግባባት እንደሚጠበቅበት ተጠቁሟል፡፡

በእኒህ አንቀጾች የአብነት ትምህርቱ ወይም ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርቱና ዘመናዊ ትምህርቱ ተጣምረው መመዘኛ መኾናቸው በአመዛኙ በበጎ ጎን ታይቷል፤ ነገር ግን ከዘመናዊ ትምህርቱ አኳያ የአብነት ትምህርቶች በተነጻጻሪ መለኪያ ሲታዩ አብላጫና ከፓትርያሪክነት ክብር አንጻር አግባብነትም ሊኖራቸው እንደሚችል ግምት ተወስዷል፡፡ በመኾኑም መመዘኛውን ለብዙዎቹ አባቶች ተጨባጭ ከማድረግ አኳያ የአብነት ትምህርቱ ብቻ (ከእኒህም ከአራቱ ጉባኤያት ቢያንስ አንዱ) እንደ ዋነኛ (በቂ) መስፈርት እንዲወሰድ የሚከራከሩ ወገኖች ተሰምተዋል፡፡

በጣም አወያይ ሊኾን እንደሚችልና እንደሚገባው የሚጠበቀው ሌላው ጉዳይ በአንቀጽ 6 የተመለከተው የአስመራጭ ኮሚቴ መቋቋም ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ አንድ (ሀ) መሠረት÷

 • 5 ሊቃነ ጳጳሳት፣
 • 5 የገዳም አበምኔቶች፣
 • ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ በየደረጃው ባለው መዋቅር ውስጥ ከሚያገለግሉት መካከል የተመረጡ 3 ሠራተኞች፣
 • 4 ምእመናንና 2 የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች

በድምሩ 19 አባላት የሚገኙበት አስመራጭ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚቋቋም ተመልክቷል፡፡

በዚሁ ንኡስ አንቀጽ ፊደል ተ.ቁ(ሐ)÷ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ጸሐፊም በቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚመደብ ይገልጻል፡፡ በንኡስ አንቀጽ 2(ሐ) ላይ ኮሚቴው ለፓትርያሪክነት የሚጠቆሙትን አባቶችን ስም እየመዘገበ እንደሚይዝ ሰፍሯል፡፡ ከሚጠቆሙትም ዕጩዎች ውስጥ የኮሚቴውን አባላት 15 እና ከዚያ በላይ ድጋፍ ያገኙና ለዕጩነት የተቀመጠውን መመዘኛ አሟልተው የተገኙትን አባቶች ስም ዝርዝር ከነመረጃቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚቀርብ ተገልጧል፡፡

በእኒህ አንቀጾች ላይ የሚነሡት የተቺዎች አስተያየት÷ ለዕጩነት የሚታሰቡትን አባቶች ጥቆማ ተቀብሎ የመመዝገብ፣ በድጋፍ የመለየትና ለቅዱስ ሲኖዶስ የማቅረብ ተግባር የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት ከመምራት – ‹‹አስመራጭ ኮሚቴ›› – አንድ መኾን አለበት ወይስ መለያየት አለበት የሚለው ነው፡፡

አንቀጹ የምርጫውንና የሢመተ ፕትርክናውን ሂደት ከውስጥ ሽኩቻ እና ሐሜት እንዲሁም ከውጭ ተጽዕኖ ለመጠበቅ ወሳኝ የኾነ አካሄድ የሰፈረበት እንደኾነ ይታሰባል፡፡ በምርጫው ሕግ ረቂቅ ላይ ሁለቱ አካላት እንደ አንድ ተወስደው የሚደራጁበት ኹኔታ፣ ሥልጣንና ተግባራቸው በአንድ አንቀጽ ተጠቃሎና በንኡሳን አናቅጽ ተከፋፍሎ ቀርቧል፡፡ አማራጭ ሐሳብ አቅራቢዎች ግን ግልጽነትን ለማስፈን፣ ለእርስ በርስ ቁጥጥርና ገለልተኝነትን ለመጠበቅ ሲባል ሁለቱ ተግባራት (ዕጩዎችን መዝኖና ለይቶ የማቅረብ ተግባር የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት ከመምራት ሥራ) መለያየት እንደሚገባቸው፣ በአባላት ጥንቅሩም የሁሉም ጾታዎች (ወገኖች) ተሳታፊነት መረጋገጥ እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡

ከሐዋርያዊ ትውፊትና ከአኀት አብያተ ክርስቲያን ልምድ አንጻር በመጨረሻው የምርጫ ደረጃ ላይ ዕጣ እንደ አንድ ሥርዐት እንዲካተት የቀረበው ጥያቄ ጠንካራ ተቃውሞ ቢገጥመውም ሊጤን እንደሚገባው ሰፊ ክርክር እየተካሄደበት ቆይቷል፡፡ በረቂቅ ሕጉ አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 2 ፊደል ተ.ቁ (ረ) ላይ በተመለከተው መሠረት÷ ኮሚቴው ከተቀበላቸው ዕጩዎች መካከል ከሦስት ያላነሱ ከሰባት ያልበለጡ ዕጩዎችን እንደሚያቀርብ፣ ከእኒህም መካከል የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለመጨረሻ ዕጩነት የሚለያቸው አባቶች ስም ዝርዝር፣ ከትምህርት ደረጃቸው፣ ከችሎታቸውና ልምዳቸው ጋራ ለ15 ቀናት ለሕዝብ ይፋ ኾኖ ኮሚቴው ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን እንደሚቀበል ተመልክቷል፡፡

የዕጣ ሐሳብ ደጋፊዎች በመጀመሪያ ላይ ሰባት አባቶች በዕጩነት ተካተው የመጨረሻዎቹ ሦስቱ በምርጫ ሥርዐት እንዲለዩ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ከሦስቱ አባቶች ግን ለፓትርያሪክነት የሚገባው ሰው መለየት ያለበት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምርጫና ፈቃድ በሚገለጥበት በዕጣ መኾን እንደሚገባው ይከራከራሉ፡፡ የዕጣ ሐሳብ ተቃዋሚዎች ደግሞ የዕጩው ብቃት በውድድር እየተመዛዘነ፣ እየጠራና እየነጠረ የሚሄድበትን ግልጽና ተአማኒ አሠራር እንዲሁም አምስቱ ፓትርያሪኮች የተመረጡበትን ሕገ ደንብ ልምድ በቂ በማድረግ የዕጣን ሥርዐት ይቃወማሉ፡፡ ከምልአተ ጉባኤው በፊት በዚህ ክርክር ሂደት የታየውና ሳይጠቀስ የማይታለፈው አንድ አስገራሚ ጉዳይ÷ ዕጣን የሚቃወሙ ወገኖች በግብጹ የ118 ፓትርያሪክ ምርጫ ለፖፕ አቡነ ታዎድሮስ ዕጣው በወጣበት ኹኔታ (አቡነ ቢሾይ የሕፃኑን እጅ የመሩበት ኹኔታ ላይ) ጥርጣሬ ያላቸው መኾኑ ነው፡፡

በረቂቁ አንቀጽ 7 በፓትርያሪክ ምርጫ ላይ የሚሳተፉ መራጮች ሊያሟሉት ስለሚገባቸው መስፈርትና ተመርጠው ስለሚመጡበት አግባብ ተገልጧል፡፡ በንኡስ አንቀጽ 1 ላይ መራጮች እነማን እንደኾኑ ሲዘረዝር÷

 • የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
 • ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
 • በጠቅላይ ቤተ ክህነት የመመሪያና የድርጅት ሓላፊዎች፣
 • የየሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣
 • በሀገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ገዳማት አበምኔቶች፣ እመምኔቶች እና የታላላቅ አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
 • በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከየሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት የተወከሉ አራት የካህናት፣ አራት የምእመናንና አራት የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ጠቅላላ ብዛታቸው ከየሀገረ ስብከቱ 12 ሰዎች፣ ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ኮሌጆች የመምህራንና የተማሪዎች ተወካዮች ከየኮሌጆቹ ሁለት ሁለት ሰው፣
 • ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ዕውቅና የሰጠቻቸውና ከቤተ ክርስቲያኗ ጋራ አብረው በመሥራት ላይ የሚገኙ ማኅበራት ተወካዮች የማኅበራቱ አንድ አንድ ሰው እንደኾኑ ያመለክታል፡፡

በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 2 ላይ መራጮች ማሟላት ከሚገባቸው መስፈርቶች መካከል ሕጋዊ የውክልና ሰነድ፣ የሰንበት ት/ቤትና የኮሌጅ ተማሪዎች ተወካዮች 21 ዓመት፣ ከዚህ ውጭ የሚወከሉት ደግሞ 30 ዓመት የሞላቸው፣ የምእመናን ተወካዮች በሙሉ በሥጋ ወደሙ የተወሰኑ፣ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ መኾን እንደሚገባቸው ተጠቅሷል፡፡ የተባሉት መረጃዎች በሚገባ የሚረጋገጡበት መንገድ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 3 ፊደል ተ.ቁ (ሀ) እና (ለ) መራጮቹ የሚላኩበት አገባብ÷ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ በሚላኩ መረጃዎች እንዲሁም በየሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በሚመራ የአስተዳደር ጉባኤ መኾኑ÷ መራጮች በየወገናቸው (ካህናት፣ ምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች) በየራሳቸው ትክክለኛ መድረክ በነጻነት የሚወከሉበትን ዕድል ከማስፋት አኳያ አጠያይቋል፡፡

በረቂቅ ሕጉ በግልጽ የተመለከተ የመንግሥት ተሳትፎ ያለው በታዛቢነት ብቻ ነው፡፡ ይኸውም በአንቀጽ 8 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ የፓትርያሪክ ምርጫ ሂደቱን የሚታዘቡት ከቤተ ክርስቲያኗ ምእመናን ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች 3፣ የአኀት አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች ከእያንዳንዱ 2 ሰዎች ከዓለም አብያተ ክርስቲያን ተወካዮች 2 ሰዎች እንዲሁም በመንግሥት የሚወከሉ 3  ሰዎች በሚለው ተገልጧል፡፡ በዚህ ንኡስ አንቀጽ ከመንግሥት የሚወከሉት 3 ሰዎች መኖራቸው ከቤተ ክርስቲያን ብሔራዊ ክብር አኳያ በጎ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ይኹንና ሃይማኖታዊ እምነታቸው እንዲሁም ለመራጮች የተቀመጠው የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተሳትፎ ተወስኖ አለመቀመጡ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የሚሰጉ አሉ፡፡ በመኾኑም እምነታቸው ተለይቶ መታወቁና የምስጢራተ መረጋገጡ አስፈላጊ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡

በአንቀጽ 11 ‹‹ስለ ቃለ መሐላ የስምምነት ሰነድ››፣ ንኡስ አንቀጽ 1/ለ ‹‹የቅዱስ ፓትርያሪኩ ቃለ መሐላ ይዘት›› አስቀድሞ አምስቱ መሠረተ ሃይማኖትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በማካተት ከተገለጸው በተጨማሪ በወቅታዊ ፈተናዎች ዐይን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንና ሌሎች አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ከሚያደርሱት በደል አንጻር÷ ፓትርያሪኩ ቤተ ክርስቲያኒቱንና መንጋዋን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት የሚመለከት ይዘት እንዲኖረው ሐሳብ ተሰጥቷል፡፡ ይህም የሦስቱን ዐበይት የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት ውሳኔዎች(Creeds) ከመቀበል ጀምሮ ገላጭ በኾነ መንገድ እንዲቀመጥ ተመክሯል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን

ማኅበረ ቅዱሳን

በነገው ዕለት በሚቀጥለው ውይይት የምርጫ ሕግ ረቂቁ ይዘት ሊጨምር ወይም ሊያጥር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በተሠየመው ኮሚቴ በተዘጋጀው የምርጫ ሕግ ረቂቅ ዝግጅት በሞያና መረጃዎችን በማቅረብ የተራዱ ወገኖች መኖራቸው ተነግሯል፡፡ ከእኒህም መካከል ሙሉ የምርጫ ሕግ ረቂቅ መድበል ያቀረበው ማኅበረ ቅዱሳንና የውሉደ አበው ዘተዋሕዶ የአገልጋዮች መድረክ የተሰኘው አካል እንደሚገኝበት ተዘግቧል፡፡ አሁንም÷ ጥያቄው ግን ከአጻጻፉና ከቋንቋ አጠቃቀሙ ጀምሮ ደረጃውን መጠበቅ እንደሚገባው የሚተቸው የሕጉ ረቂቅ÷ የቤተ ክርስቲያናችንን የሰላምና አንድነት ጥያቄዎች እንዲሁም ሌሎች ገንቢ ሐሳቦች ለማጤንና ለማካተት ምን ያህል ክፍት ነው የሚል ነው፡፡

ተጨማሪ ዘገባዎችን ይከታተሉ

Advertisements

3 thoughts on “የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ላይ መወያየት ጀምሯል

 1. andadirgen December 14, 2012 at 6:30 am Reply

  ባሉ በርቱ ሰዎች ቀጥታ የናተን ገጽ ለመጎብኝት እስኪችሉ ድረስ በአንድ አድርገን በኩል ጽሁፋሁን እናስተዋውቅላችኋለን .. እስከ መጨረሻው ለመዝለቅ እንጂ ለማቋረጥ አትስሩ….

 2. Kinfegebriel December 14, 2012 at 1:38 pm Reply

  EGZIABHER tiru Abatin yishumlin eske ahun bekerebew neger lay betam des belognal melkam yehonewun besira lay endina wul, sihtetochin endinastekakil ye kidest betekristianachin ras yehonew irsu Medhanealem Kiristos yirdan.

 3. askale mariam December 17, 2012 at 8:40 am Reply

  EGZIYABIHAR semu ybarek ersu hizibun bemelikam man endemimera yawekal enam ersu yewededewen abat yshumilin egnanem 1 yadergen meliso degemom yadergenal erise bersachin yeminwaded yeminfekaker yefiker sewech endinhon yerdan !!!!!enanteb bertu tebareku !!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: