ፕሬዝዳንቱ በግላቸውም ቢኾን ደብዳቤውን መጻፍ እንደማይችሉ ተገለጸ

  • የፕሬዝዳንደብዳቤ መዘዝ ገና አላበቃም፤ ልዩ አማካሪያቸውም በሠሩት ስሕተት ተጨማሪ መግለጫ እየተጠበቀ ነው
  • ኢንጅነር አራጋው ጥሩነህ ‹‹አሳሳች›› ተባሉ
  • ‹‹ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት ለአገራቸው አፈር እንዲበቁ እንጂ ሌላ ነገር የለም›› /ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ/

በአሜሪካ ዳላስ ቴክሳስ በቅዱስ ሲኖዶስ ልኡካንና በስደት ላይ በሚገኙት ብፁዓን አባቶች መካከል የሚካሄደው ውይይት ሦስተኛ ቀኑን ባስቆጠረበት በዛሬው ዕለት÷ የኢ.ፌ.ዴ.ሪው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለአራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እና ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ‹‹በግላቸው›› እንደጻፉት የተገለጸውና ያለሥልጣናቸው በችኰላና በስሜት የተፈጸመ ስሕተት በመኾኑ እንዲሰበሰብ የተደረገው ደብዳቤ መዘዝ ገና አላበቃም፡፡

ደብዳቤው ቢያንስ የቅዱስ ሲኖዶሱ ልኡካን ከያዟቸው የመነጋገሪያ ነጥቦች ጋራ የማይጣጣም በመኾኑ በልኡካኑ ላይ ቅሬታ ያሳድራል፤ ውጥረት ፈጥሮ ንግግሩን ሊያሰናክለውም ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በባህላችን ሽምግልና የሚከበር ቢኾንም ኢንጅነሩ ፕሬዝዳንቱን ያግባቡት በተወላጅነት ስሜት በተሰባሰቡ ግለሰቦች አማካይነት እንደኾነ በስፋት መነገሩም ምቾት አይሰጥም፡፡ ይህን ተከትሎ ስድስት አባላት ያሉት የአገር ሽማግሌዎች ቡድን አባላት የተባለውን ደብዳቤ እንደማያውቀው ለመንግሥትና ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካላት ማሳወቁ ተዘግቧል፤ ይህንኑም በደብዳቤ እንደሚያሳውቅ ተገልጧል፡፡

ፕሬዝዳንቱ

ፕሬዝዳንቱ

‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ›› የገለጹት የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶ በበኩላቸው ፕሬዝዳንቱ ለማለት የፈለጉት÷ አራተኛው ፓትርያሪክ ወደ አገራቸው መግባት መብታቸው እንደኾነ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት በምርጫው ዕጩ ኾነው መቅረብ እንደሚችሉ መኾኑን በትላንትናው ምሽት ለሬዲዮው ተናግረዋል፡፡ በርግጥም ደብዳቤውን መዘዘኛ የሚያደርገውም በዚህ የአቶ አሰፋ ከሲቶ አስተያየት ሳቢያ ከድጡ ወደ ማጡ የሄደው የመንግሥት ስሕተት ነው፡፡

ከሁሉ በፊት አቶ አሰፋ የጠቀሱት ሕገ ቤተ ክርስቲያን÷ አራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው የሚመለሱት ‹‹ዳግመኛ ዕጩ ኾነው ቀርበው በመወዳደር ነው›› ስለማይል በአላዋቂነት የተነገረ ነው፡፡ በፍትሐ ነገሥቱ የፍትሕ መንፈሳዊ ክፍል አንቀጽ 4 ንኡስ አንቀጽ 70 በተደነገገው መሠረት÷ በአንድ አገር/መንበር ሁለት ፓትርያሪክ የሚሾምበት ኹኔታ ቢኖር መንበሩን ለሚገባው ለመወሰን የሹመት ቅድምና ይህም ባይሆን በታቦቱ ፊት በሚወጣው ዕጣ መሠረት እንደኾነ ይደነግጋል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ተጨባጭ ኹኔታ ሁለት ፓትርያሪኮች የነበሩበት ዘመን በእግዚአብሔር ጊዜ መፍትሔ አግኝቶ አንዱ ቀርተዋል፡፡ ሦስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የዳላሱ ውይይት እኚህ የቀደሙት ፓትርያሪክ እንደምን ከሥልጣን እንደወረዱ፣ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ አልያም እንዳይመለሱ ቢወሰን ከታሪክ፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ከትውፊት አንጻር የሚኖረው ተጽዕኖ በሰላምና አንድነት ጉባኤው አማካይነት በአጀንዳነት ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት በመኾኑ በዚያው መፍትሔ እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡ ከዚሁ ጋራ የተያያዘው የአቶ አሰፋ ከሲቶ ስሕተት መንግሥት ለዕርቀ ሰላሙ ሳይሆን ለምርጫው ትኩረት እንደሰጠ በሚያሳብቅ አኳኋን መገለጹ ነው፡፡

ልዩ አማካሪው ለሬዲዮው የሰጡት ማብራሪያ የመንበረ ፓትርያሪኩን ከፍተኛ ሓላፊዎችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን አሳዝኗል፡፡ ይህም በፈጠረው ግፊት ልዩ አማካሪው ዳግመኛ በመንግሥት ብዙኀን መገናኛ ሌላ የማስተካከያ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሳይታዘዙበት እንደማይቀር መንግሥታዊ ምንጮች እያመለከቱ ነው፡፡ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዛሬ፣ ኅዳር 28 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ጋራ በነበራቸው አጭር ቆይታ ምላሽ የሰጡበት መንገድም ይኸው የአቶ አሰፋ ከሲቶ አስተያየት የፈጠረው ጫና በጉልሕ የታየበት እንደኾነ እየተተቸ ነው፡፡

ዐቃቤ መንበሩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል

ፕሬዝዳንቱ ደብዳቤውን ‹‹በግላቸው ለመጻፍ ያሳመናቸው››÷ ‹‹በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሲኖዶስ አያስፈልግም፤ የሄዱት ሰውዬ ወደ መንበራቸው ቢመለሱ ምናለበት በሚል ነው፤›› የሚል መኾኑ በተለያዩ የጡመራ መድረኰችና በማኅበራዊ ድረ ገጾች ምስጋናና አድናቆት አትርፎላቸዋል፡፡ ይኹንና ነገሩ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ መኾኑን ለሬዲዮው የተናገሩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል÷ ፕሬዝዳንቱ ስለ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና የሚመለከታቸው ነገር ባለመኖሩ እንደግልም ቢኾን መጻፍ እንደማይችሉ ነው ያሳሰቡት፡፡

ፕሬዝዳንቱን ያሳሳቷቸው ግለሰቦች መኾናቸውን አያይዘው የገለጹት ብፁዕነታቸው÷ መንግሥት ድርጊቱን መቃወሙን፣ ደብዳቤውም እንዲሰበሰብ ማዘዙን አስታውቀዋል፡፡ እንደ መንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች ገለጻ÷ ፕሬዝዳንቱ የቀደመው የሬዲዮው ምልልሳቸው በተሰማ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የዘለቁ የመንግሥት ሰዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተላከውን ደብዳቤ ይዘው ሄደዋል፡፡ ዐቃቤ መንበሩም ከአንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ጋራ በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ፕሬዝዳንቱን በስልክ እንዲያነጋግሯቸው ተደርጓል፤ ፕሬዝዳንቱም ራሳቸውን የተቃረኑበትንና ደብዳቤያቸውን የሳቡበትን ሁለተኛውን ማስተባበያ ለሬዲዮው እንዲሰጡ ታዝዘዋል፡፡

በዐቃቤ መንበሩ አገላለጽ ‹አሳሳች› የተባሉትና ደብዳቤው እንዲጻፍ ምክንያት ኾነዋል የተባሉት ኢንጅነር አራጋው ጥሩነህ÷ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ሊያነጋግራቸው ቢፈልግም ‹‹ስላመመኝ ሲሻለኝ ሌላ ጊዜ አገኝሃለኹ›› በሚል ምክንያት አስተያየታቸው ሳይደመጥ ቀርቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ አራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገራቸው ገብተው፣ አስፈላጊው ሁሉ ተሟልቶላቸው በመረጡት ስፍራ እንዲቀመጡ ውሳኔ ማሳለፉን ያወሱት ዐቃቤ መንበሩ÷ ‹‹አሁንም ቅዱስ ሲኖዶስ ቀድሞ በወሰነላቸው መሠረት ወደ አገራቸው እንዲገቡ፣ ለአገራቸው አፈር እንዲበቁ እንጂ ከዚህ ውጭ ሌላ ነገር የለም፤›› በማለት በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡

በፕሬዝዳንት ግርማ ደብዳቤ ሳቢያ ክሡት እንደኾነ የተገመተው የመንግሥት ፍላጎትና በእርሱም የተነሣ የሚካሄዱ ምልልሶች የዕርቀ ሰላሙን ሂደት ሊያውኩ የሚችሉ እንዲህ ዐይነት ምልልሶችን እንደ ሚያስከትሉ ቀድሞም የተገመተ ነበር፡፡ ልኡካኑ በመልካም የንግግር መንፈስ ላይ እንዳሉ እየተዘገበ በሚገኝበት ወቅት እንዲህ ዐይነቶቹ አቋሞች የቱንም ያህል ትክክል ቢኾኑ ከድርድር መድረኩ ውጭ መደመጣቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ብዙዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: