የዕርቀ ሰላሙ ልኡክ ወደ አሜሪካ አመራ

• ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በልኡካን ቡድኑ ውስጥ ተካተዋል
• ዕርቀ ሰላሙ ሰፊ የአገልጋዮችና ምእመናን ንቅናቄ ሊደረግበት ይገባል

በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙት አባቶች ጋራ የሚነጋገረው የቅዱስ ሲኖዶስ ልኡክ ዛሬ፣ ኅዳር 24 ቀን 2005 ዓ.ም ማምሻውን ወደዚያው አምርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ባመቻቸው መድረክ መሠረት ከኅዳር 26 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በዳላስ ቴክሳስ እንደሚጀመር የሚጠበቀው የዕርቀ ሰላም ንግግር እስከ ኅዳር 30 ቀን ሊዘልቅ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ

ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ

የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በልኡክነት የሠየማቸው ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስና ብፁዕ አቡነ ገሪማ ናቸው፡፡ በቡድኑ ጸሐፊነት የልኡኩ አባል ከኾኑ በኋላ ተወግደው የነበሩት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ተመልሰው እንዲካተቱ መደረጉ ለዕርቀ ሰላሙ በሚኖራቸው አስተዋፅኦ ላይ ጥያቄዎች እየተነሡ ነው፡፡ ንቡረ እዱ በአዲሱ አደረጃጀት መሠረት ሥራ አስኪያጅ ከነበሩበት የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በዐቃቤ መንበሩ ብቸኛ ውሳኔ ተነሥተው በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የመንፈሳዊ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኾነው እንደተሾሙ መነገሩም ኅዳር 30 ቀን ከተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በኋላ ይጀመራል ከተባለው የፓትርያሪክ ምርጫ ሂደት አንጻር ንቡረ እዱ እንዲኖራቸው በተፈለገው አስተዋፅኦ ላይ የተነሣውን ጥርጣሬ የሚያጠናክር ነው ተብሏል፡፡

የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ባስቀመጠው መሠረት የልኡካን ቡድኑ በዝርዝር ያልተገለጹ አምስት የመደራደሪያ ነጥቦች መያዙ ተጠቁሟል፡፡ አራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ድምፃቸውን እንዲያሰሙና ወደ መንበር ስለ መመለስ ፈቃዳቸውን እንዲያስታውቁ እየተጠየቀ ባለበት ወቅት የቅዱስ ሲኖዶሱ ልኡክ በሁለቱም ወገኖች በኩል የተላለፈው ውግዘት ተነሥቶ፣ ፓትርያሪኩ ወደ አገር ቤት ተመልሰው በመረጡት ስፍራ አስፈላጊው ሁሉ ተሟልቶላቸው እንዲቀመጡ፣ ለቀጣዩ ፓትርያሪክ ምርጫ ሂደትም ቡራኬያቸውን እንዲሰጡ ይጠይቃል ተብሏል፡፡
በውግዘት የተለያዩት ተነጋጋሪ ወገኖች ባወጧቸው ተፃራሪ መግለጫዎችና ባስቀመጧቸው ቅድመ ኹኔታዎች ሳቢያ የዕርቀ ሰላም ውይይቱ ከወዲሁ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ እየተገለጸ ነው፡፡ በሁለቱም ወገኖች በኩል አቋሞች በይፋ በወጡበት ኹኔታ ነገ የሚጀመረው ውይይት ውጤቱ ቀድሞ ለታወቀ ጉዳይ ጊዜንና ገንዘብን እንደማባከን አድርገው የሚቆጥሩ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ ከስድስተኛው ፓትርያሪክ ሹመት አስቀድሞ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የሚያደርገው የመጨረሻ ጥረት ነው መባሉም ውጤቱ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠብቀው አገልጋይና ምእመን ቁጥርም ጥቂት አይደለም፡፡ በመኾኑም የዕርቀ ሰላም ሂደቱ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ካለው ፋይዳ አንጻር አገልጋዩና ምእመኑም በባለቤትነት ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር ግፊት እንዲያካሄድበት እየተጠየቀ ነው፡፡

Advertisements
%d bloggers like this: