ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ በፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ላይ ይመክራል

• አርቃቂ ኮሚቴው ነገ የማጠቃለያ ውይይት ያደርጋል
• በረቂቁ ላይ ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል
• የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያው ተጓቷል

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት

በጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በተቋቋመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎች ኮሚቴ ሲዘጋጅ የቆየው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ በመጪው ዓርብ፣ ኅዳር 28 ቀን 2005 ዓ.ም ለቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ እንደሚመከርበት የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች ገለጹ፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

አራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሁለት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና አንድ ከፍተኛ የሕግ ምሁር በአባልነት በሚገኙበት አርቃቂ ኮሚቴ የተሰናዳው የምርጫ ሕግ ዝግጅት÷ የቀደሙት አምስት ፓትርያሪኮች የተመረጡባቸውን ደንቦች፣ የአኀት አብያተ ክርስቲያንን በተለይም የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን የምርጫ ሕግና ተዛማጅ ጥናቶች በማገናዘብ እንዲሁም በወቅታዊና መፃኢ የቤተ ክርስቲያን ኹኔታዎች ላይ በተወሰዱ ግምገማዎች ላይ የተመሠረተ ነው ተብሏል፡፡ የምርጫ ሕጉ አገልግሎት ከኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በይፋ እንደሚጀመር ለሚጠበቀው የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ብቻ ይኹን አልያም በቋሚነት ይኹን በምልአተ ጉባኤው ውሳኔ እንደሚረጋገጥ ተጠቁሟል፡፡

የምርጫ ሕጉ ረቂቅ የፊታችን ዐርብ ዐሥራ አምስት አባላት ላሉት ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ከመቅረቡ በፊት ነገ፣ ኅዳር 26 ቀን 2005 ዓ.ም መላው የኮሚቴው አባላት በተገኙበት የማጠቃለያ ውይይት እንደሚካሄድበት ተገልጧል፡፡ የኮሚቴው አባላት ዝርዝር ከብፁዓን አባቶች÷ አቡነ ገብርኤል፣ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ አቡነ ቄርሎስ እና አቡነ ሳሙኤል ናቸው፡፡ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን÷ የሊቃውንት ጉባኤ አባል የኾኑት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁንና ሊቀ ኅሩያን መሐሪ አስረስ (የሕግ ባለሞያም ጭምር ናቸው) እና ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ ይገኙበታል፡፡

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በኮሚቴ ሰብሳቢነት በመሩት በሕግ ረቂቁ ዝግጅት ሂደት÷ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ እና በተወሰነ መልኩ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በሕመም ሳቢያ እክሎች ገጥመዋቸው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ኮሚቴው ተገቢውን የባለሞያዎች እና የአስፈላጊ መረጃዎች ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ጉልሕ ሚና መጫወታቸው ተዘግቧል፡፡ ከዚህ አኳያ ሂደቱ በብፁዕነታቸው ብቸኛ ቁጥጥር ሥር እንደኾነና ለተሳትፎም ዝግ እንደ ነበር በአንዳንዶች የሚናፈሰው አሉባልታ ብፁዓን አባቶችን ለመከፋፈልና ሂደቱን ተቀባይነት ለማሳጣት ያለሙ አካላት አጀንዳ ሊኾን እንደሚችል ምንጮቹ ያላቸውን አስተያየት ተናግረዋል፡፡

የምርጫ ሕጉ ረቂቅ ለቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ቀርቦ ከተመከረበት በኋላ ቅ/ሲኖዶሱ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት በይዘትም ይኹን በሚሸፍናቸው ዐበይትና ዝርዝር ጉዳዮች የበለጠ የሚዳብርበት ሰፊና አሳታፊ የኾኑ ተጨማሪ መድረኮች እንደሚመቻች ምንጮቹ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ከፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ጋራ በዚሁ ኮሚቴ ተሰናድቶ ለኅዳር 30 ቀን እንዲቀርብ በምልአተ ጉባኤው የተወሰነው የ1991 ዓ.ም የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ዝግጅት ሊጠናቀቅ እንደማይችል እየተነገረ ነው፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሥልጣን የመጨረሻ ባለቤት የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመራበት ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከሚሻሻለው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ጋራ በሚኖረው ዝምድና ላይ የቅደም ተከተልና የተመጋጋቢነት ጥያቄ ሊያሥነሳ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: