የዋልድባ አብረንታንት መነኰሳት ውሳኔያቸውን የሚያሳውቁበት ቀን ተቀጠረባቸው

• ‹‹እኛ እናታችንን ልንሸጥ አልመጣንም፤ እናት አትሸጥም፤ ቤተ ክርስቲያንን ሸጠን ካሳ አንበላም፡፡›› /መነኰሳቱ ለባለሥልጣናቱ የተናገሩት/
• ሌሎች የዋልድባ ገዳማት ለስብሰባው አለመጠራታቸው አነጋጋሪ ኾኗል
የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት በሚገኝበት ምዕራባዊ ትግራይ ወልቃይት ወረዳ ማይ ገባ ከተማ ላይ በፕሮጀክቱ ሳቢያ ስለሚነሡት በርካታ አብያተ ክርስቲያን በምትኩም ይከፈላል ስለተባለው ካሳ ለመምከር ከትላንት በስቲያ፣ ኅዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም ስብሰባ የተጠሩት የዋልድባ አብረንታንት መነኰሳት÷ ‹‹እኛ እናታችንን ልንሸጥ አልመጣንም፤ እናት አትሸጥም፤ ቤተ ክርስቲያንን ሸጠን ካሳ አንበላም፤›› በሚል የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማግባቢያ ሳይቀበሉት መቅረታቸው ተገለጸ፡፡

የገዳሙ እቃ ቤት


የሰሜን ምዕራብ ትግራይ – ሽሬ እንዳሥላሴና የሑመራ ዞኖች እንዲሁም የምዕራብ ትግራይ ወልቃይት ወረዳ እና የፀለምት – ማይ ፀብሪ ወረዳ ባለሥልጣናት ከስኳር ኮርፖሬሽን ተወካይ ጋራ እንደተገኙበት በተገለጸው በዚሁ ስብሰባ÷ በዛሬማ ወንዝ ላይ የሚሠራው ግድብ የሚሸፍናቸው 4 የገዳሙ አብያተ ክርስቲያንና 18 ያህል የገጠር አብያተ ክርስቲያን እንዲነሡ፣ ስለዚህም መንግሥት ካሳ ለመክፈል የተዘጋጀ በመኾኑ ማኅበረ መነኰሳቱ የፕሮጀክቱን ዕቅድ በፈቃዳቸው ስለመቀበላቸው ውሳኔያቸውን እንዲያስታውቁ ተጠይቀዋል፡፡
በቁጥር 800 የሚኾኑ አበው መነኰሳት ካሉበት የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ዘቤተ ሚናስ ማኅበር ኻያ ያህሉ በማኅበሩ ተወክለው በተገኙበት በተካሄደው ስብሰባ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ÷ ‹‹አሁን ወደ ሥራ ልንገባ ስለሆነና ቤተ ክርስቲያኖችን ለማንሣት ስለምንፈልግ ውሳኔያችኹን እንፈልጋለን። ለሚነሡት ቤተ ክርስቲያኖችም ካሳ እንሰጣለን፤›› የሚል ሐሳብ ማቅረባቸው ተገልጧል፡፡ የዜናው ምንጮች እንዳብራሩት የማኅበረ መነኮሳቱ ተወካዮች ባለሥልጣናቱ ካሳን አስመልክቶ ስላነሡት ሐሳብ በሰጡት ምላሽ÷ ‹‹እኛ እዚህ የመጣነው፣ የተሰበሰብነው ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ልንሰማ እንጅ ልንወስን አይደለም፤ እኛ አፈር ጠባቂዎች ነን፤ እናታችንን ልንሸጥ አልመጣንም፤ እናት አትሸጥም፤ ቤተ ክርስቲያንን ሸጠን ካሳ አንበላም፤›› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
የማኅበረ መነኰሳቱን አቋም በተመለከተም ‹‹ይህን ማኅበሩ ይመልስላችኹ›› በማለታቸው ስብሰባው ሳይቋጭ ለጥር 4 ቀን 2005 ዓ.ም መተላለፉ ተገልጧል፡፡ ‹‹አስባችኹ ውሳኔያችኹን አሳውቁን›› በሚል አጽንዖት ስብሰባውን የዘጉት የመንግሥት ባለሥልጣናቱ በፕሮጀክቱ አቀባበል ላይ ሦስቱም የዋልድባ ገዳማት (የዋልድባ አብረንታንት መድኃኔዓለም ዘቤተ ሚናስ፣ የሰቋር ኪዳነ ምሕረት ዘገዳመ ዋሊ ቅድስት፣ የደልሽሐ ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ ደናግል ገዳማት) ተመሳሳይ አቋም እያላቸው ከዋልድባ አብረንታንት ገዳም ዘቤተ ሚናስ ማኅበር ብቻ ሠላሳ ተወካዮች እንዲላኩ ለይተው የጠሩበት ኹኔታ ቀጣይ የመንግሥት ርምጃን በተመለከተ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬን አጭሯል፡፡
የማየ ሕርገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የዕጣኖ ቅድስት ማርያም፣ የደላስ ቆቃህ አቡነ አረጋዊ እና የቅዱስ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያን የዋልድባ ገዳም የገቢ ምንጭና መተዳደርያ የኾኑ የእርሻና የአዝመራ ይዞታዎች የሚገኙባቸው ናቸው፡፡ አብያተ ክርስቲያኑ እህል አይዘራብሽ፤ ኀጢአት አይሻገርብሽ በተባለችው የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ከሙዝ ተክል የሚዘጋጀው ቋርፍ የሚዘጋጅባቸው፣ ቋርፉ ያልተስማማቸው ሕሙማንና አረጋውያን ከቋርፍ ቤት ወደ እህል ቤት ወጥተው እህል የሚቀምሱባቸውና ጥንታውያን የሴቶች መነኰሳዪያት መኖርያዎች የሚገኙባቸው ወሳኝ የገዳሙ መተዳደሪያዎች ናቸው፡፡ የሦስቱ ገዳማት ማኅበረ መነኰሳት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ እኒህን ወሳኝ የገዳሙ መተዳደሪያ ቦታዎች ማጥፋት መነኰሳቱን፣ መናንያኑንና ተማሪዎችን ለስደት እንዲገፋና የገዳሙ ታሪክ እንዲያከትምለት መፍረድ እንደኾነ ተገልጾ ነበር፡፡
ፕሮጀክቱ በዋልድባ ገዳም ህልውናና ክብር ላይ ከሚያደርሰው ተጨባጭ አደጋና ከሚጋርጠው ቀጣይ ስጋት አኳያ በአቋማቸው የጸኑትን ማኅበረ መነኰሳት አሳምኖ አራቱን የገዳሙን አብያተ ክርስቲያን አስቀድሞ ማንሣት በሚፈጥረው አመቺ ኅሊናዊ ኹኔታ በሌሎቹ ዐሥራ ስምንት የገጠር አብያተ ክርስቲያን ላይ ተመሳሳይ ርምጃ ለመውሰድ መታቀዱ ነው የተመለከተው፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ገዳሙ ሕፃናትን እያስተማረና መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠ ያቀናቸውና ምእመኑ በሚያበረክተው የነፍስ ዐሥራት በኢኮኖሚ የሚደግፍባቸው ሰበካዎች መኾናቸው ተዘግቧል፡፡ አጥቢያዎቹ በዐሥራ አንድ መንደሮች በሚቋቋሙና ከገዳሙ እስከ 36 ኪ.ሜ ርቀት በሚመሠረቱ አዲስ ሰፈራዎች እንደሚተኩ ቢነገርም ትላንት የተደረገው ማኅበረ መነኰሳቱን አስቀድሞ የማሳመን አካሄድ የምእመናን ተቃውሞ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የተሸጋገረባቸውን ቀበሌዎች አቋም ለማላላትና ለማሳመን ያለመ መኾኑ ተመልክቷል፡፡

Advertisements

One thought on “የዋልድባ አብረንታንት መነኰሳት ውሳኔያቸውን የሚያሳውቁበት ቀን ተቀጠረባቸው

  1. T/MARIAM December 11, 2012 at 10:31 am Reply

    LEZIH HULU TETEYAKI HAGERE SIBKET NEW. KE DEHA KAHNAT BE SHIWOCH YEMIKOTERU BIRROCHIN KEMEKEBEL ANSITO ESKE FERIHA EGZIABHER YELELACHEWN SEWOCH BE BETEKIRISTIAN GUBO EYETEKEBELE BMESEBSEBU NEW. EGZIABHER LE ETHIOPIA BETEKIRISTIAN FIRD MESTETU AYKERIM….GETA HOY TOLO NA

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: