የዋልድባ መነኰሳት ማይ ገባ ላይ ስብሰባ ተጠርተዋል

  • ‹‹በዓዲ አርቃይ ወረዳ በርካታ አድባራት ከዋልድባ ችግር ጋራ በተያያዘ ፐርሰንት አንከፍልም በማለት ዐምፀዋል፡፡›› /የሀ/ስብከቱ ሪፖርት/
  • የዋልድባ ደልሽሐ ኪዳነ ምሕረት መነኰሳዪያት የድረሱልኝ ጥሪ አቅርበዋል

የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት በዋልድባ ገዳም ህልውና እና ክብር ላይ ስለሚያስከትለው ተጨባጭ አደጋና በቀጣይ ስላሳደረው ስጋት የተነሣው ተቃውሞ እልባት ባላገኘበትና ከዚህም ጋራ በተያያዘ የመነኰሳቱ ስደትና እንግልት በቀጠለበት ኹኔታ የስኳር ኮርፖሬሽን መነኰሳቱን ለስብሰባ መጥራቱ ተሰማ፡፡

ስለ ኮርፖሬሽኑ የ2005 ዓ.ም የሩብ ዓመት ዕቅድ ክንውን መግለጫ የሰጡት የኮርፖሬሽኑ ሓላፊዎች÷ ከማኅበረ መነኰሳቱ ጋራ የተፈጠረው አለመግባባት የፕሮጀክቱን ጥቅም ካለመረዳት የመነጨ መኾኑንና ፕሮጀክቱ ገዳሙን ቢጠቅም እንጂ እንደማይጎዳ መናገራቸው በማኅበረ መነኰሳቱ ዘንድ አሁንም ተቀባይነት እንዳላገኘ ተዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ ኹኔታ ለ31ው የመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ውብሸት በቀረበው ሪፖርት÷ በዛሬማ ወንዝ ላይ በሚሠራው ግድብ ምክንያት የተነሣው ውዝግብ በተቀናጀ የቡድን ተልእኰ መረጋጋት ስለመቻሉ የተሰማው ዘገባ ከእውነት የራቀ መኾኑን መነኰሳቱ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ካቀረበው ሪፖርት ጋራ የተጋጨበት ኹኔታ በአስረጅነት ተጠቅሷል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሪፖርት በአንድ በኩል÷ በዛሬማ ወንዝ መገደብ የተነሣ በዋልድባ ገዳም ውዝግብ መነሣቱንና ይህም በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ሥነ ልቡናዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን አምኖ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከፌዴራል መንግሥት፣ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተውጣጣ ልኡክ ቦታው ድረስ ተጉዞ ባቀረበው ሐሳብ መነሻነት በደባርቅ፣ በዛሬማና በዓዲ አርቃይ ከተማዎች በተካሄዱ የሕዝብ ኮንፈረንሶች ሕዝበ ክርስቲያኑን ለማረጋጋትና ግንዛቤ ለማስጨበጥ መቻሉን ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል በሀ/ስብከቱ ስላጋጠሙ ችግሮች በዝርዝር ካመለከታቸው ነጥቦች መካከል ግን የሚከተለው ይጠቀሳል – ‹‹በአልፋ ወረዳ 12 አድባራት ፐርሰንት አንከፍልም ብለው ማመፅና በዓዲ አርቃይ ወረዳ በርካታ አድባራት ከዋልድባ ችግር ጋራ በተያያዘ ፐርሰንት አንከፍልም በማለት ማመፅ፤ በውይይትና በምክር ያልተመለሱትን በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡››

ኮርፖሬሽኑ ዛሬ፣ ኅዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም በማይገባ ከተማ በጠራው ስብሰባ በፕሮጀክቱ አቀባበል ላይ ማግባባቱ አልያም ማስፈራራቱ እንደሚቀጥል የሚጠበቅ ሲሆን ከዋልድባ አብረንታንት ገዳም ሠላሳ መነኰሳት እንዲገኙ ጥሪ ተላልፏል ተብሏል፡፡ የገዳሙ ምንጮች እንደሚሉት ማኅበረ መነኰሳቱ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ያላቸው ፈቃደኝነት ‹‹ከዚህ በፊት በነበሩት መድረኰች ካጋጠማቸው የመደመጥ ችግር የተነሣ አጠራጣሪ ነው፡፡››

በተያያዘ ዜና በሰሜን ጎንደር ዓዲ አርቃይ ወረዳ የሚገኘውና ከዋልድባ ገዳማት አንዱ የኾነው የዋልድባ ደልሽሐ ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ ደናግል ገዳም የአስቸኳይ ርዳታ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ከ400 ያላነሱ መነኰሳዪያት የሚገኙበትን ገዳም በዘላቂ የራስ አገዝ ልማት ፕሮጀክቶች ለመርዳት በሀገረ ስብከቱ ጥያቄና በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የዕቅድና ልማት መመሪያ ፈቃድ ቀደም ሲል ገዳሙን በተለያዩ መንገዶች ሲረዱ የቆዩ ታዋቂ ምእመናን የሚገኙበት የልማት ኰሚቴ ተቋቁሟል፡፡

ኰሚቴው ለሚዲያ አካላት ባሠራጨው ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው በአካባቢው በሚታየው የአየር ለውጥ ፍሬ አልባ በኾኑት የገዳሙ የዳጉሳና የማሽላ ሰብሎች ሳቢያ እስከ መጪው ጥር ወር ድረስ መድረስ ይገባቸዋል ያላቸውን የርዳታ ዐይነቶች ሲዘረዝር፡- 50 ኵንታል ዘንጋዳ፣ 50 ኵንታል ባቄላ፣ 50 ኵንታል ዳጉሳ፣ ጨው፣ በርበሬ እና እያንዳንዳቸው ሠላሳ ሜትር የኾኑና መነኰሳዪያቱ ቀሚስ፣ ቆብ፣ መቀነትና ነጣላ የሚያዘጋጁባቸው 60 ጣቃ አቡጀዲ ናቸው፡፡ ጊዜያዊ ርዳታው ከነማጓጓዣ ወጪው እስከ ብር 350,000 ወጪ እንደሚያስፈልግ በኮሚቴው ደብዳቤው ላይ የተመለከተ ሲሆን በጎ አድራጊ ምእመናን የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡

ኮሚቴው አስቸኳይ ርዳታውን ከማሰባሰብ ጎን ለጎን ለገዳሙ የራስ አገዝ ልማት በለያቸው ተግባራት አጠቃላይ ወጪያቸው ከብር 3 – 5 ሚልዮን የሚኾኑ የሚከተሉትን ዕቅዶች አስቀምጧል፡፡

  • ለኳሬዳ ትል (በሞቃት አየር ወቅት በአረጋውያት የመነኰሳዪያት ሰውነት እያሳበጠ የሚያሠቃይ ነው) መራቢያ ምቹ ኹኔታ የፈጠሩትን የሣር ክዳን ጎጆዎች በቆርቆሮ ለመለወጥ፤
  • ከዕንጨት በመሥራታቸው ለምስጥ ጥቃት እየተጋለጡ ቶሎ የሚፈርሱትን ቤተ እግዚአብሔር (የአረጋውያንና ሕሙማን መጦሪያ) እና ቅራት ቤቶች (የእንግዶች እና ሠራተኛ ወንዶች ማረፊያ) በተወሰነ ከፍታ በኮንክሪት ለመገንባት፤
  • የውኃ መሳቢያ ሞተር፣ የውኃ ማጠራቀሚያ ታንክ፣ የልብስ ማጠቢያ ገንዳዎችና የገላ መታጠቢያ ቤቶች ለመሥራት እንዲሁም የመስኖ ልማት ማካሄድ፤
  • የእህል ወፍጮ በገዳሙ ውስጥ ወይም በአቅራቢያው ለመትከል፤
  • የገዳሙን ልማት በቀጣይነት ለማገዝ እንዲያስችል በጎንደር ከተማ አዘ ጸለየ በተሰኘው አክስዮን ማኅበር በብር 700,000 ወጪ የሚሠራውን ባለአራት ደጃፍ ሱቅ ማስጨረስ፤
  • በፀሐይ ኀይል የሚሠሩ የኀይል ምንጮችን በመትከል የማኅበረ ደናግሉን የጸሎት ጊዜ፣ የሥራና ጤንነት ኹኔታዎች ማሻሻል፤
  • የቦታውን ተፈጥሯዊ ሀብት በመጠቀም ዘመናዊ የንብ ማነብ እና የማር ምርት ለማካሄድ፤

አስቸኳይ ርዳታውንም ይኹን ለዘላቂ የራስ አገዝ ልማት ፕሮጀክቱ ድጋፋቸውን መስጠት የሚሹ ወገኖች በተከታዩ አድራሻ መጠቀም እንደሚችሉ በደብዳቤው ላይ ተመልክቷል፡፡

የኮሚቴው አድራሻ፡- c/o እማሆይ አስካለ ማርያም ወልደ ሳሙኤል

                   ስልክ ቁጥር፡- 09-1-1975582

የባንክ ሒሳብ ቁጥር፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የቁጠባ ሒሳብ ቁጥር – 1000031033296

አስቸኳይ ጥሪው የተላለፈበትን ደብዳቤ ከዚህ ቀጥለው ይመልከቱ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: