ሕዝብ ሲያዝን እግዚአብሔርም ያዝናል – ከምርጫው በፊት ለዕርቀ ሰላሙ ሰፊ ጊዜ ይሰጥ!!

(ውሉደ አበው ዘተዋሕዶ)

በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከር እና መስፋፋት ወሳኝ ኾነው ከወጡት ጉዳዮች መካከል በውግዘት    በተለያዩትአባቶች  መካከልየተጀመረውየዕርቀሰላምሂደትመልካምፍጻሜአግኝቶየቤተክርስቲያንን ሰላም እና አንድነት ማረጋገጥ፤የሕገቤተክርስቲያን፣የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ፣የቃለዐዋዲው ማሻሻያዎችና  እኒህን ተከትሎ በቤተክርስቲያናችንመዋቅራዊአሠራርዙሪያመፈጸምየሚገባቸውየተቋማዊለውጥአጀንዳዎች ናቸው፡፡ ከእኒህም መካከል የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት የሕገ ቤተ ክርስቲያንና የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ማሻሻያ ዝግጅቱ ተገባዶ የምልአተ ጉባኤውን መጠራት እየተጠባበቀ መኾኑ ሲገለጽ የዕርቀ ሰላም ሂደቱ ከሁለቱም ወገኖች በተሰጡ መግለጫዎች ሳቢያ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባው በፊት በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ አማራጮችን ሲያቀርብ የቆየው ውሉደ አበው ዘተዋሕዶ የተሰኘው የአገልጋዮች መድረክ የሁለቱም ወገኖች መግለጫ ከኅዳር 26 – 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ በሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ውይይት ላይ ስለሚፈጥረው ተጽዕኖ ያለውን ስጋት በመግለጽ ሁሉም ወገኖች ሰፊ ትዕግሥት እንዲኖራቸው ጠይቋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሚያስቸኩላት አስገዳጅ ኹኔታ በሌለበት ለምርጫው የሚጣደፉቱ ‹‹ጎጠኞችናጥቅመኞችናቸው›› የሚለው መድረኩ  ‹‹መዘዙየከፋነውናለዕርቅናሰላምቅድሚያእንስጥ፤ከግብጻውያንወንድሞቻችንእንማር›› በማለት ይመክራል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የቤተ ክርስቲያን አንድነት ጉዳይ የበርካታ ወገኖች ድምፅ የተሰማበት መኾኑን በማስታወስና የሰላም ቀን ምንጊዜም እንደማይመሽ በማሳሰብ የዳላሱ ውይይት ለዕርቀ ሰላሙ ‹‹የመጨረሻጥረትነው›› መባሉም ሊጤን እንደሚገባው መድረኩ ይጠይቃል፡፡ መድረኩ ለአራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም የተማኅፅኖ መልእክት አለው – አንድም፡ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ቡራኬያቸውን እንዲሰጡ፤ አልያም ሥልጣነ ፕትርክናቸው በአባታዊ ቡራኬ ተወስኖ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በቡራኬ እንዲመራ ሁለቱም ወገኖች ፈቃዳቸውን ይኾን ዘንድ፡፡

ሙሉጽሑፉንቀጥሎይመልከቱ፡፡

በወርኀ ጥቅምት የመጀመሪያ ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ 31ው የመንበረ ፓትርያሪክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤና እርሱን ተከትሎም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባዎች ተካሂደዋል፡፡ ሁለቱም ስብሰባዎች በየዓመቱ በዚሁ ወቅት በመደበኛነት የሚካሄዱ ከመሆናቸው አንጻር በተለመደ አቀባበልና አኳኋን ይካኼዱ ይኾን የሚል ጥያቄ አልፎ አልፎ የነበረ ቢኾንም ከአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ሞተ ዕረፍት በኋላ በየፊናቸው የመጀመሪያ ስብሰባ በመኾናቸው የተለያዩ ወገኖች ከሚጠብቋቸው ትንንሽ ወይም ትልልቅ ክንዋኔዎች እና ውሳኔዎች አንጻር አጓጊዎች ነበሩ፡፡ በዚህች አጭር ጽሑፍ በተለይም በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከተላለፉት ውሳኔዎች መካከል አፈጻጸማቸው በጥንቃቄ እና በተጠና መልኩ ሊኾን ይገባል ስለምንላቸው ጉዳዮች ጥቂት ነጥቦችን ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡ ከሁሉ በፊት ግን ምስጋና ለሚገባቸው ሁሉ እነሆ፡፡

በእነዚህ ሁለት ስብሰባዎች ምእመናንና አገልጋዮቿ አባቶቻችንን እንድናከብርና እግዚአብሔርን እንድናመሰግን የሚያደርጉን ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ውሳኔዎችም ተላልፈዋል፡፡ ይበል ከሚባልላቸው ክዋኔዎች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል መልኩ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ስብሰባ ወቅት ከየሀገረ ስብከቱ ለተሰባሰቡት ተወካዮች እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሚመች መልኩ የቀረቡትና ልዩ ልዩ ቁልፍ ጉዳዮችን የዳሰሱት ጥናታዊ ጽሑፎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የእነዚህ ጽሑፎች መቅረብም የፓትርያሪኩን ዕረፍት ተከትለው እየታዩ ያሉት ለውጦች ነጸብራቅ ናቸው ብለን ካመንን ድርጊቱ በራሱ ስላሳለፍነው የመታፈንና የጫና ዘመን የሚነግርን ትልቅ ቁም ነገር አለው፡፡

የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባውን ተከትሎም ለዐሥር ቀናት በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ሲዘክር የነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕድገት የሚበጁ፣ ምእመናንም አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንራመድ የሚያደርጉን ናቸው፡፡ ርግጥ ነው ባለፉት ዓመታት ጥሩ ጥሩ ውሳኔዎች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ የአሁኖቹን ለየት የሚያደርጋቸው ግን እንደተለመደው የአፈጻጸም ሳንካ ካልገጠማቸው መሠረታዊ ለውጦች ሊያመጡ የሚችሉ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ዕድገት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ቦታ በላቀ ኹኔታ ከፍ የሚያደርጉ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ መኾናቸው ነው፡፡ ምናልባት የውሳኔዎች ማማር እና መንጋጋት በራሱ ብቻውን የሚፈይደው ነገር የለምና ተፈጻሚነታቸውን በጋራና በተለየ ጉጉት የምንጠብቀው ይኾናል፡፡ ይህ ግን መልካሙን ዜና እንድንሰማና የመጎብኘታችን ጊዜ ይኾን ብለን እንድንጠይቅ ያደረጉንን አባቶቻችንን በምስጋና እና በአክብሮት እጅ ከመንሳት አይከለክለንም፡፡

ከዚህ በማስከተል በአንዳንድ ውሳኔዎች ላይ ያደረብንን ስጋት እና የተሻለ ይኾናል የምንለውን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡

  1. 1.  ዕርቀ ሰላም እና የፓትርያሪክ ምርጫ

ከፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት በኋላ በእነዚህ ሁለት ዋና ዋና እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፋፊ ዘገባዎች እየቀረቡ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ እንዲያውም ከዘገባዎች ባሻገር የተለያዩ ወገኖች ይበጃሉ የሚሏቸውን ሐሳቦች በፊርማቸው ሳይቀር አስደግፈው ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር፣ የፀረ – ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያንና ዘማርያን ጥምረት፣ የዋልድባን እናድን ዓለም አቀፍ ኮሚቴና በተለያዩ አጥቢያዎች የሚገኙ ምእመናን እንደሚገኙበት ተሰምቷል፡፡

 

በቡድን ከቀረቡት ተመሳሳይ ሐሳቦች ባሻገር በግል ደረጃ ለተለያዩ አባቶች የጉዳዮቹን አሳሳቢነትና የምእመናን የልብ ትርታ ምን እንደኾነ እንዲውቁት ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ብፁዓን የሲኖዶስ አባላት ከተለያዩ ወገኖች ያገኟቸውን የሐሳብ ግብአቶች እንደማይጠቅሙ ሳይቆጥሩ አክብሮት በመስጠት በአጀንዳ እንደተወያዩባቸው ተገልጿል፡፡ ኾኖም ግን የተወሰኑት ውሳኔዎች የአጀንዳዎቹን ክብደት እና አያሌ የቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮች የሰጧቸውን ዋጋ ያላገናዘቡ ናቸው ብንል ማጋነን አይኾንብንም፡፡

በርግጥ አባቶቻችን ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ቤተ ክርስቲያኗንና ምእመናን ይጠብቃሉ እንጂ ምእመናን እነርሱን ይመራሉ ብለን አናምንም፡፡ ይህ መኾኑ ግን አባቶች የልጆቻቸውን ጥያቄዎች ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ወይም በማጣጣል ረግጠዋቸው ይሄዳሉ ማለት አይደለም፡፡ በአንድ በኩል አስተያየቶቹ እና ጥያቄዎቹ ሊናቁ ከማይገባቸው ብዙ ወገኖች የቀረቡ መኾናቸው እየታወቀ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ ሰላም መታሰብ ሲገባው እነዚህን ያላገናዘቡ ውሳኔዎችና ከዚያም በኋላ ከአንዳንድ አባቶች የሚደመጡት ሐሳቦች ፈንጥቆ የነበረውን የተስፋ ብርሃን ሊያጨልሙት እንደሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ከሁሉ በፊት በቤተ ክርስቲያኗ ተከታዮች ዘንድ ያለው እሳቤ ዕርቅ እና የፓትርያሪክ ምርጫ ለየብቻ የሚታዩ ጉዳዮች እንዳልኾኑ ነው፡፡ ይህም ማለት የፓትርያሪክ ምርጫ ከመታሰቡ በፊት የዕርቁን ጉዳይ እልባት መስጠት ግድ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ለአባቶች የቀረቡት ምክረ ሐሳቦችም ኾኑ በተለያዩ ሚዲያዎች የወጡት ጽሑፎች የሚያሳስቡትም ይህንኑ ነው፡፡ የዕርቁ ውጤት ምንም ይኹን ምንም እኛ ግን ስድስተኛውን ፓትርያሪክ እንመርጣለን ብሎ መግለጫ መስጠት ሲጮኸለት የነበረውን ጉዳይ ከትቢያ መደባለቅ ነው፡፡ የዕርቁንም ጉዳይ ከልብ ሳይኾን ለፊት መመለሻ ያህል እንደ አጀንዳ ተደርጎ እንዲቀርብ የተደረገ ያስመስለዋል፡፡ አነጋገሩ እንደ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ይቆጠርም አይቆጠርም ለምሳሌ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ ተብሎ እንደ አማራጭ የሚቀርበውን ሐሳብ ፈጥሞ የማይቀበል ከመኾኑ አንጻር በጉጉት እየተጠበቀ ያለውን ድርድር ከጅምሩ ሊያከሽፍ የሚችል ነው፡፡

ከዚህ በተያያዘ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ በቋሚነት የሚጠቅምና ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ ስንዱ የሚያደርግ በመኾኑ ሁሌም የሚደገፍ ቢኾንም እንዲህ በተዋከበ ኹኔታ ሕጉን ለማውጣት መሯሯጥ የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የግድ አሁንና በፍጥነት መፈጸም አለበት የሚል መልእክት ያለው ነውና ስጋታችንን ዕጥፍ ያደርገዋል፡፡ በእነዚህ ሁለት ታላላቅ አጀንዳዎች ዙሪያ በቂ ጊዜ መስጠት የራሱ የኾነ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በተለይም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለፓትርያሪክ ምርጫ የሚያስቸኵላት አስገዳጅ ኹኔታ አለ ለማለት በማያስደፍርበት ኹኔታ ውስጥ በጥድፊያ ወደ ምርጫው መግባት መዘዙ የከፋ ይኾናል፡፡ ከወንድሞቻችን ግብጻውያን ኮፕቶች መማር ያስፈልገናል፡፡

ሌላው ከምርጫ ጋራ በተያያዘ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ ሂደቱ ነው፡፡ ውጤት የእግዚአብሔር ጥሪና ምርጫ ነው፡፡ ሂደቱ ከተበላሸ ግን የእግዚአብሔር ነው የምንለው ውጤት ሊበላሽ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ሂደቱ ሲበላሽ ኹኔታውን በጉጉት እየተጠባባቀ ያለው ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ያዝናል፡፡ ሕዝብ ሲያዝን እግዚአብሔርም ያዝናል፡፡ ይህም ከላይ እንዳልነው ሁሉንም ሊያበላሸው ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ረድኤቱን ያርቃል፡፡ መንበሩን ለራሳቸው ብቻ ለሚያስቡ በዚህም ምክንያት ደጋፊዎቻቸውን ለማብዛት በሚያደርጉት ዘመቻ ሁሌ እሽ ባይ ጥቅመኞችንና ጎጠኞችን በሚያሰባስቡና በአቦ ባዮች ብቻ መከበብ ለሚፈልጉ ዐምባገነኖች አሳልፎ ይሰጣል፡፡ እውነተኛ የእግዚአብሔር ሰዎች ደግሞ ይህን ማየት አይፈልጉም፡፡ ስለዚህ ለቤተ ክርስቲያንም ለመንጋውም የሚበጀው ቅድምናውን ለሰላም እና ዕርቅ በመስጠት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መመለስ ነው እንላለን፡፡

2. ድርድርንበተመለከተ

ቅዱስ ሲኖዶስ በስብሰባው ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል ከኅዳር 26 – 30 ቀን 2005 ዓ.ም በአሜሪካ ቴክሳስ ዳላስ ውስጥ ለሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ውይይት ሦስት ብፁአን አባቶች ያሉበት ልኡክ መሠየሙ አንዱ እንደኾነ ተነግሯል፡፡ ከዚህ በተያያዘም የልኡኩ መነጋገሪያ የሚኾኑ ዝርዝራቸው ያልታወቁ አምስት ነጥቦችን ማስቀመጡ ተገልጧል፡፡ አምስቱን ጉዳዮች መግለጥ ከድርድሩ በፊት ለሚፈጠሩ ውዥንብሮች በር ላለመክፈት ታስቦ ሊኾን ይችላል የሚል ግምት ቢኖረንም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሰጡት የመጨረሻ ቀን ጋዜጣዊ መግለጫ ግን ሌላ ጥርጣሬ ሊያጭር የሚችል ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ከተሰጠው የመረጃ ውስንነት በመነጨ ጉዳዩን በቅርበት በምንከታተለው ወገኖች ዘንድ እየተፈጠረ ያለው ሌላው ስጋት የመደራደሪያ ነጥቦች ብቻ መቀመጣቸው ድርድሩን ስኬታማ ሊያደርገው ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡

እኒህን ሁለት ስጋቶች የሚያገዝፋቸው ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ከተሰማ በኋላ በስደት የሚገኙት አባቶች በምላሹ ሰጡት የተባለው መግለጫ ይዘት ነው፡፡ ከሁለቱ መግለጫዎች እንደምንረዳው መጪው ድርድር ውጥረት የበዛበት ሊኾን እንደሚችል ነው፡፡ ስለዚህም የቅዱስ ሲኖዶሱ ተደራዳሪ አባቶች ለሥምረቱ አብዝተው ሊጨነቁበት ይገባል፡፡

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ይህ የኅዳር ድርድር የመጨረሻ መኾን አለበት የሚለውና አንዳንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ አባቶች ይዘውታል የሚባለው አቋም ነው፡፡ የዕርቁ ጉዳይ እልባት ያገኝ ዘንድ የተቻለውን ያህል ዋጋ ተከፍሎ እስከ ጥግ ድረስ መሄድ የሚያስፈልግ ቢኾንም ዕርቅ በዋናነት የሁለት ወገኖች ጉዳይ በመኾኑ አንዱ ወገን ብቻ እንዲህ ማሰቡ ሊለዝቡ የሚችሉ ጉዳዮችን አክርሮ ሂደቱን ወደ መክሸፍ ሊያመራው ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር ተደራዳሪ አባቶች ከወዲሁ ከትዕግሥት ጋራ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው እኛ ታናናሽ ልጆቻቸው ልንመክርና ልናሳስብ እንወዳለን፡፡ በሌላ በኩል የሰላም ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር ሙሉ እጆቹን ያስገባ ዘንድ በመላው ዓለም የምንገኝ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ሁሉ በአንድ ልብ እንድንጸልይ አባቶች አጽንዖት ሰጥተው ቢያሳስቡ ከሁሉም ይልቅ የሚበጅ ነው፡፡

ይህን ጽሑፍ ስናጠቃልል ዕርቁ ከሁለት በአንዳቸው ቢደመደም ለዛሬዋም ኾነ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን እጅግ የተሻለ ይኾናል የምንላቸውን አማራጮች ከፍ አድርገን በማስተጋባት ይኾናል፡፡ የመጀመሪያው በስደት ላሉት አባቶች በተለይም ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በተማኅፅኖ መልክ የሚቀርብ ነው፡፡

ቅዱስ አባታችን÷ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሩጫዬን ጨርሻለኹ›› ብለው በታላቅ እና በማይረሳ ክብር ይህችን ምድር ለመሰናበት እና ለቤተ ክርስቲያንም ዘመን የማይሽረው ውለታ ለመዋል ተደራዳሪ አባቶችን፣ ‹‹ልጆቼ÷ እስከ አሁን ላደረጋችኹት ሁሉ እግዚአብሔር ይስጣችኹ፤ ስላከበራችኹኝ እግዚአብሔር ያክብራችኹ፤ ድካማችኹን ማየቴ ብቻ ይበቃኛል፡፡ ከአሁን በኋላ ብዙም ነገር አልፈልግም፡፡ ስለዚህ በግራ ቀኙ ያላችኹት ልጆቼ አንድ ኹናችሁ ወደሚቀጥለው ፓትርያሪክ ምርጫ ግቡ፤›› ብለው ታላቅ የምሥራች ቃልዎን ያሰሙን፡፡ ይህ በእውን ከተሳካ ለቅዱስነታቸው የሚስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው፣ ስማቸው እየተጠራ በመረጡት ቦታ በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ ቢመቻች ከሁሉም ይልቅ የሚሻል ይኾናል፡፡ ኾኖም ይኸኛው አማራጭ በእርሳቸው ተነሣሽነትና መልካም አባታዊ ፈቃድ ብቻ እንጂ የድርድር ነጥብ ባይኾን ይመረጣል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ የመጀመሪያው የማይሳካ ከኾነ በአሁኑ ሰዓት የአብዛኞቹ ሐሳብ የኾነውና የአዲስ አበባዎቹ አባቶች እንደ ዋነኛ መደራደሪያ ሊያደርጉት እንዲሁም በስደት ያሉት አባቶችም ይቀበሉት ዘንድ የግድ የምንለው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥልጣነ ፕትርክናቸው በአባታዊ ቡራኬ ብቻ ተወስኖ በወደዱት ቦታ እንዲቀመጡ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ደግሞ በእንደራሴ እንዲመራ መወሰን ነው፡፡ ከአሁን በፊት ሲገለጽ እንደቆየው በእንደራሴ መመራት ለቤተ ክርስቲያን አዲስ ካለመኾኑ በተጨማሪ ከአሁን በኋላ ለሚኖሩት የፓትርያሪክ ምርጫዎች ሰፊ የዝግጅት ጊዜ ይሰጣል፡፡

ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን ሰላምና አንድነት ይጠብቅልን፡፡ አሜን፡፡                 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: