፮ኛው ፓትርያርክ እንዴት ይመረጡ?

(ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ርእሰ አንቀጽ፤ ፶፮ ዓመት ቍ. ፳፭፤ ጥቅምት ፳፻፭ ዓ.ም)

የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ካሳለፋቸው በርካታ ውሳኔዎች አብዛኛዎቹ ወቅታዊና የሕዝቡን የልብ ትርታ ያዳመጡ በመኾናቸው ሊደገፉ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም የስድስተኛውን ፓትርያርክ ምርጫ አስመልክቶ ያሳለፈው ውሳኔ ቤተ ክርስቲያናችን ለኻያ ዓመታት ያህል የተጓዘችውን ሐዋርያዊ ጉዞ ለማምከን በጥቂቶች ታቅዶ የነበረውን ከንቱ ምኞት ያከሸፈና ግንዛቤ በጎደለው መረጃ በሁሉም ዘንድ ሠርጾ እስከ ዛሬ ድረስ በቂ ምላሽ ሳያገኝ በሕዝቡ ልብ ሲጉላላ ለኖረው ጥያቄ የማያዳግም መልስ የሰጠ ውሳኔ ነው፡፡

ምርጫውን አስመልክቶ የተላለፈው ውሳኔ እስከ ኅዳር ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ድረስ የምርጫ ሕግ እንደሚረቀቅና ኅዳር ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሕጉ ጸድቆ የምርጫው ሂደት እንደሚቀጥል ይጠቁማል፡፡ ይኹን እንጂ በረቂቅ ሕጉ ላይ እነማን መካተት እንዳለባቸው የተብራራ ነገር የለም፡፡ የምርጫው ሕግ ተሻሽሎ ይወጣል ከተባለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ዘለቄታ የሚኖረው ይኹን ወይም ጊዜያዊ የምርጫ ሕግ እንደኾነ ስለማይገልጽ በቅጡ መብራራት አለበት፡፡ በምርጫው ሕግ ረቂቅ ላይም ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋራ ሌሎችም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምሁራን ቢኖሩበት የተሻለ ይኾናል፤ ሐሜትንና ትችትን ያስወግዳል ወይም በጋራ ለመቀበል ያስችላል፡፡ ከዚህም ሌላ ‹‹ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል›› እንደተባለው ችኮላው ተጨማሪ ስሕተት እንዳይፈጥርና እንደተለመደው ከጀርባው ሌላ ግፊት ያለበት እንዳይመስል ለምርጫው ጥራትና ብቃት ሲባል በቂ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል፡፡

ካለፈው ተሞክሮ በመነሣት ከሁሉም እጅግ አሳሳቢው የሚመረጠው አባት የምርጫ አፈጻጸም ጉዳይ ነው፡፡ ከጠላት ወረራ በፊት በጣም ፍጹማን የኾኑት አባቶች ሃይማኖት ላይ ብቻ በማተኰር ለሥራና ጊዜው ለሚጠይቀው ሥልጣኔ ዕንቅፋት ይኾናሉ እየተባለ መለስተኛ የኾኑት የዐፄዎቹ፣ የመኳንንቱ እና የመሳፍንቱ ንስሐ አባቶች ነበሩ ለጵጵስና የሚመረጡት፡፡ ከነጻነት ወዲህ ደግሞ አልፎ አልፎ የወንዝ ጉዳይና የመንግሥት እጅ ቢኖርበትም ከመጀመሪያው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የምርጫ ዘመን ጀምሮ በሹመት ቅድሚያ ያላቸው አባቶች ነበሩ ለፓትርያሪክነቱ ተወዳድረው የሚመረጡት፡፡ በሁለተኛው ፓትርያሪክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የምርጫ ዘመንም የተፈጸመው በዚህ ዐይነት ነበር፡፡

የሦስተኛውና የመናኙ ፓትርያሪክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ ሢመት ግን የጭቁኖች ዘመን ስለነበር የፓትርያሪክነቱ የምርጫ ሥነ ሥርዐት የተካኼደው ከበፊቱ ለየት ባለመልክ ነበር፡፡ ይኸውም ምን ዐይነት አባት ፓትርያሪክ መኾን እንደሚገባው የመላው ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ድምፅ ተሰብስቦ÷ ከተሰበሰበው ድምፅ በተገኘው ውጤት መሠረት ከጳጳሳት ሁለት፣ ከገዳማት መናንያን ሦስት ቆሞሳት ለፓትርያሪክነት ምርጫ በዕጩነት ቀርበው በመወዳደር ነበር ከቆሞሳቱ መካከል መናኙ አባት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በድምፅ ብልጫ አሸንፈው ሦስተኛ ፓትርያሪክ ኾነው የተመረጡት፡፡

አሁንም ቢኾን ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶ በሦስተኛው ፓትርያሪክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የምርጫ ሥነ ሥርዐት አፈጻጸም ቢከናወን አንዱ ወገን ብቻ ሳይኾን ሁሉም የሸክሙ ተካፋይ ሊኾን ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በተሰጠው ሰፊ የሃይማኖት ነጻነት መሠረት የመንግሥት እጅ ይኖርበታል ተብሎ ስለማይታሰብና ሊኖርበትም ስለማይገባ በምንም፣ በማንም ማሳበብ አይቻልም፡፡ ካህናቱና ምእመናኑ የፈለጉትን አባት በነጻነት መምረጥ ይችላሉ፡፡ የዓለም ሕዝቦች በይበልጥ የሚፈልጉትና የሚናፍቁትም ዓለም አቀፋዊውን አባት ብቻ ሳይኾን በጸሎቱ፣ በትሩፋቱ እና በቅድስናው ዓለምን የሚዋጀውን ፍጹም አባት ጭምር ነው፡፡

ከዚህም ጋራ እስከ አሁን በተግባር እንደተረጋገጠው የቅዱሳን ፓትርያሪኮች አንኳር ችግሮቻቸው ቤተሰቦቻቸውና የአካባቢያቸው ሰዎች ስለኾኑ ምንም እንኳን መነኰሳት የመላእክት ዝርያ ባይኾኑም የሚመረጠው አባት እንደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመድ አልባ ቢኾን ይመረጣል፡፡ ‹‹ቤተሰቡን ያልተወ ሊያገለግለኝ አይችልም›› የሚለውም አምላካዊ ቃል በትክክል ተግባራዊ ሊኾን የሚችለው ይህ ሲኾን ብቻ ነው፡፡ ይህን በተመለከተም አዲስ በሚረቀቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ደንብ ሊበጅለት ይገባል፡፡

የቅዱሳን ፓትርያሪኮች የምርጫ ኹኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚስተዋለው በእኛ ብቻ ሳይኾን በሌሎችም አገሮች የሚፈጸመው በዚህ መንገድ እንደኾነ ከግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት መውሰድ ይቻላል፡፡ በዘመነ ሐዋርያት ሊቀ ዲያቆናት እንኳ መምረጥ የሚቻለው በዚህ መልክ እንደነበር የቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን የምርጫ ታሪክ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደ ዘመነ ሐዋርያትና እንደ ግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን አካኼድማ ብንኼድ በማን ዕድላችን? ምርጫውን እግዚአብሔርም ሕዝብም በአንድነት ይስማሙበታልና፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: