የፓትርያሪክ ምርጫው ሰፊ ጊዜ እንዲሰጠው ተጠየቀ

  • በምርጫ ሕጉ የገዳማት መናንያን በዕጩነት የሚካተቱበት ሥርዐት እንዲታይ ተጠቁሟል
  • የሚመረጠው አባት እንደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመድ አልባ ቢኾን ይመረጣል
  • ‹‹የዓለም ሕዝቦች በይበልጥ የሚፈልጉትና የሚናፍቁት ዓለም አቀፋዊውን አባት ብቻ ሳይኾን በጸሎቱ፣ በትሩፋቱ እና በቅድስናው ዓለምን የሚዋጀውን ፍጹም አባት ጭምር ነው፡፡›› /የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ/

መንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚቀመጠው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ምርጫ እግዚአብሔርም ሕዝብም በአንድነት የሚስማሙበት ጥራትና ብቃት ያለው፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምሁራን የሚሳተፉበት፣ የሰፊው ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ድምፅ የሚሰበሰብበት፣ የመንግሥትን እጅ ጨምሮ የውጭ ተጽዕኖን በጋራ በመከላከል ሐሜትንና ትችትን ለማስወገድ የሚያስችል ይኾን ዘንድ ሰፊ ጊዜ እንዲሰጠው ተጠየቀ፡፡ ጥያቄው የቀረበው በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሥር የሚዘጋጀው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ባስነበበው ርእሰ አንቀጽ ነው፡፡

ጋዜጣው በ56 ዓመት ቁጥር 125፣ ጥቅምት 2005 ዓ.ም እትሙ ባወጣው ርእሰ አንቀጽ የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የስድስተኛውን ፓትርያሪክ ምርጫ አስመልክቶ ያሳለፈው ውሳኔ÷ ቤተ ክርስቲያናችን ለኻያ ዓመታት ያህል የተጓዘችውን ሐዋርያዊ ጉዞ ለማምከን በጥቂቶች ታቅዶ የነበረውን ከንቱ ምኞት ያከሸፈና ግንዛቤ በጎደለው መረጃ በሁሉም ዘንድ ሠርጾ እስከ ዛሬ ድረስ በቂ ምላሽ ሳያገኝ በሕዝቡ ልብ ሲጉላላ ለኖረው ጥያቄ የማያዳግም መልስ የሰጠ እንደኾነ ገልጧል፡፡ ርእሰ አንቀጹ ‹‹በጥቂቶች የታቀደ ነበር›› ያለው ‹‹ከንቱ ምኞት›› ምን እንደኾነባያብራራም የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ዝግጅት ከኅዳር 30 ቀን በፊት ተጠናቆ ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ስብሰባ እንደሚጸድቅ የሚጠበቀውን የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ዝግጅት አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች ጠቁሟል፡፡

እንደ ርእሰ አንቀጹ ምልከታ÷ የረቂቅ የምርጫ ሕጉ ዝግጅት እነማን መካተት እንዳለባቸው አያብራራም፡፡ ተሻሽሎ ይወጣል ከተባለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ዘለቄታ የሚኖረው ይኹን ወይም ጊዜያዊ የምርጫ ሕግ እንደኾነ አይገልጽም፡፡ በመኾኑም ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋራ ሌሎችም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምሁራን ቢኖሩበት የተሻለ እንደሚኾን በመጠቆም ይህም ‹‹የምርጫ ሕጉን እንደሚመቻቸው እያዘጋጁ ነው›› ወይም ‹‹ከጀርባው ሌላ ግፊት አለበት›› የሚለውን የተለመደ ሐሜት እና ትችት ለማስወገድ ወይም ሓላፊነቱን በጋራ ለመቀበል እንደሚያስችል ጠቁሟል፡፡ ለምርጫው ሕግ ረቂቅ ዝግጅት የተሰጠው ጊዜም አጭር በመኾኑ ችኮላው ተጨማሪ ስሕተት እንዳይፈጥር ለምርጫው ጥራትና ብቃት ሲባል በቂ ጊዜ ሊሰጠው እንደሚገባ ይመክራል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተሰጠው ‹‹ሰፊ የሃይማኖት ነጻነት›› መሠረት የፓትርያሪክ ምርጫ ሥነ ሥርዐት አፈጻጸሙ የመንግሥት እጅ እንደማይኖርበት ተስፋ የሚያደርገውና ሊኖርበትም እንደማይገባ የሚያሳስበው ርእሰ አንቀጹ የፓትርያሪክ ምርጫ ሂደቱን አስመልክቶ ‹‹በምንም፣ በማንም ማሳበብ አይቻልም›› በማለት ካህናትና ምእመናን የፈለጉትን አባት በነጻነት መምረጥ እንደሚችሉ ያሳስባል፤ የሚመረጠውም አባት የዓለም ሕዝቦች በይበልጥ የሚፈልጉትና የሚናፍቁት ‹‹ዓለም አቀፋዊ አባት ብቻ ሳይኾን በጸሎቱ፣ በትሩፋቱ እና በቅድስናው ዓለምን የሚዋጀውን ፍጹም አባት ጭምር ነው፤››በማለት የሦስተኛው ፓትርያሪክ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት

ን ሢመተ ፕትርክና (የምርጫ ሥነ ሥርዐት) አፈጻጸም በምርጥ ተሞክሮነት ይጠቅሳል፡፡ ይኸውም የምርጫ ሥነ ሥርዐቱ በአንድ በኩል ገዳማውያን መናንያን ከየገዳሙ የታሠሡበት እና በዕጩነት የተካተቱበት ሲኾን በሌላ በኩል ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው ልኡክ በሁሉም አህጉረ ስብከት በመገኘት ሉላዊውና አገራዊው ኹኔታ ስለሚሻው አባት ከአገልጋዩና ምእመኑ ጋራ ግልጽ ውይይት ማካሄዱን ነው፡፡

የግብጽ – ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 118ውን ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስን በመንበረ ማርቆስ በሾመችበት የምርጫ አካሄድ ብንኼድ ‹‹ምንኛ መታደል ነው›› በማለት ሢመተ ፕትርክናውን በአካል በመገኘትና በቀጥታ የብዙኀን መገናኛ ሥርጭት የተከታተሉ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያንን ጠንካራ ምኞት የሚጋራው ርእሰ አንቀጹ አያይዞም÷ በሓላፊነት ላይ የነበሩ የፓትርያሪኮች የሥጋ ዘመዶችና የአካባቢ ሰዎች በተወላጅነት በመሰባሰብ ከፍተኛ ሓላፊነት ለተጣለበት አባታዊ ተግባር ዕንቅፋት ሲፈጥሩ መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡ በዝግጅት ላይ የሚገኘው የምርጫ ሕግ ለዚህ ደንብ የሚያበጅበት ኹኔታ እንዲኖርም ጠይቋል – ‹‹መነኰሳት የመላእክት ዝርያ ባይኾኑም የሚመረጠው አባት እንደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመድ አልባ ቢኾን ይመረጣል፡፡››

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: